አቶ ሌንጮ ለታና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር | ኢትዮጵያ | DW | 30.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አቶ ሌንጮ ለታና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር

በውጭ የሚገኘው ተቃዋሚ ፓርቲ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመሳተፍ ከመንግስት ጋር ለመደራደር ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ሌንጮ ለታ ተናገሩ። ፓርቲው ወደ ፊትም ከመንግስት ጋር ለመደራደር ግፊት ማድረጉን ይቀጥላል ተብሏል።

አቶ ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (Oromo Democratic Front) መስራች እና ፕሬዝዳንት ናቸው። አቶ ሌንጮ ከአሁኑ ፓርቲያቸው በፊት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (OLF) ከፍተኛ አመራር ነበሩ። በስደት የተመሰረተው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ከወሰነ ከራርሟል። ፓርቲው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ለመሳተፍ ውሳኔ ቢያሳልፍም ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር መደራደር ግን ቀዳሚው ጉዳይ ነው። «አብዛኞቻችን በኦሮሞ ነጻነት ግንባር በኃላፊነት ስንሳተፍ የነበርን ሰዎች ስለነበርን ከገዢው ፓርቲ ጋር የቆየ ግንኙነት እንዲሁም አለመግባባት ስለነበረን በእነሱም በኩል ጥያቄዎች ሊነሱ ይችላሉ በእኛም በኩል ሃሳቦች አሉን።» የሚሉት አቶ ሌንጮ ኦዴግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለሚያደርገው ተሳትፎ ድርድሩ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህንን ድርድር ለመጀመር በአቶ ሌንጮ ለታ የሚመራ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር ልዑክ መጋቢት 9/2007 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ አቅንቶ በለስ ሳይቀናው ተመልሷል። የልዑካን ቡድኑ ወደ ኢትዮጵያ ያቀናው ለሁለት አመታት ከመንግስት ጋር ቀጠሮ ለመያዝ የተደረገው ሙከራ ባለመሳካቱ መሆኑን አቶ ሌንጮ ይናገራሉ።

«እዚህ ውጪ ሆነን ከሁለት አመት በላይ ከመንግስት ጋር ቀጠሮ ለመያዝ ሞክረን ስላልተሳካልን ድንገት እዚያው ብንሄድ የተሻለ አጋጣሚ ይሆናል በማለት ነበር የሄድንው።» የሚሉት አቶ ሌንጮ «ከመንግስት ጋር ውጪ ሆናችሁ ተነጋግራችሁ ያ ካለቀ በኋላ ነው ወደ ሃገር መመለስ የምትችሉት።» የሚል መልዕክት እንደደረሳቸው ተናግረዋል።

አቶ ሌንጮ ለታ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለመሳተፍ የሚያደርገውን ጥረት እንደሚቀጥል እና ከመንግስት ጋር ለመወያየት ግፊት እንደሚያደርግ ተናግረዋል። በዚህ ዘገባ ላይ የኢትዮጵያ መንግስትን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

እሸቴ በቀለ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic