አትክልቶች አንጎል አላቸው ? ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ? | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 20.05.2009
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አትክልቶች አንጎል አላቸው ? ሳይንቲስቶች ምን ይላሉ?

ከሳይንስ ጋር ግንኙነት ያላቸው ጉዳዮችም ሆነ፣ ሳይንስ ነክ ዜና- የዩናይትድ ስቴትስ ጠፈርተኞች፣ በአትላንቲስ መንኮራኩር ወደ ኅዋ ተጉዘው፣

default

ድንክዬ ዛፍ፣

ብልሽት አጋጥሞት የነበረውን የጠፈሩን ቴሌስኮፕ «ሃብል»ን ጠግነው እንደገና ተግባሩን እንዲያከናውን ያሠማሩት መሆኑ ተነገረ። የጥገናው ተግባር የተከናወነው፣ ከአፍሪቃ ክፍለ-ዓለም 560 ኪሎሜትር ርቀት፣ ኅዋ ላይ ሲሆን፣ የመጨረሻውና ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደው የጥገና ተግባር ከትናንት በስቲያ የተከናወነው ከ 6 ሰዓት በላይ ጠፈርተኞችን አድክሞ ነው። ሰው ክብደቱን አጥቶ እንደ አበባ ብናኝ በሚንሳፈፍበትና ራስ በሚያዞርበት ሁኔታ የተሠራው ሥራ አስደናቂ መሆኑ አላጠራጠረም። ሁለቱ ጠፈርተኞች፣ ጆን ግሩንስፌልድና አንድርው ፎይስተል፣ ጎንት የጠፈርተኛ ጓንት እንዳደረጉ፣ አንዳንዴም የኅዋ ልዩ ልብሳቸውን ሊቀድ ይችል በነበረ የሰላ መሣሪያ ጭምር በመጠቀም፣ 111 ብሎኖችን ም በማጥበቅ የተደነቀ ተግባር ያከናወኑት። ። Hubble Telescope በመጀመሪያ በኅዋ እንዲሠማራ የተደረገው እ ጎ አ በ 1990 ዓ ም ሲሆን፣ በ 1993, 1997 ፣ በ 1999 እና በ 2002 ዓ ም ፣ እድሳት ብቻ ሳይሆን ፣ አዳዲስ የምርምር መሣሪያዎችም እየተጨመሩበት፣ ስለኅዋ ባለፉት 19 ዓመታት፣ በሰፊው ሳይንሳዊ መረጃ ሲያቀርብ መቆየቱ የታወቀ ነው። ሃብል፣ በሚመጡት 5 ዓመታት አንዳች እንከን ሳያጋጥመው ተግባሩን እንደሚያከናውን ነው ተስፋ የሚደረገው። ሃብልን ጠግነው ያሠማሩት ጠፈርተኞች ፣ በአትላንቲስ መንኮራኩር ከነገ በስቲያ ወደ ምድር በመመለስ፣ ፍሎሪዳ በሚገኘው በአሜሪካ የኅዋ ምርምርና የበረራ አስተዳደር NASA ጣቢያ በሆነው የኬነዲ የኅዋ ምርምር ማዕከል ያርፋሉ።

ብራዚልና ቻይና ፣ ከጋራ ሳቴላይቶቻቸው ለአንዳንድ የአፍሪቃ መንግሥታት መረጃ ለመስጠት መስማማታቸው ተነገረ። ደቡብ አፍሪቃ ውስጥ፣ ሃርተቢሾክ በተሰኘው ጣቢያ ፣ ግብጽ ውስጥ በአስዋን፣ እስፓኝ ውስጥ ማስፓሎምስ በተሰኙ ጣቢያዎች የሚገኙ ጣቢያዎች፣ ከቻይናና ብራዚል የጠፈር ሳቴላይት መረጃዎችን እንዲያገኙ ይደረጋል። የ 3 ቀናት ጉብኝታቸውን የደመደሙት የብራዚል ፕሬዚዳንት ልዊዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ፣ ቤይጂንግ ውስጥ ይኸው የኅዋ መረጃ አቅርቦትን በተመለከተው ውል የመፈራረም ሥነ-ሥርዓት ለመገኘት ችለዋል። ቻይናና ብራዚል፣ በዚሁ ስምምነታቸው ከአፍሪቃ ጋር የቱን ያህል የመቀራረብ ፍላጎት እንዳላቸው ሳያመላክቱም አልቀሩም። ሉላ፣ ገብኝታቸውን ፈጽመው፣ ዛሬ፣ ከቤይጂንግ ከመነሣታቸው በፊት፣ ትናንት በተከናወነ ውሎች የመፈራረም ሥነ-ሥርዓት፣ የኃይል ምንጭን፣ ሳይንስና ኅዋንና ሌሎች ሌሎችንም የሚመለከቱ 13 ስምምነቶችን ፈርመዋል።

ሳይንቲስቶች፣ ከሰው፣ ከ ጦጣና ዝንጀሮ ፣ ቤተሰብ ጋር ቀጥተኛም ባይሆን የሩቅ ዝምድና ሳይኖረው እንዳልቀረ የተነገረለት ፣ 47 ሚሊዮን ዓመታት ያስቆጠረ፣ የአንድ ዝንጀሮ ቅሪተ-አካል ማግኘታቸውን ገለጡ። ቅሪተ-አካሉ የተገኘው በጀርመን ሀገር ሲሆን፣ ከጉልበቱ በታች አንደኛው እግሩ ብቻ ከመጉደሉ በስተቀር፣ ቅሪተ አካሉ የተሟላ ነው ተብሏል። ይሁንና ይኸው ቅሪተ-አካል፣ ስለመቅድማዊው ዝግመታዊ ለውጥ ፍንጭ ሳይሰጥ እንደማይቀር ተገምቷል።

በዓለም ውስጥ ሀይወት ካላቸው ነገሮች ሁሉ፣ ለመገመት በሚያስቸግር ሁኔታ እጅግ ረዘም ያለ ዕድሜ ያለው፣ ከአውስትሬሊያ በስተደቡብ በተስማኒያ ደሴት የሚገኘው Lomatia Tasmanica በሚል ሳይንሳዊ መጠሪያ የሚታወቀው ዛፍ መሆኑን፣ በየብስ ከሚኖሩት ዐራዊትና እንስሳት መካከልም የትኞቹ እንደሆኑ ፣ ከዚህ ቀደም በዚህ ክፍለ-ጊዜ መጥቃሳችን ይታወስ ይሆናል። በባህር ውስጥ ከሚኖሩት እንስሳት የዕድሜ ባለጸጎቹ የትኞቹ ይመስሏችኋል? አሣ ነባሪ አይደለም። ይሁን እንጂ ምድቡ ከአሣ ነው። ከአሣም እጅግ ውድ የሆነውን ለጤነነትም፣ ለቅንጦትም ማዕድ የሚቀርበውን ካቢያር የተሰኘውን እንቁላል ከሚጥሉት የአሣ ዝርዮች መካከል፣ Acipenserinae ከሚሰኘው ቡድን የሚመደበው Acipenseridae በሚል የሳይንስ መጠሪያ የሚታወቀው ነው። ጀርመናውያን፣ Stör ይሉታል። 152 ዓመት የኖረ አንድ ካቪያር የሚያመርት አሣ እንደነበረ የተመዘገበ ሲሆን፤ ከዚያ በላይ 154 ዓመት ድረስ መኖር የቻለ የዚሁ ዝርያ አሣ እንደነበረም ይነገራል። ከኣሦች መካከል አጥቢዎች ከሆኑት የባህር እንስሳት መካከል አንዳንድ አሣ ነባሪዎች 100 ዓመት ድርስ መኖር እንደሚችሉ መረጋገጡን Harro Hieronimus የተባሉ ጀርመናዊ የአሣ ምርምር ጉዳይ ባልደረባ አስረድተዋል። 70 ዐመት መደፈን የማይሳናቸው ሞልተዋል። ወርቅማ አሣ (ጎልድፊሽ)የሚባለው ደግሞ እስክ 46 ዓመት ድረስ መኖር እንደሚችል ተረጋግጧል። አሦችን የውጭ አካላቸውን በማየት ብቻ የዕድሜአቸውን መጠን መገመት ከባድ ነው። ማርጀታቸው የሚታወቀው ልክ እንደ ዛፍ ግንድ ክብ- ክብ መስመሮች ባሉት ጆሮአቸው ነው።

ሳይንቲስቶች፣ በአዲስ የ DVD ሥን-ቴክኒክ፣ መረጃዎችን፣ በ 5 አቅጣጫዎች ለማሰባሰብ ፣ ከ 2,000 በላይ ፊልሞችን በአንድ ዲስክ ውስጥ ማጠራቀም የሚቻልበትን ዘዴ ማስተዋወቃቸው ተነገረ። በሜልበርን አውስትሬሊያ የሥነ ቴክኒክ ዩኒቨርስቲ የምርምር ቡድን አባላት ረቂቅ ሥነ-ቴክኒክን (ናኖቴክኖሎጂ)ን በመጠቀም ነው፣በአንድ መደበኛ የ DVD ዲስክ መሰብሰብ ከሚቻለው በላይ 10,000 እጥፍ የተለያዩ ነገሮችን መቅረጽ እንደሚቻል ለማረጋገጥ ችልዋል።

ባለፈው ወር የዩናይትድ ስቴትስ ግዙፍ የሥነ-ቴክኒክ ኢንዱስትሪ ኩባንያ General Electric መደበኛው DVD ከሚይዘው 100 እጥፍ የሚያጠቃልል አዲስ ዲስክ መሥራቱን አስታውቆ እንደነበረ ይታወስ ይሆናል። በሁለት ወገን የሚሠራው የብሉ ሬይ ዲስክ ከመደበኛው DVD የላቀ 10 እጥፍ የሚፈለገውን ነገር መቅረጽ የሚያስችል መሆኑ ይታወቃል።

ከታወቁት ህይወት ካላቸው ነገሮች መካከል፣ ከሰውና እንስሳት ሌላ ሣር ፣ ቅጠላ-ቅጠል፣ አትክልቶች፣ ዕጽዋት መሆናቸው የታወቀ ነው። አትክልቶች የሰውንም ሆነ የአንስሳትን መሰል አንጎል የላቸውም። ነገር ግን ፣ መሬት ውስጥ በሥራቸው፣ ተግባራቸውን የሚቆጣጠር ትእዛዝ ማስተላለፊያ አንጎል መሰል አካል አላቸው። በምርምር የመራቀቁ ሁኔታ እየሰፋ በሄደ ቁጥር ፣ አዳዲስ ግንዛቤን ማካባት ያለ ነገር ነው። የሁምቦልት ዩኒቨርስቲ በሰጠው ነጻ የትምህርት ዕድል፣ ከእስሎቫኪያ ለከፍተኛ ምርምር፣ ወደ ጀርመን በመምጣት በቦን ዩኒቨርስቲ ምርምር የሚያካሂዱት ፍራንቲሴክ ባሉስካ እንዲህ ይላሉ።

«በፍሎሬንስ ምርምር ከሚያካሂድ ቡድን ጋር በመቀናጀት ባደረገነው ጥናት፣ አትክልቶች፣ በአንጎል እንደሚከናወኑ ተግባራት በሥሮቻቸው፣ ተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚከናወን በኤልክትሪክ ሞገድ አማካኝነት ለማሳየት ችለናል። የኅዋሳቱም ይዞታ በአንስሳት አንጎል ካለው የሥራ እንቅሥቃሴ ጋር ተማሳሳይነት እንዳለው የተረጋገጠ ነው። ይህ ምርምር እርግጥ ነው በጅምር ላይ ያለ ነው። ስለሆነም፣ የአትክልት አንጎል ብሎ መናገር ያዳግታል። ማለት የሚቻለው ፣ ትእዛዝ አስተላላፊ ማዕከል፣ ነው።»

በ 1990 ዎቹ ዓመታት በብራቲስላቫና ቦን ዩኒቨርስቲዎች ትብብር ሳቢያ ወደ ጀርመን የመጡት ባሉስካ፣ በቦን ዩኒቨርስቲ በሚያካሂዱት ምርምር ፣ የአትክልት ሥርና ኮምፒዩተር አይለዩአቸውም። ፍራንቲሴክ ባሉስካ፣ በአትክልት ሥር ፣ የተለያዩ ክፍሎችን እርከኖችና ተግባራቸውን ለይተው ያስረዳሉ።

የሥን ፍጥረት ተመራማሪ ባሉስካ፣ የአንድ አትክልት ሥር ፣ ሾጠጥ ያለው ጫፉ ብርሃን ወይም መርዘኛ ነገር --የሚያጋጥመውን ይመዘግባል። ሥሩ፣ ከጫፉ ወደ መሃል፣ መልእክት ሲተላለፍለት፣ ጠቅላላው ሥር፣ አትክልቱ፣ ወደየት አቅጣጫ ማደግ እንዳለበት ይወስናል። በቦን ዩኒቨርስቲ የአፀድ ጥናት ክፍል ተመራማሪ ዲተር ፎልክማን እንዳሉት፣ ይህ ዓይነቱ ሂደት በእንስሳት ዓለም አንጎል ከሚታየው የተለየ አይደለም። የአትልክልት ትእዛዝ አስተላላፊ ጣቢያ ፣ የአትክልት የነርቭ መዋቅር ነው ማለት ይቻላል። ሌላው የተጠቀሰው ዘርፍ ባልደረባ ሁበርት ፌለ፣ በበኩላቸው---

«አትክልት አይንቀሳቀስም ፣ መሮጥ አይችልም። ጡንቻም ፣ እግርም የለውም። ስለዚህ ባለበት፣ በራሱ ዘዴ ጥቃት ሊሠነዝር የሚመጣ ጠላትን መመከት ይኖርበታል። በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ማለትም ፣ በግማሽ ሰዓት ውስጥ አደጋ ጣዪው የሚግጠውም ሆነ የሚቀምሰው ግንድ ቅርንጫፍም ሆነ ቅጠል፣ እንዳይጥመው የሚያደርግ እርምጃ አትክልቱ ይወስዳል። አለበለዚያም አጥቂው እንዲመረዝ ያደርጋል ማለት ነው።»

አትክልቶች፣ ከእንስሳት የባሱ እንደግዑዝ ጾታ ሆነው መታየት የለባቸውም። ልዩነታቸው አንደኛው ወገን ከቦታ-ቦታ ሲንቀሳቀስ ፣ አትክልት ካለበት ንቅንቅ የሚል አለመሆኑ ብቻ ነው።

ተክሌ የኋላ፣

ሒሩት መለሰ፣