አቶ ክፍሌ-የአፕሉ ገበሬ  | ኤኮኖሚ | DW | 09.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

 አቶ ክፍሌ-የአፕሉ ገበሬ 

ቱፋህ፤ ፖም ወይም አፕል በበርካታ አገሮች ተወዳጅ ይሁን እንጂ ዛሬም ድረስ በኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደ ቅንጦት ይታያል። አዲስ አበባ ላይ አንድ ኪሎ ከ75-90 ብር ይሸጣል።  በደጋማ አካባቢዎች ለሚኖሩ ገበሬዎች አማራጭ የገቢ ምንጭ ይሆናል የሚል እምነት ያላቸው የግብርና ባለሙያዎች አፕልን በኢትዮጵያ ለማስተዋወቅ ሲጥሩ ይታያል። 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:59
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
10:59 ደቂቃ

አቶ ክፍሌ በሱሉልታ የአፕል ችግኝ እያራቡ ያከፋፍላሉ

በኢትዮጵያ ቀድማ ከአፕል የተዋወቀችው የጋሞ ጎፋዋ ጨንቻ ነበረች። የመጀመሪያዎቹ የአፕል ዛፎች በጨንቻ የቃለ-ሕይወት ቤተ-ክርስቲያን ግቢ የተተከሉት ከስድሳ አመታት ገደማ በፊት ነበር።በሌሎች የአፍሪቃ አገራት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ብሎም ኑሮን ለመደጎም ሁነኛ መፍትሔ ሆኖ የሚመረተው አፕል ታዲያ የኢትዮጵያ ምርቱ የተገደበ ነው። ዛሬም አንድ ኪሎ ከ75-90 ብር እየተሸጠ የቅንጦት ምልክት ሲሆን ይታያል። ዓለም አቀፍ የርዳታ ድርጅቶች እና የግብርና ባለሙያዎች ግን  በኢትዮጵያ ደጋማ አካባቢዎች ለበርካታ መቶ አመታት እህል እና ጥራጥሬ ብቻ ሲያመርት ለኖረው ገበሬ አማራጭ ገቢ መደጎሚያ ሊሆን እንደሚችል እምነታቸው ነው። ከእነዚህ መካከል አቶ ክፍሌ ቡሎ አንዱ ናቸው።

"አንዱ በተለይ በደጋማ አካባቢ ላይ የሚኖረው የኢትዮጵያ ገበሬ እንደ ቆላማ ወይንም ዝቅተኛ አካባቢ አርሶ አደር የሰፋ የፍራፍሬ አማራጭ የለውም። በሌላ አንጻር ደጋማው አካባቢ ለአፕል እምቅ የሆነ አቅም አለው። እርጥበት አለ። አፈሩ ምቹ ነው። ገበሬው መኖሪያው አካባቢ ላይ አስር እግር ቢተክል ለዛ የሚሆነው ፍግ በቀላሉ ያገኛል። ለእንክብካቤ ቤተሰቡን ቢያሰማራ በቂ የሆነ ጉልበት ይኖራል። ስለዚህ በዚህ ምቹ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የደጋውን አርሶ አደር በፍራፍሬ ላይ ብናሳትፈው እና ይኸንን አማራጭ ብናቀርብለት እንዲሁም ኤኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ከሌላ ጋር ብናነፃፅረው ከፍተኛ የሆነ ፋይዳ አለው። አንድ እግር ዛፍ ቢተከል ከ30-50 ኪ.ግ. ፍሬ ሊሰጥ ስለሚችል አዋጪ ነው።"

የቀድሞው የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፋንታሁን መንግሥቱም አፕል ለኢትዮጵያ ገበሬዎች የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ እንደሆነ ይስማማሉ። በአሁኑ ወቅት በተቋሙ በተመራማሪነት የሚያገለግሉት ዶ/ር ፋንታሁን የአገሪቱ የአየር ጠባይ አመቺ መሆን ተጨማሪ እድል እንደሆነ ይናገራሉ።

"የአፕልን ምርት የሚወስነው የቅዝቃዜ መጠን ነው። ኢትዮጵያ አፍሪቃ ውስጥ ካሉ አገራት በተለይ ተለዋጭ የአየር ጠባይ ስላላት እጅግም ቀዝቃዛ እጅግም ሞቃት ያልሆነ አማካኝ የሙቀት መጠን ይገኝባታል። ስለዚህ ደጋማው አካባቢ በአጠቃላይ ለበርካታ የአፕል ዝርያዎች አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል። በአንድ በኩል የአየር ጠባዩ አመቺ ነው። ሁለተኛ በደጋማ አካባቢ የሚኖረው አርሶ አደር የምርት አይነቱ ጠባብ ስለሆነ ቋሚ የሆነ አትክልት እና ፍራፍሬ ከሌላው ሰብል ጋር አጣምሮ ቢያመርት በጣም ጠቃሚ ይሆናል።"

ከአዲስ አበባ 18 ኪ.ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው የሱሉልታ ከተማ አቶ ክፍሌ ቡሎ የአፕል ችግኝ እያራቡ ለገበሬዎች ያከፋፍላሉ። አቶ ክፍሌ የደን ሳይንስ እና የልማት አስተዳደር የሰለጠኑ ባለሙያ ናቸው። ባለሙያው በአፕል ፍቅር ወድቀው ከኢትዮጵያ ገበሬ ጋር ሊያስተዋውቁት ደፋ ቀና ሲሉ 20 አመታት አስቆጥረዋል። 

"አፕል የደጋ ፍራፍሬ ነው። በተለምዶ ደጋማ ወይም ቀዝቃዛማ በምንለው የአየር ንብረት ውስጥ ተተክሎ ፍሬ መስጠት የሚችል ነው። ይኸ ዛፍ የራሱ የሆነ የስር ክፍል አለው። የራሱ የሆነ ፍሬ ሰጪ ክፍል አለው። እነዚህን ሁለቱን ክፍሎች በከተባ ወይም በማዳቀል ዘዴ በማገናኘት ችግኙ ይዘጋጃል። ለተከላ የሚደርሰው ችግኝ 3 አመት ይወስዳል። በዚህ ደረጃ የተዘጋጀው የአፕል ችግኝ በአግባቡ ከተተከለ እና አስፈላጊው እንክብካቤ ከተደረገለት በደንብ ፍሬ ሊሰጥ ይችላል።"

ከባህር ጠለል በላይ ከ1, 800 እስከ 3, 000 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኙ ደጋማ አካባቢዎች አፕል ለማምረት ምቹ ናቸው። መነሻው ከወደ አውሮጳ እና የእስያ አገራት ነው።  አንድ የአፕል ዛፍ እንደ እፍጋቱ መጠን* (density) ከ40-200 ኪ.ግ. ምርት ይሰጣል። የአፕል ገበሬዎች ይኸንን የፍራፍሬ ዝርያ ለኑሮ መደጎሚያ ፤ ለንጥረ-ምግብ ይዘቱ (ቫይታሚን ሲ) እንዲሁም የአፈር መከላትን ለመከላከል ይተክሉታል። 


"የተለያዩ የአፕል ዝርያዎች አሉ። ሁሉም በአንድ ከፍታ ላይ የሚበቅሉ አይደሉም። እንደየዝርያቸው የተለያየ ከፍታ ይፈልጋሉ። በተለይ ቀይ መሬት ቀይ አፈር ለአፕል ምቹ ነው። ውሐ የማይተኛበት ረግረጋማ ያልሆነ ቦታ ለአፕል ልማት ምቹ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አፕል በተለይ መካከለኛው ደጋማ አካባቢዎች ላይ ለአፕል ፍላጎተ ቅዝቃዜያቸው (chilling requirement)  አነስተኛ የሆኑ የአፕል ዝርያዎች መካከለኛ የአገሪቱ ደጋማ አካባቢ ላይ መብቀል ይችላሉ። ፍላጎተ ቅዝቃዜያቸው (chilling requirement)  ከፍተኛ የሆነ ወይም መካከለኛ ላይ ያሉት እርጥብ ደጋ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ተተክለው ውጤታማ ሊያደርጉ ይችላሉ። በተለይ ሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ለአፕል ምቹ የሆነ አካባቢ ነው። አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉትም ደጋማ አካባቢዎች ምቹ ናቸው።"

አቶ ክፍሌ "የኢትዮጵያ አርሶ አደር በአፕል መለወጥ ይችላል" የሚል እምነት አላቸው። በስማቸው ባቋቋሙት ኩባንያቸው የአፕል ችግኝ እያራቡ ለገበሬዎች ይሸጣሉ። ደንበኞቻቸውንም ያሰለጥናሉ። 

"መጀመሪያ የችግኙን እድሜ ማየት ያስፈልጋል። ስሩን አባዝቶ ለማዳቀል እስከ አንድ አመት ይፈጅብናል። ከተዳቀለ በኋላ እና ለተከላ እስኪወጣ ድረስ የተባዛው ሥር መሰረት ይዞ ጠንክሮ እስኪዳቀል ሌላ ተጨማሪ ስምንት ወራቶችን ይፈልጋል። ከዛ በኋላ የማዳቀል ሥራው ይሰራ እና ለአንድ አመት ይቆያል። ለሶስት አመት በችግኝ ጣቢያችን ይቆያል። ይኸ የሶስት አመት እድሜ ያለው ችግኝ ገበሬ ጋ ሔዶ ከተተከለ ከሁለት አመት በኋላ ፍሬ መስጠት ይጀምራል።"

ከ2000 ዓ.ም. ጀምሮ አፕልን ለገበሬዎች ለማስተዋወቅ ችግኝ አራብቶም ለማከፋፈል ደፋ ቀና የሚሉት አቶ ክፍሌ በመጀመሪያዎቹ አመታት ሙከራዎቻቸው በገንዘብ እጦት መሰናክል ገጥሞት ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥት እና የዓለም ባንክ ለሥራ ፈጣሪዎች ያቀረቡት የውድድር እድል ግን በር ከፈተ። "የአፕል ችግኝ አዘጋጅቼ፤የገበሬውን እውቀት አሳድጌ ለአርሶ አደሮች ማከፋፈል አቅጃለሁ" የሚል እቅድ ይዘው የቀረቡት አቶ ክፍሌ አሸናፊ ሆኑ። በአሸናፊነታቸው ሥራቸውን የሚከውኑበት 15,000 ዶላርም ከእጃቸው ገባ። 

Kifle Bulo Apfel Sämling Produzent (privat)

አቶ ክፍሌ ቡሎ በሱሉልታ የአፕል ችግኝ ማራቢያቸው ውስጥ

"የአፕል ችግኙን አዘጋጅቼ የገበሬውን እውቀት አሳድጌ ቢያንስ በሱሉልታ አካባቢ ላሉት አርሶ አደሮች ከዛም አልፎ በተለይ በኦሮሚያ አካባቢ ላሉት አርሶ አደሮች ችግኙንና እውቀቱን በማጣመር ብናስፋፋ  ጥቅም እንሰጣለን በሚል የሥራ እቅዴን አቅርቤ የ15,000 ዶላር ተሸላሚ ሆኜ ነው ሥራውን የጀመርኩት። ሥራውን ስጀምር ከዓለም ባንክ እና ከኢትዮጵያ መንግሥት ይኸንን ሽልማት ላግኝ እንጂ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት 'ይኼ የሚበረታታ ሥራ ነው። ለአርሶ አደሩ የሚጠቅም ሥራ ነው። ስለዚህ ግፋበት' ብለው አንድ ሔክታር መሬት ከሊዝ ነፃ ሰጥቶኝ የአፕል ችግኝ ሥራውን እና የእውቀት ሽግግሩን በመስራት ላይ እገኛለሁ"

አቶ ክፍሌ እንደሚናገሩት የአፕልን ሥር አባዝቶ ለማዳቀል እስከ አንድ አመት ይወስዳል። የተባዛው ሥር መሰረት ይዞ ጠንክሮ እስኪዳቀል ሌላ ስምንት ወራት ይፈጃል።  ከዚያ የማዳቀል ሥራው ተሰርቶ ለአንድ አመት ይቆያል። በአጠቃላይ አንድ የአፕል ችግኝ ተዳቅሎ ከገበሬው እጅ ከመግባቱ በፊት ሶስት አመት ገደማ በጣቢያው ይቆያል። ይኸ ችግኝ ወደ ገበሬው ደርሶ ከተተከለ ከሁለት አመት በኋላ ፍሬ መስጠት ይጀምራል።

"ለገበሬ ምቹ የሆኑትን የአፕል ዝርያዎች በማዳቀል ለገበሬ እናቀርባለን። ከዛ ባለፈ እገዛ ማድረግ በምንችልበት ቦታ ላይ ወደ ገበሬ አካባቢ ላይ ሔደን የገረዛ ሥራ፤ የቦታ አመራረጥ ሥራ የዛፍ አተካከል ሥራ ተግባራዊ የሆነ ምክር በማሳቸው ላይ ለአርሶ አደሮች የምንሰጠው ይኖራል። ስለ አፕል ተከላ ቦታ አመራረጥ፤አተካከል እና ስለ አያያዝ እንዲሁም የፍሬ አመራረት ላይ ስልጠና እንሰጣለን። በሽያጭ ነው ችግኞቻችንን ለገበሬው የምናሳራጨው። እስካሁን ባለን መረጃ ከ4,000 በላይ ችግኞች ከእኛ ተሰራጭ ተዋል።"

ገብስ እና ስንዴ አምራቹ የሱሉልታ ገበሬ አቶ አበበ ቶላ በማሳቸው 20 የአፕል ዛፎች አሏቸው። ከዚህ ቀደም ከጨንቻ ያመጧቸው የፕል ችግኞች እንዳቀዱት ውጤታማ አልሆኑላቸውም። የኋላ ኋላ ከአቶ ክፍሌ የችግኝ ማራቢያ የወሰዷቸውን የአፕል ዛፎች ግን ወደዋቸዋል።  በአምስት አመታት ውስጥ ሶስት ጊዜ ምርት የሰበሰቡት አቶ አበበ ገበያ አውጥተው ባይሸጡትም ልጆቻቸው እና ቤተሰቦቻቸው ግን ወደውታል።
"መጀመሪያ ከውጪ ሲመጣ የወሰድኩት በጣም አሪፍ ነው። ፍሬም አለው ቀለሙም ያምራል። መጀመሪያ አስር ወሰድኩ። ከዚያ ደግሞ 10 ጨመርኩ። በአጠቃላይ 20 አፕሎች አሉ። አምስት አመት ሆኖታል። ሶስት ጊዜ ነው {ምርት} የሰበሰብኩት። ስንት ኪሎ እንደሆነ አልመዘንውም። በጣም ምርጥ ነው።"

የሱሉልታው ነዋሪ አቶ ከበደ አረዶ በመኖሪያ ግቢያቸው ካሏቸው ሰባት የአፕል ዛፎች ከእያንዳንዳቸው እስከ 31 ኪሎ ምርት ሰብስበው ያውቃሉ። 

"ክፍሌ ጥሩ ነገር ነው እየሰራ ያለው። እኔ ግቢ ውስጥ ተክያለሁ። ሰባት እግር ነው ያለኝ አሁን። የመጀመሪያው አራቱ በዚህ በክረምት አምስት አመት ይሆናቸዋል። ቀጣዮቹ ሶስቱ ደግሞ ሶስት አመታቸው ነው። እንክብካቤ በጣም ይፈልጋል። ክትትል ከተደረገ እጅግ በጣም ቆንጆ ምርት ነው የሚሰጠው። በመጀመሪያ ዓመት ማፍራት እንደጀመረ ትርፍ ምርት ሰጥቶኝ ነበረ። በሁለተኛ ዓመት ላይ ከአንድ እግር እስከ 31 ኪሎ ድረስ ነው የለቀምኩኝ። በዚህ ዓመት ከአንድ እግር ከ35-40 ኪሎ አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ።"

"ዘመደ ብዙ ነኝ" የሚሉት አቶ ከበደም ምርታቸውን ወደ ገበያ አላወጡትም። ወደ ቤታቸው ጎራ ያሉ ሁሉ አቶ ከበደ እና ቤተሰቦቻቸው ባቀረቡላቸው አፕል ተገርመዋል። "እኛ ጋ ሲመጣ ያልቀመሰ እንግዳ የለም" ይላሉ የሱሉልታው ነዋሪ። 


"ከፒያሳ ገዝቼ ከውጪ ከሚመጣው ጋር አወዳደርኩት።  በጣም በተሻለ ሁኔታ ነው ሊሆን የሚችለው። ግን እንክብካቤ ይፈልጋል። 31 ኪሎ ከአንድ እግር ላይ ለቅሜ ብሸጠው ኖሮ {አንዱን ኪሎ} 50 ብር እንኳ ብታስበው ምን ያህል ብር ነው ሊመጣ የሚችለው? ከኑሮ መደጎሚያነትም አልፎ ቢዝነስ ሊሆን የሚችል ነገር ነው።"

የአፕል አመራረት በአገሪቱ ኋላ ቀር በመሆኑ ሁሉም ደንበኞቻቸው ስኬታማ ሆነዋል ብሎ መናገር ይቸግረኛል ያሉት አቶ ክፍሌ ምርት ሰብስበው ለገበያ ያቀረቡ መኖራቸውን ግን አልሸሸጉም። በገበሬዎችም ይሁን ዘንድ በቂ እውቀት አለመኖሩ እክል እንደሆነባቸው ተናግረዋል። የግብርና ተመራማሪው ዶ/ር ፋንታሁን መንግሥቱ ግን የትኞቹ የአፕል ዝርያዎች ለየትኛው የአየር ጠባይ ይስማማሉ የሚለው ጉዳይ በአግባቡ አለመለየቱ ተጨማሪ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

"አፕል ከገባ ረጅም ጊዜው ነው። እስካሁን ግን ምርጥ የሚባል፤ጥሩ ጥራት ያለው የአውሮጳ አገራት እንደሚያመርቱት ያለ ጥሩ የሆነ የአፕል ዝርያ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ካልሆነ በስተቀር በጥሩ ሁኔታ እያመረትንው አይደለም። ዋናው ችግር ከውጭ የምናስገባቸው የአፕል ዝርያዎች ለየትኛው አካባቢ ነው የሚስማሙት የሚለውን ነገር በደንብ አልሰራንውም። ጨንቻ ላይ አንድ ጊዜ ቃለ-ሕይወት ያመጣው ነው መነሻ እየሆነ ያለው። ዝርያውም ድብልቅልቅ ነው። ስለዚህ ተመሳሳይ ዝርያ በመላ አገሪቱ ደጋማ አካቢዎች ላይ የመውሰድ አዝማሚያ ነው ያለው። ያ ደግሞ አይሰራም።"

ለአቶ ክፍሌ የአንድ የአፕል ችግኝ ዋጋ መወደድ ሌላው የሚያሳስባቸው ጉዳይ ነው። ለገበሬ አነስተኛ ቅናሽ እናደርጋለን የሚሉት አቶ ክፍሌ የዋጋውን ነገር የሚመለከታቸው ሁሉ መላ ሊፈይዱለት ይገባል ባይ ናቸው። 

"ውድ ነው አፕልን ማዘጋጀት። ለአንድ አርሶ አደር {አንድ ችግኝ} እስከ መቶ ብር ድረስ ነው የምንሸጠው። ይኼ ገበሬ እስከ መቶ ብር ድረስ አውጥቶ የመግዛት አቅሙ በጣም ይከብደዋል። ሶስት አመት ችግኙ ከእኛ ጋር ስለሚቆይ ከፍተኛ ወጪ ነው የምናወጣበት እና በዚህ ዙሪያ ያሉት ነገሮች ናቸው ለስራው ፈታኝ የሚሆኑብን።"
 

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic