አነጋጋሪዉ ባዮፊዩል | ጤና እና አካባቢ | DW | 02.10.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

አነጋጋሪዉ ባዮፊዩል

በጎርጎሮሳዉያኑ 2006ዓ,ም አካባቢ ፅዱና አስተማማኝ የነዳጅ ምንጭ ተደርጎ ብዙ ተወርቶለታል፤ ዓለም በአንድ ቋንቋ የሚናገር እስኪመስል Biofule ከሁሉም አፍ ገባ። ዓመታት ሳይገፉ ግን የምግብ እጥረትና የምግብ ዋጋ መናር Biofuleን ዳግም ዓይን አስገባዉ።

default

የዓለማችን ግንባር ቀደም በቆሎ አምራችና አቅራቢ ሀገር ዩናይትድ ስቴትስ በዘንድሮዉ የሰሜን ንፍቀ-ክበብ የበጋ ወራት ለድርቅ በመጋለጧ የበቆሎ ምርት በከፍተኛ ሁኔታ ተጎድቷል። አዝማሚያዉ በዓለም የምግብ አቅርቦት ላይ አደጋ ያስከትላል በሚል የስጋት የገባዉ የተመድ አሜሪካ ከበቆሎ ነዳጅ ማምረቷን እንድታቆም አሳስቧል። ሁኔታዉ ከመነሻዉ በጥርጣሬ ይታይ የነበረዉን ከተክሎች የሚገኝ ነዳጅ ማለትም Biofule ጥያቄ ላይ ጥሎታል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከምታመርተዉ በቆሎ 40 ከመቶዉ ወደፋብሪካ ገብቶ ወደነዳጅ እንዲለወጥ የሀገሪቱ ህግ ይፈቅዳል። ዘንድሮ ግን በሀገሪቱ ማዕከላዊ ምዕራብ ግዛቶች የበቆሎ እርሻዋ በተከሰተዉ ከባድ ሙቀትና የዝናብ እጥረት ምክንያት ለምርት አልበቃም። ይህም በሀገሪቱ ለወትሮዉ በየዓመቱ ይመረት የነበረዉን መጠን በ12 በመቶ ቀንሶ እጥረትን ሊያስከትል እንደሚችል ይፋ ሆኗል።እንደዉም አሜሪካ ዉስጥ ከ17ዓመታት ወዲህ እጅግ አናሳ ምርት ሲገኝ የዘንድሮዉ የመጀመሪያ መሆኑ ነዉ የተሰማዉ። ባለፈዉ ሰኔ ወር የወጡ ዘገባዎች እንዳመለከቱት አሜሪካና ሩሲያ ዉስጥ የደረሰዉ ድርቅ ሰብሎችን በመጉዳቱ የምግብ ዋጋ 50 በመቶ እንዲንር አድርጓል። ሁኔታዉ ያሰጋዉ የተመ የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት የዋጋ ንረትና የምግብ እህል እጥረት ባለበት በዚህ ወቅት ለሰዎች ምግብነት ሊሆን የሚገባዉ የበቆሎ ምርት ለነዳጅ ማለትም biofuelን ለማምረት እንዳይዉል አሳስቧል።

Biofuel watch የተሰኘዉና ብሪታንያና ዩናይትድ ስቴትስ ባሉ ፅህፈት ቤቶቹ አማካኝነት ይህንኑ ጉዳይ በቅርበት እየተከታተለ መረጃዎችን ይፋ የሚያደርገዉ ተቋም ከተክሎች ይገኛል የሚባለዉን ነዳጅ አጥብቆ ከሚቃወምባቸዉ ነጥቦች መካከል በእርሻዉ ዘርፍ በአንድ የምርት ዓይነት መወሰንን ከማስከተሉ በላይ ለዚህ ተግባር የሚፈለጉ ተክሎችን ፈጥኖ ለማልማት ሲባል የሚዉለዉ ሰዉ ሰራሽ ማዳበሪያ ኬሚካልና የመሳሰለዉ ለአየር ንብረት ለዉጥ አሉታዊ አስተዋፅኦ ማስከተሉን ያነሳል። ለሰዎች ጥቅም ሊዉል የሚገባዉን እህል ከመፍጀቱ ሌላ የምግብ እጥረትን ለማባባስ የመሬት መቀራመትንም እንደሚያስከትል የተቋሙ ተባባሪ ዳይሬክተር አልሙት ኤርኒስቲን ያስረዳሉ፤

Jatropha Pflanze wird als Biokraftstoff angebaut

የጃትሮፋ ተክል

«በምግብ ምርት ላይ የሚያደርሰዉ ተፅዕኖ ከሁለት ወገን  ይታያል፤ በአንድ በኩል የምግብ ዋጋ ላይ ያለዉ ሲሆን፤ ባለፈዉ ዓመት ምግብና እርሻ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪዎች ደረጃ የቀረበ አንድ ቅኝት አለ፤ biofuel ለቅባት እህሎችም ሆነ ለምግብ እህል ዋጋ መናርና አለመረጋጋት ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አመልክቷል። ስለዚህ በተለይ በመላዉ ዓለም ለሚገኙ ድሆችን ኑሮ ለጎዳዉ የዋጋ ንረት ምክንያት ነዉ። ሁለተኛዉ ተፅዕኖ ደግሞ ሰዎች የእርሻ መሬት የማግኘት እድላቸዉን ማጨናገፍና የመሬት ቅርምትን ማስፋፋት ነዉ። የመሬት ቅርምትን በሚመለከት የተሠራዉ ዋነኛ ጥናትም biofuel ለመሬት ቅርምት ዋና ምክንያት እንደሆነ አመልክቷል።»

Biofuel watch ተባባሪ ዳይሬክተር እንደሚሉትም የመሬት ቅርምትን የሚመለከት ጥናት ይፋ ባደረገዉ መሠረት እህል ለማምረት በሚል በባለሃብቶች የሚያዙ ሰፋፊ መሬቶች አላማቸዉ የምግብ እህል አምርቶ ባለመሬቱን ህዝብ ማቅረብ መመገብ ባለመሆኑ ይመሳሰላሉ ነዉ የሚሉት፤

«በዚህ ረገድ መሬት የምግብ እህል ለማምረትም ይያዝ ወይም ጃትሮፋ፤ ጉሎና መሰል ለነዳጅ የሚሆኑ ተክሎችን ለማልማት ግቡ አይለያይም፤ ያዉ የመሬት ቅርምት ነዉ። በተለይ ይህን ለማሳየት አክሽን ኤድ meals per gallon በሚል ርዕስ ያዘጋጀዉ ሰፊ ጥናት ምሳሌ በማቅረብ በዚህ ምክንያት የተለያዩ ማኅበረሰቦች ለምግብ እህል ማምረቻ የሚሆን መሬት እንዳጡ፤ ምግብ እንዳጡ ይህም በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ለጉዳት እንደዳረጋቸዉ ያሳያል። ምክንያቱም መሬታቸዉ ጃትሮፋን ጨምሮ የተለያዩ ለBiofuel ግብዓት ይሆናሉ የሚባሉ ተክሎችን ለማልማት ተወስዷልና።»

Ölpalmenplantage

ኢትዮጵያ ዉስጥ ከተረፈ ምርት ብሎም ከተክል የሚገኝ ነዳጅ ስለማምረት መነገር ከጀመረ ዉሎ አድሯል። ከመነሻዉ በስኳር ምርት ሂደት ከሸንኮራ አገዳ የሚገኘዉን ተረፈ ምርት ከቤንዚን ጋ ቀላቅሎ መጠቀም መጀመሩ ሀገሪቱ ከዚህ በፊት ይህን ተረፈ ምርት ለሌላ ሀገር እየላከች በተቃራኒዉ ራሷ ለከፍተኛ ወጪ የተዳረገችበትን ሁኔታ ያስቀራል በሚል ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወገኖች አወድሰዉታል። በተቃራኒዉ የምግብ እጥረት ደጋግሞ በሚከሰትባት ሀገር ለምግብ እህል ማምረቻ የሚበጅን መሬት ጃትሮፋ፤ ጉሎና የመሳሰሉትን ነዳጅን ለማስገኘት ይችላሉ ለሚባሉ ተክሎች ያለጥናት መስጠት ተገቢ እንዳልሆነ የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክን ጨምሮ ጉዳዩን የሚከታተሉ ወገኖች እርምት እንዲወሰድ ሲያሳስቡ ተደምጧል።

የአካባቢ ተቆርቋሪዎች መድረክ ያወጣዉ ጥናት እንደሚያሳየዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለነዳጅ የሚዉል ተክልን ማለትም Biofuelን ለማልማት 83 ተቋማት ተመዝግበዋል። ሆኖም  በአሁኑ ወቅት ወደ13 ገደማ የሚሆኑት ተግባራዊ ሥራ መጀመራቸዉን እንደሚታወቅ ይኸዉ ጥናት ጠቅሷል። ቀደም ሲል ይኸዉ ተቋም ባለወጣዉ ጥናት ጃትሮፋና መሠል ተክሎችን ለዚሁ ሲባል ለማልማት ከእርሻ መሬቶች በተጨማሪ የዱር እንስሶች የሚገኙባቸዉ በብሄራዊ ፓርክነት የተከለሉ ቦታዎች ሳይቀሩ አደጋ አንዣቦባቸዉ ታይተዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic