አቶ ጃዋርን ጨምሮ በሽብርተኝነት ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ዉሎ  | ኢትዮጵያ | DW | 21.09.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አቶ ጃዋርን ጨምሮ በሽብርተኝነት ተጠርጣሪዎች የፍርድ ቤት ዉሎ 

አቶ ጃዋር መሃመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሃምዛ አዳነ እና ሌሎችም በክስ መዝገቡ የተያዙት 18 ሰዎች ዛሬ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ ጃዋርን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙና ከሃገር ውጭ በሚገኙ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብርተኝነትና ሎሎች በርካታ ክስ መስርቻለሁ ማለቱ ይታወቃል፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:11

ፖሊስ ለቀጣይ ሃሙስ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ቀጠሮ ተሰጥቶአል


እነ አቶ ጃዋር መሃመድ ለፍርድ ቤት ቀረቡ፡፡ አቶ ጃዋር መሃመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሃምዛ አዳነ እና ሌሎችም በክስ መዝገቡ የተያዙት 18 ሰዎች ዛሬ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት ቀርበዋል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ባለፈው እለተ ቅዳሜ አቶ ጃዋርን ጨምሮ በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙና ከሃገር ውጭ በሚገኙ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብርተኝነትና ሎሎች በርካታ ክስ መስርቻለሁ ማለቱ ይታወቃል፡፡ በዚሁ መሰረት ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በዋለው ችሎት ላይ የቀረቡት ተጠርጣሪዎች ለእለቱ ችሎት በሰጡት ቃላቸው ወንጀሉን እንዳልፈጸሙ በመግለፅ የታሰሩትም በፖለቲከዊ ምክኒያት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች እንደሚሉት በመንግስት ቁጥጥር ስር ለሚገኙ ተከሳሾች ስለተከፈተባቸው ክስ ምንነት ዛሬ ጠዋት ለፍርድ ቤት እስከቀረቡበት ጊዜ ድረስ በእጃቸው የደረሰ የክሱ ዝርዝር ጉዳይ አልተገለጸም፡፡ ዐቃቤ ህግ ክስ ከመመስረቱ አስቀድሞ የክሱን ዝርዝር ጭምር ለተጠርጣሪዎች ማድረስ ነበረበት የሚሉት ጠበቃ ቱሊ ባይሳ ቻርቹ ጠበቆችንም ሆነ ተጠርጣሪዎችን የደረሰው ገና ዛሬ ችሎት ላይ ነው ብለዋል፡፡
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የህግ መመህር የሆኑት ደጀን የማነህ በበኩላቸው ጠቅላይ አቃቤ ህግ ቅዳሜ እለት የክስ ምስረታውን በሰበር ዜናነት የመውጣቱን ሂደት ተችተውታል፡፡ የክስ ምስረታው የአቃቤ ህጉ የዕለት ተዕለት ስራ ነው ያሉት መመህር ደጀን ከዚያም አስቀድሞ የክስ ቻርጁ በተጠርጣሪዎች እጅ ላይ ደርሶ በጉዳዩ ላይ ከጠበቆቻቸው ጋር የመወያየት መብት ነበራቸው ነው የሚሉት፡፡ ከሃገር ውስጥ ያልቀረቡ 2 ተጠርጣሪዎች በአካል እንዲቀርቡና በውጭ ሃገር የሚገኙ ተጠርጣሪዎችን በተመለከተ ደግሞ ፖሊስ ለቀጣይ ሃሙስ ለተያዘው ቀጠሮ ቀርቦ መልስ እንዲሰጥ ፍርድ ቤቱ በማዘዝ ነው የዛሬ የችሎት ውሎ የተጠናቀቀው፡፡

ስዩም ጌቱ 


አዜብ ታደሰ 
እሸቴ በቀለ 
 

Audios and videos on the topic