አቶ ታዬ ደንደዓ ከተመሰረተባቸው ሦስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ተባሉ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30 2016አቶ ታዬ ደንደዓ ከተመሰረተባቸው ሦስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ተባሉ
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደዓ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሁሴን በፍርድ ቤት ተጠርተው እንድጠየቁልኝ ሲሉ አመለከቱ፡፡ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ያስቻለው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 1ኛ የሕገመንግስትና ሕገ-መንግስት ስርዓት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ላይ ያለ ጠበቃ የቀረቡት አቶ ታዬ የጥብቅና መብት ለመከልከላቸው ብሔራዊ መረጃ ደህንነትን ከሰዋል፡፡ በመሆኑም ተቋሙን የሚመሩትና ተቋሙ በቀጥታ ለጠቅላ ሚኒስትሩ ተጠሪ እንደመሆኑ ተነፈግኩ ላሉት ህገመንግስታዊ መብት ፍርድ ቤቱ እንዲጠይቅላቸው ተማጽነዋል፡፡ ዛሬ በልደታ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያስቻለው ችሎቱ አቶ ታዬ ከተከሰሱበት ሶስት ክሶች በሁለቱ ነጻ ስላቸው አንዱን ግን እንዲከላከሉ በይኗል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ እና የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ጨፌ ኦሮሚያ አባል የነበሩት አቶ ታዬ ደንደዓ ዛሬም ፍርድ ቤት ቀርበው የተመሰረተባቸው ክስ ብይን ስሰሙ ምንም ጠበቃ አብሯቸው አልቀረበም፡፡ ጠበቆቻቸው ባልቆሙበት ዛሬ በተመሰረተባቸው ሶስት ክሶች ላይ በፍርድ ቤቱ የተነበበላቸው ብይን በሁለቱ ክሶች ነጻ ብሎአቸዋል፡፡
ነጻ የተባሉበት የክስ ጭብጦች
የፍትህ ሚኒስቴር የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ጉዳዮች ዳይሪክቶሬት ዐቃቤ ሕግ በተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደአ ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 251/ሐ እና አንቀጽ 257/ሰ ስር የተመላከተውን ድንጋጌ በመተላለፍ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው ሲሰሩ የሀገርን፣ የመንግስት እና የህዝብን ደህንነት ማስጠበቅ፣ ማረጋገጥ ሲገባቸው ይህን ወደጎን በመተው፤ በአንድኝነት ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎችን አሰራጭተዋል፤ በሁለተኛም ከመንግስት ጋር ጦርነት ውስጥ የገቡትን የ“ኦነግ ሸነ እና ፋኖ” ዓላማን ለማሳካት በስማቸው በተከፈተ ማህበራዊ ሚዲያና ሌሎችም መሰል ይዘት ያለው መልእክቶችን አስተጋብተዋል የሚሉ ክሶች ከቀረበባቸው የክስ ጭብጦች ናቸው፡፡
እነዚህም ሁለት ክሶች በማስመልከት አቶ ታዬ በተለያዩ ጊዜያት በግል ማህበራዊ ገጻቸው ጽፈው ያሰራጩትን እና ህዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም. በቢቢሲ አፋን ኦሮሞ በኩል የተሰራጨው የግል ምልከታቸው ላይ የተላለፉ መልእክቶችን በጥልቀት ዘርዝሮ መመልከቱን ያተተው ችሎቱ፤ በነዚህ ጊዜያት በጽሁፎቻቸው መንግስት “ከኦነግ ሸነ” ጋር ያደረገው ግጭት የማቆም ውይይቶች በመንግስት መደናቀፉን ገልጸው የተቹበትና ህዳር 30 ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቀው ሰልፍ እንዳይካሄድ መታገዱ “የሰላም ጸር” ነው የሚል የግል ምልከታቸውን አንስተው መሞገታቸውን አስታውሷል፡፡
ተከሳሽ እነዚህን ተግባራት መፈጸማቸውን ነገር ግን ድርጊቶቹ ወንጀል አለመሆናቸው አምነው መከራከራቸውም በችሎቱ ተጠቁሟል፡፡ በመሰል ጽሁፎቻቸው ወንጀል ፈጽመዋል በሚል የቀረበባቸውን ክስ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መስመርን የጣሰ እንደሆነ በችሎቱ በጥልቅ መታየቱን የገለጸው ፍርድ ቤቱ ከተከሰሱበት አንቀጽም አንጻር ሃሳባቸው ከአገር ሉዓላዊነት ማስደፈርም ሆነ ከህዝብ ሞራል ጋር የማይጋጭ በመሆኑ እነዚህን ሁለት ክሶች መከላከል ሳይጠበቅባቸው በነጻ ተሰናብተዋል ሲል በይኗል፡፡
“የህገወጥ ጦር መሳሪያ” አያያዝ ክስ
ተከሳሹ ፍቃድ ሳይኖራቸው በህገወጥ መንገድ የተያዘ የተባለው የጦር መሳሪያ አዋጁን በመተላለፍ በታኅሣስ 1 ቀን 2016 ዓ.ም በልደታ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በሚገኝ መኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በተደረገ ብርበራ አንድ ታጣፊ ክላሽንኮቭ ከሁለት የክላሽንኮቭ ካዝና ከ60 ጥይት ጋር ተይዞባቸዋል በሚል የቀረበባቸውን ሶስተኛ ክስ ግን እንዲከላከሉ ተበይኗል። ለዚህም መከላከያ ምስክር እንዲያቀርቡ የተጠየቁት ተከሳሽ አቶ ታዬ ደንደዓ መከላከያ ምስክሮቹን ለማቅረብእንደማይቸገሩ፤ ነገር ግን ለዛሬ የተዘጋጀ መከላከያ ምስክር አለመኖሩን ለችሎቱ መልሰዋል፡፡ በዚሁ ላይ አክለው ግን በዋናነት በተከሰሱበት አንደኛ እና ሁለተኛ ክሶች ነጻ በመባላቸው የዋስትና መብታው እንዲጠበቅላቸው አቤት ብለዋል፡፡ አቃቤ ህግ ግን የተመሰረተባቸው ሶስተኛ ክስም ህጋዊ እልባት እስኪያገኝ ድረስ የዋስትናው ጥያቄ ይቆይ ሲል የተከሳሹን ጥያቄ ተቃውሟል፡፡
የተከሳሹ አቤቱታ
“አቃቤ ህግ ለህግ ነው መወገን ያለበት” በሚል ተቃውሟቸውን የገለጹት ተከሳሹ አቶ ታዬ ደንደዓ ግን “እኔ የህዝብ ተወካይ ነኝ፤ በሰልም ሚኒስትር ዴኤታነት ሃላፊነቴም ሰባት ጥበቃዎች ስቆሙልኝ የነበረ እውነት ሆኖ ሳለ አንድ ክላሽ ይዘህ ተገኝተሃል ተብዬ ልከሰስም ባልተገባ ነበር” ሲሉ ሞግተው ዋስትናው ተጠብቆላቸው “በችግር ላይ ያሉ” ላሏቸው ቤተሰቦቹ በመድረስ ቀሪውን የክስ ጭብጥ ከውጪ ተመላልሰው ለመከራከር እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል፡፡ ተከሳሹ አቶ ታዬ ከዋስትና መብት ጋር ተያይዞ ባቀረቡት አቤቱታም “በህገመንግስቱ አንቀጽ 20 መሰረት ተከሳሽ ያሻውን ጠበቃ የማቆም መብት ብደነገግም፤ ጠበቃ እንዳይቆምልኝ፤ የቆሙልኝንም በማስፈራራት ብሔራዊ መረጃ ደህንነት በነጻነት ላይ ወንጀል ፈጽሟል” በማለት የጥብቅና መብት ያለአግባብ መከልከላቸውን ለችሎት ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ተቋሙን የሚመሩት ኃላፊ፤ እንዲሁም ተቋሙ ቀጥታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተጠሪ እንደመሆኑ ፍርድ ቤት ጠርቶ ማብራሪያ እንዲጠይቃቸው ሲሉ በቃል አመልክተዋል፡፡
የቀድሞ የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ከአንድ ወር በፊት ለችሎት ቀርበው እንዳስረዱት “አቃቤህግ እና ሰዎቻቸው” ባሏቸው አንድም ጠበቃ እንዳይቆምላቸው በጠበቆቻቸው ላይ ከመንግስት የሰላ ማስፈራሪያ በመድረሱ መብታቸው መጣሱን ሰኔ 18 ቀን 2016 ኣ.ም. ለችሎት ገልፀው ነበር፡፡ ችሎቱ አቶ ታዬን በመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ይፈልጉ እንደሆን ብጠይቃቸውም፤ “በመንግስት የሚቆምልኝ ጠበቃ አልፈልግም” የሚል ምላሽ መስጠታቸውም ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ጊቢ ውስጥ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አፍሪካ ህብረት ቅርንጫፍ በሀሰተኛ ሰነድ ከስድስት ሚሊየን ዶላር በላይ ገንዝብ ለማውጣት ሞክረዋል በሚል ክስ የተመሰረተባቸው የእነ ቀሲስ በላይ መኮንን መዝገብ ለብይን ለዛሬ ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩ በሚገባ መታየት አለበት በሚል ብይኑን ለመስጠት ለመስከረም 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሠ