አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ተበየነ | ኢትዮጵያ | DW | 01.11.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ በቀረበባቸው ክስ እንዲከላከሉ ተበየነ

የአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እነ አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ በቀረበባቸው ክስ ላይ እንዲከላከሉ ዛሬ ብይን ሰጥቷል፡፡ ፍርድ ቤቱ የዛሬውን በነ አቶ በረከት ስምዖን ላይ የከፈተውን መዝገብ ሲያጠናቅቅ ለህዳር 24/2012 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ነው፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:31

ለኅዳር 24 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል

እነ አቶ በረከት ህዝባዊ ድርጅቶችን ሥራን በማያመች ሁኔታ በመምራትና ሌሎች እንዲጠቀሙ አድርገዋል በሚል 4 ክሶች ተመስርቶበቸው ሲከራከሩ ቆይተዋል፤ በአንደኛ ክስ የዳሽን ቢራ ፋብሪካ የማምረትም ሆነ የገበያ አቅም እያለውና ተገቢው ጥናት ሳይካሄድ ለእንግሊዙ ዱየት ቢቬሬጅ ፋብሪካ ድርሻውን 50 ነጥብ 14 በመቶ በመሸጥ በፋብሪካው ላይ ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት ሊደርስ ችሏል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

በሁለተኛ ከስ ዱቬንቱስ ዊንግ ከተባለ የግል ኩባንያ ጋር የመብራትና የውሃ ቆጣሪ እዲያመርት የአዋጭነት ጥናት ሳይካሄድ ከህግ አግባብ ውጭ በመዋዋል ጉዳት ማድረስ ችለዋል፡፡ በዚህም ለባንክ ጋራንት በመስጠት፣ ለፋብሪካ ግንባታ ኪራይ፣ ለህንፃ ጥገናና መሰል ላልተሰራባቸው እንዲሁም ምንም አይነት የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ሳይኖር ከ210 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲባክን አድርገዋል በሚል ተከስሰዋል፡፡

በሦተኛና በአራተኛ ክስ ደግሞ ከዱቬንቱስ ዊንግ ኩባንያ ጋር በተያያዘ የጥረትን ጥቅም ማስጠበቅ ሲገባቸው ለዱቬንቱስ ዊንግ ኩባንያ የባንክ እዳ ጭምር በመክፈል ከ149 ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ብር ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል በሚል በዋና ወንጀል አድራጊነት ክስ ቀርቦባቸው በጠበቃቸው አማካይነት ሲከራከሩ ቆይተዋል፡፡

የቀድሞዎቹ የኢህዴን በኋላም የብአዴንና የኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት የነበሩት አቶ በረከት ስምዖንና አቶ ታደሰ ካሳ የአማራ ክልል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በሙስና ወንጀል ጠርጥሯቸው በባሕር ዳርና አካባቢው ከፍተኛ ፍርድ ቤትና በአማራ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከጥር አጋማሽ 2011 ዓ ም ጀምሮ ጉዳያቸው ሲመረምር ቆይቷል፡፡

የእነ አቶ በረከት ጉዳይ በፍርድ ቤት ሲታይ በመጀመሪያዎቹ የፍረድ ቤት ውሎዎች ጠበቃ ያልነበራቸው ሲሆን በኋላ 2 ጠበቃዎችን በራሳቸው ያቆሙ ቢሆንም ጠበቆቹ ዛቻ ደርሶብናል በሚል ጥብቅናቸውን አቋርጠዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት እነ አቶ በረከት ከአዲስ አበባ ጠበቃ በፕላዝማ ይቁምልን ሲሉ ጥያቄም አቅርበው የነበረ ቢሆንም በወቅቱ ይህ እንደማይቻል በፍርድ ቤቱ ተገልፀላቸው ነበር፤
ከዚያም ተጠርጣሪዎቹ ለሚያቆሙት ጠበቃ ዋስትና አንዲሰጥላቸው አመልክተው ከአዲስ አበባ ጠበቃ ቀጥረው ማቆም የቻሉ ሲሆን ጠበቃቸውም አስፈላጊው ጥበቃ በመንግስት በኩል እንዲደረግ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ የነ አቶ በረከት የፍርድ ቤት ሂደቱ ክርክር በጠበቃ በኩል ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ 

መስከረም 30/ 2012 ዓ ም ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ እንደ አጋዥ ማስረጃ ይያዝልኝ ሲል ያቀረበውን ተጨማሪ 141 ገፅ የሰነድ ማስረጃ ተቀብሎ ከዚህ ቀደም ለቀረበው 1000 ገፅ ለሚጠጋ የሰነድ የማስረጃ አካል አድርጎ ከመረመረ የአማራ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እነ አቶ በረከት ስምዖን፣ አቶ ታደሰ ካሳ እና በዱቬቱስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ስራ አስኪያጅና ባለቤት አቶ ዳንኤል ግዛው የቀረበባቸውን ክስ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል፡፡ ዛሬ ተከሳሾቹ ወደ ፍርድ ቤት ሲገቡም ሆነ ሲወጡ እንደከዚህ ቀደሙ የተቃዎሞ ድምፆች አልተሰሙም፡፡

ግለሰቦቹ አጠቃላይ በጥረት ኮርፖሬሽን ላይ ከ2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር በላይ እንዲባክን አድርገዋል በሚል ነው ጉዳቸው በፍርድ ቤት እየታዬ ያለው፤ የኢፌድሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና የሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 13/3 ስር የተደነገገውን የሙስና ወንጀል የተላለፈ ከ15-25 ዓመት እስር እንደሚያስቀጣ ይደነግጋል፡፡

ጥረት የብአዴን (አዴፓ) ትስስር እንዳለው ሲታወቅ አቶ በረከት በቦርድ ሰብሳቢነት፣ አቶ ታደሰ ካሳ ደግሞ በሥራ አስፈፃሚነት ኮርፖሬሽኑን ለዓመታት መርተውታል፡፡ የተቋቋመውም በትጥቅ ትግል ወቅት በዓይነትና በጥሬ ገንዘብ ባሰባሰበው ንብረት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ የዛሬውን በነ አቶ በረከት ስምዖን ላይ የከፈተውን መዝገብ ሲያጠናቅቅ ለህዳር 24/2012 ተለዋጭ ቀጠሮ በመስጠት ነው፡፡

ዓለምነው መኮንን
እሸቴ በቀለ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች