አቶ በቀለ ገርባ እና የኦፌኮ አመራሮች ተፈቱ | ኢትዮጵያ | DW | 13.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አቶ በቀለ ገርባ እና የኦፌኮ አመራሮች ተፈቱ

ለሁለት ዓመት ከሁለት ወር ገደማ በእስር ላይ የቆዩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር አቶ በቀለ ገርባ ዛሬ ተፈቱ፡፡ አብረዋቸው ታስረው የነበሩ ስድስት የፓርቲው አመራሮች እና አባላትም ተለቅቀዋል፡፡  

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:35

አቶ ሙላቱ ገመቹ ስለ ፍቺው የሰጡት አስተያየት

ዛሬ ከተፈቱት ውስጥ የፓርቲው ምክትል ጸሐፊ አቶ ደጀኔ ጣፋ፣ የወጣቶች ክንፍ ምክትል ኃላፊው አቶ ጉርሜሳ አያኖ እና የወጣቶች ክንፍ ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ አዲሱ ቡላላ ይገኙበታል፡፡ የአቶ በቀለ ገርባን መፈታት የኦፌኮ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙላቱ ገመቹ ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል፡፡  አቶ ሙላቱ እነ አቶ በቀለ የተፈቱት በህዝብ መራር ትግል ነው ሲሉ ተናግረዋል። 

አቶ በቀለ ከተፈቱ በኋላ ለኦሮሚያ ብሮድካስቲን ኔትዎርክ (ኦቢኤን) በሰጡት አጭር ቃለ-ምልልስ እንዲለቀቁ ግፊት ላደረጉ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን አመስግነዋል። ተቀዳሚ ምክትል ሊቀ-መንበሩ መኖሪያ ቤታቸው ወደ ሚገኝበት አዳማ ከተማ ሲደርሱ ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አቶ በቀለ ገርባ እና አብረዋቸው የተከሰሱ ስድስት ሰዎች ክሳቸው እንዲቋረጥ መንግሥት መወሰኑን ትላንት አስታውቆ ነበር፡፡ አቶ በቀለን ጨምሮ አራት የኦፌኮ አመራሮች ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል አንድ ዓመት የእስር ቅጣት የተላለፈባቸው ቢሆንም ጉዳያቸው በይቅርታ ቦርድ ታይቶ እንዲፈቱ መወሰኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማዕረጉ አሰፋ ትላንት ለዶይቼ ቬለ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ 

አቶ በቀለ ከሌሎች 21 ተከሳሾች ጋር በመጀመሪያ የተከሰሱት የሀገሪቱን የጸረ-ሽብር ህግ ተላልፈዋል በሚል ነበር፡፡ በአቶ በቀለ ላይ የቀረበው የሽብር ክስ ወደ መደበኛ ወንጀል ክስ በተቀየረ ወቅት ከእርሳቸው ጋር አብረው ታስረው የነበሩ አምስት ሰዎች በነጻ ተለቅቀዋል፡፡ ከተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበሩ ጋር ጉዳያቸውን በፍርድ ቤት ሲከታተሉ ከነበሩ ተከሳሾች መካከል ዘጠኙ ከሳምንታት በፊት በአንደኛው ዙር የእስረኞች ፍቺ መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ 

አቶ ሙላቱ ገመቹ ስለ ኦፌኮ አመራሮች ፍቺ የሰጡትን አስተያየት የድምፅ ማዕቀፉን በመጫን ያድምጡ። 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic