አቶ አባዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አረጋገጡ | ኢትዮጵያ | DW | 08.10.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አቶ አባዱላ ገመዳ የሥራ መልቀቂያ ማስገባታቸውን አረጋገጡ

አፈ-ጉባኤው የሥራ መልቀቂያውን ያስገቡት "በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ምክንያቶች በመኖራቸው እና ፍላጎቱም ስለሌለኝ" ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ የሥልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ማቅረባቸውን በይፋ አረጋገጡ። አፈ-ጉባኤው ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ "አሁን በደረስኩበት ደረጃ በዚህ ኃላፊነት ለመቀጠል የማያስችሉኝ ምክንያቶች በመኖራቸው እና ፍላጎቱም ስለሌለኝ ለመልቀቅ ድርጅቴን እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ጠይቄያለሁ" ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ አባዱላ ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሱት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከወከሉት እና የኢሕአዴግ አባል ከሆነው ፓርቲያቸው ጋር ተማክረው ይሁን አይሁን ግን በግልፅ ያሉት ነገር የለም። 

አቶ አባዱላ ከአፈ-ጉባኤነት ኃላፊነታቸው ለመልቀቅ የወሰኑባቸውን ምክንያቶች በግልፅ አልተናገሩም። "ድርጅቴ እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁኔታውን አይተው ሕጋዊ መስመሩን ተከትለው ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ያገኛል" ያሉት አቶ አባዱላ "ጥያቄዬ ተገቢውን ምላሽ ሲያገኝ የምክር ቤት አፈ-ጉባኤነቴን ለመልቀቅ የፈለኩባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር ለሕዝብ አስረዳለሁ" ሲሉም አክለዋል። 

አፈ-ጉባኤው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ ማስገባታቸውን አዲስ ስታንዳርድ የተባለው የድረ-ገፅ መፅሄት እና ሪፖርተር ጋዜጣ ቅዳሜ መስከረም 27 ቀን 2010 ዓ.ም. በተከታታይ ዘግበው ነበር። ሪፖርተር ጋዜጣ እንደ ዘገበው አቶ አባዱላ ያቀረቡት የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤ "ለፓርላማው ምልዓተ-ጉባዔ ይቀርብና" ገዢው ግንባር ተተኪያቸውን እጩ አቅርቦ ያሾማል።

አዲስ ስታንዳርድ በበኩሉ፦ አፈ-ጉባኤው የሥራ መልቀቂያ ደብዳቤያቸውን ያስገቡት "የፌዴራል የጸጥታ ተቋማት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የተከሰተውን ኹከት የያዙበትን መንገድ ጨምሮ የቅርብ ጊዜያት ፖለቲካዊ ኩነቶችን በመቃወም ነው" ሲል አትቷል። 

የኦሮሚያ እና የሶማሌ ክልሎች በሚዋሰኑባቸው አካባቢዎች በተነሳ ግጭት በርካታ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው ተፈናቅለዋል። በሁለቱ ክልሎች ባለሥልጣናት መካከል መወራረፍ እና መወነጃጀልም ተስተውሏል። ባለፈው ሳምንት የኢትዮጵያ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ከሶማሌ ከ75 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ዜጎች ከኦሮሚያ ደግሞ 392 ዜጎች መፈናቀላቸውን ከሁለቱ ክልሎች ሪፖርት ደርሶናል ሲሉ ተናግረው ነበር። 

ዛሬ በብሔራዊው እና ክልላዊ የቴሌቭዥን ጣቢያዎች በተላለፈው ጋዜጣዊ መግለጫ "ጥያቄዬ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤነት የመልቀቅ ቢሆንም የመረጠኝን ሕዝብ እና ያስመረጠኝን ድርጅት ስለማከብር በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነት እቀጥላለሁ" ያሉት አቶ አባዱላ "ለሕዝብ ይጠቅማሉ በምላቸው ሥራዎች ባለኝ ጊዜ ተሰማርቼ የማገለግል ይሆናል" ሲሉም አክለዋል። 

አቶ አባዱላ ገመዳ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው የተመረጡት ከሰባት ዓመታት በፊት ነበር። ገዢው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር ከሁለት ዓመት በፊት የተካሔደውን ምርጫ መቶ በመቶ ማሸነፉ ከተገለጠ በኋላ ጠቅላይ ምኒሥትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ መስከረም 24 ቀን  2008 ዓ.ም. ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ አቶ አባዱላ በያዙት ሥልጣን ቀጥለዋል። አቶ አባዱላ ገመዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት በመከላከያ ሚኒሥትርነት እና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ-መሥተዳድርነት ያገለገሉ ጉምቱ ፖለቲከኛ ናቸው። 

አቶ አባዱላ ገመዳ በአፈ-ጉባኤነት የሚመሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነገ መስከረም 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ሥራቸውን ይጀምራሉ። 

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ