አትሌት ሹሚ ደቻሳ ማራቶን ማሸነፉ፣ --- | ስፖርት | DW | 05.05.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ስፖርት

አትሌት ሹሚ ደቻሳ ማራቶን ማሸነፉ፣ ---

በዛሬው ዝግጅት ፤ አትሌቲክስ፤ የሜዳ ቴኒስ ፣ በይበልጥ ደግሞ እግር ኳስና ይሆናል ላቅ ያለ ትኩረት የሚሰጠው።

ትናንት በሰሜን ጀርመን የወደብ ከተማ ሓምበርግ፣ ለ 29 ኛ ጊዜ በተካሄደው የማራቶን ሩጫ ውድድር ፣ ኢትዮጵያዊው የ 24 ዓመት ወጣት አትሌት ሹሚ ደቻሳ፣ 42 ኪሎሜትር ከ 195 ሜትር ርቀቱን በ 2 ሰዓት ከ 6 ደቂቃ ከ 44 ሴኮንድ በማጠናቀቅ አንደኛ ሆኗል ። ዝነኛው ኃይሌ ገ/ሥላሴ በዚህ ሩጫ ለመሳተፍ ተዘጋጅቶ እንደነበረ ቢታወቅም፤ የአበባ ብናኝ ሳንክ «አለርጂ» አስከትሎ ስላስቸገረው እንደማይሳተፍ አሠልጣኙ ቀደም አድርገው ማስታወቃቸው የሚታወስ ነው።

በትናንቱ የሀምበርግ የማራቶን ውድድር 2 ቱ ኬን4ያውያን ታዋቂ ራጮች፣ ኤሪክ እንዲማና ፊሊሞን ሮኖ በአንድ ደቂቃ ገደማ ልዩነት 2ኛ ና ሦስተኛ ወጥተዋል። ከጀርመን ዩልያን Flügel2 ሰዓት ከ 15 ደቂቃ ከ 39 ሴኮንድ 14 ለመውጣት ችሏል።

በሴቶች የማራቶን ውድድር ኬንያዊቷ ጂዎርጂና ሮኖ በ 2 ሰዓት ከ 26 ደቂቃ ከ 48 ሴኮንድ አንደኛ ስትሆን፤ ኢትዮጵያዊቷ አትሌት ድንቅነሽ መካሻ በ 2 ሰዓት ከ 27 ደቂቃ ከ 30 ሴኮንድ 2ኛ፣ ሌላዋ ኬንያዊት ዊኒ ጄፕኮሪር ደግሞ 3ኛ ለመሆን በቅታለች። መልካም ግዛው 4ኛ ሆናለች።

ጀርመናዊቷ ካታሪና ሃይኒኽ በ 2 ሰዓት ከ 33 ሴኮንድ ከ 56 ሴኮንድ 9ኛ ነው የወጣች።

እግር ኳስ፤

የዓለም የእግር ኳስ ዋንጫ ብራዚል ውስጥ ሊጀመር አንድ ወር ከአንድ ሳምንት ቀርቶት ሳለ በተለያዩ ሃገራት የክለቦች የተለያዩ ውድድሮች በመገባደድ ላይ ናቸው። በዚህ ላይ ለምሳሌ ያህል አውሮፓ ውስጥ የሻምፒዮን ሊግ ፍጻሜና በየገራቱም የክለቦች ጥሎ ማለፍ የዋንጫ ውድድሮች የሚጠናቀቁት በዚህ ወር ውስጥ ነው። ታዲያ ቀደም ብሎ በሰኔ ወር መግቢያ ላይ የዓለም የአግር ኳስ ዋንጫ የሚጀመር መሆኑ፤ ያን ያህል በቂ ዕረፍት ሳያገኙ ከክለቦች ወደ ብሔራዊ ቡድኖች ከባድ ውድድር የሚሸጋገሩት ተጫዋቾች፣ የቀረው ጊዜ አጭ ር በመሆኑ ፣ የሚጠበቅባቸውን ያህል ተጫውተው ለአመርቂ ውጤት የመብቃት ችሎታቸው እስከምን ድረስ ይሆን? ሳንክ አያጋጥማቸውም ወይ ? የእስፖርት ጉዳዮች ተንታኛችን መሥፍን መኮንን እንዲህ ይለናል።

አሁንም ከዚያው ከእግር ኳስ ሳንወጣ፤ የተለያዩ ታዋቂ የእግር ኳስ ተጫዎቾች በቴሌቭዥን እንደመስታወቂያ «ዘረኛነት ቦታ የለውምቢሉም ፤ የዓለም የአግር ኳስ ፌደሬሽንና የአውሮፓ የአግር ኳስ ማሕበር ተመሳሳይ ማስታወቂያ በታላላቅ ግጥሚያዎች ስታዲዮም ውስጥ ቢያሳዩም ይህ እኩይ ልማድ ሊገታ የቻለ አልመሰለም።

ኢጣልያ ውስጥ፤ በዘንድሮው የዋንጫ ፍጻሜ ግጥሚያ ቅዳሜ ዕለት ፣የናፖሊ ክለብ ፍሎሬንስን (ፊሬንዜ)3-1 ከማሸነፉ በፊት በደጋፊዎች መካከል ፣ የእግር ኳስ አፍቃሪውን ዓለም ባስደነገጠ ሁኔታ በተፈጠረው አምባጓሮ ብዙዎች ቆስለዋል። አንድ የ A S ROMA ቡድን ደጋፊ በናፖሊ ደጋፊዎች ላይ በሽጉጥ 4 ጊዜ ተኮሶ አንዱን በጠና አቁስሏል። የቆሰለው ሰው አስቸኳይ ቀዶ ህክምና ተደርጎለት በሳምባው በኩል ጀርባው ላይ የተሠነቀረውን ጥይት አውጥተውለት ህይወቱ ብትተርፍም ሽባ ሆኖ መኖር መጥፎ ዕጣው ሊሆን እንደሚችል ተነግሯል። የአውሮፓ የአግር ኳስ ማሕበር እንዳለው ባለፉት 5 ዓመታት እንደ ኢጣልያ የእግር ኳስ ክለቦች አስከፊ ሁኔታዎች ያየሉበት በየትናውም የአውሮፓ ሀገር አልታየም። ባለፉት 30 ዓመታት እንዲያውም በሥርዓት አልበኛነት ቀዳሚውን ቦታ መያዙ ነው የሚነገርለት። በኢጣልያ ስታዲየሞች፤ ዘረኞች፤ ፋሺስቶች፤ ማፊያዎች ና ሌሎች ወንጀለኞች ሆነዋል ዋንኞቹ ተዋናዮች። የኢጣልያ

ጋዜጦች እንደጻፉት፤ የሀገሪቱ መንግሥት ፤ ለእነዚህ የኃይል እርምጃ ለሚወስዱ ጥቂት ጋጠ- ወጦች እጁን ሰጥቷል ። 4 ጊዜ የዓለምን ዋንጫ ያገኘችው ሀገር መንግሥት ያላት አልመሰለችም፤ የእግር ኳስ እስፖርትም እጅግ ከባድ ቀውስ አጋጥሞታል ።

ጁቬንቱስ ቱሪን ፤ የዘንድሮው የኢጣልያ ሽምፒዮና ለመሆን ሲበቃ፤ በኢንግላንድ ማንቸስተር ሲቲ ለ 2ኛ ጊዜ ሻምፒዮን የሚሆንበትን ነጥብ በመሰብሰብ ላይ ሲሆን ፤ ቅዳሜ ኤቨርተንን 3-2 ረተትቷል።

በዚህ በጀርመን ሀገር የቡንደስሊጋ ሻምፒዮን ባየርን ሙዑንሸን፤ ግንቦት 9 ቀን 2006 ዓ ም

በርሊን ውስጥ ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ ጋር የዋንጫ ግጥሚያ ለማካሄድ ሁለቱን ቡድኖች በመዘጋጀት ላይ እንዳሉ፤ ለ50 ዓመታት ያህል ከአንደኛ ምድብ ወርዶ የማያውቀው የሃምበርግ እግር ኳስ ክለብ ወደ 2ኛ ምድብ እንዳይወርድ በብርቱ ሥጋት ላይ ይገኛል። በሳምንቱ ማለቂያ ላይ በባየርን 4-1 ነበረ የተሸነፈው።እስፓኝ ውስጥ፤ ከ3 ቱ ታላላቅ ክለቦች፤ አትሌቲኮ ማድሪድ በሌባንቴ 2-0 ሲሸነፍ ፤ ሪያል ማድሪድ በሜዳው ከባሌንሲያ ጋር 2-2 ተለያይቷል፣ ባርሴሎናም በራሱ ሜዳ ከ ጌታፈ ጋር 2-2 ነው የተለያየው።

በመጨረሻም፤ በሜዳ ቴኒስ ፣ በብሪታንያ አንድ ወቅት ግንባር ቀደም የሜዳ ቴኒስ ተቻዋች የነበረችው ኤሌና ባላታቻ በጉበት ካንሠር ሳቢያ ቅዳሜ ሌሊት ማረፏ ተነግሯል። ታዋቂ ቴኒስ ተጫዋቾች፤ ሴሬና ዊልያምስ ፤ ኪም ክልይስተርስ፣ ማርቲና ናርቫቲሎቫ ቢሊ ጂን ኪንግ በኤሌና ሞት የተሰማቸውን ኀዘን ገልጸዋል።

ተክሌ የኋላ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic