አቴና፤ ምክር ቤት የቁጠባ እቅዱን አሳለፈ | ይዘት | DW | 29.06.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ይዘት

አቴና፤ ምክር ቤት የቁጠባ እቅዱን አሳለፈ

የግሪክ ምክር ቤት በዓለም ዓቀፍ ገንዘብ አበዳሪዎቹ የተጠየቀዉን ከእዳ መዉጫ እቅድ አሳለፈ።

default

ቀረጥ በመጨመር ወጪን መቀነስን ያካተተዉ ጠንካራ የቁጠባ እቅድ ማለፍ አገሪቱ ከአዉሮጳ ኅብረትና የዓለም የገንዘብ ተቋም IMF የ28 ቢሊዮን ዩሮ ብድር እንድታገኝ እንደሚረዳ እየተገለጸ ነዉ። እንዲያም ሆኖ በክስረት አፋፍ ላይ የቆመዉ የግሪክ መንግስት እቅዱን ቢያጸድቅም፤ ተግባራዊ የሚያደርግበት አቅም ከየት ይመጣል የሚለዉ እያነጋገረ ነዉ። ፕሮፌሰር ቶማስ ሽትራዉሃር የሃምቡርግ የምጣኔ ሃባት ተቋም ዳይሬክተር፤

«ባጠቃላይ በግሪክ ቀረጥን መሰብሰብ መጀመሩ በጣም አስፈላጊ ነዉ። ሆኖም ይህን ብቻ ራሱ ተግባራዊ የማድረጉ ነገር አዳጋች ይመስለኛል።»

በአንፃሩ አቴንስ ዉስጥ በተቃዉሞ ጎዳና ላይ የወጣዉ ሕዝብ ከምክር ቤቱ ደጃፍ ከፀጥታ አስከባሪዎች ጋ ሲጋጭ ዉሏል። በአነስተኛ ንግድ ሠራ የተሰማራ የሁለቶች አባት የሆነዉ የ30ዓመት ወጣት አንቶኒስ ክሪቲኮስ ላለፉት አምስት ሳምንታት በምክር ቤቱ ደጃፍ በየምሽቱ ተቃዉሟቸዉን ከሚያሰሙት መካከል አንዱ ነዉ።

«በምርጫ ወቅት እነዚህ ፖለቲከኞች ከግሽበቱ በላይ የሚሆን የደሞዝ ጭማሪ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዉ ነበር፤ በተቃራኒዉ ደሞዙ ባለበት ሆኖ አሁን ደግሞ ግብር ለመጨመር ተዘጋጅተዋል፤ የምግብ ሸቀጥ ዋጋ ንሯል። በዚያ ላይ ምንም እንኳን ለአራት ዓመት ብቻ ቢመረጡም ለቀጣይ አርባና ሃምሳ አመት የሚያሰቃየን ዉሳኔ ሊያሳልፉ ተዘጋጅተዋል።»

ተቃዋሚዎቹ በግሪክ ፖስታ ቤት ህንፃ አንደኛ ፎቅ ላይም እሳት መለኮሳቸዉን በቅርብ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ