አቦል ጥበብ | ባህል | DW | 14.09.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ባህል

አቦል ጥበብ

«በ 2010 በጣም ብዙ ለዉጥ የሚመስሉ ንፋሶች ያየንበት ነዉ። በርግጥ ለዉጥ መምጣት አለመምጣቱን የምንወስነዉ ወደፊት ነዉ። የአንድነት ነፋሱ እንዳለ ሆኖ በጣም አስጊና አስፈሪ የሆኑ ነገሮች እየታዩ ነዉ። ለኢትዮጵያ አንድነት፤ ለፍቅር ለመቻቻል እና ለተሻለ ነገር፤ የጥበብ ሰዎች የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት መጀመር አለብን ብዬ አምናለሁ።» ገጣሚዋ

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:47
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
15:47 ደቂቃ

ለዉጡን የኪነ-ጥበብ ሰዎች ሊሰሩበት ይገባል 

እንኳን ለአዲሱ 2011 የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት አደረሳችሁ! ግጥም ከኪነ-ጥበብ  የሰው ልጅ ሁለንተናውን የሚነድፍበት፣ ስሜቱንና አመለካከቱን የሚቀርጽበት ዘርፍ መሆኑን ምሁራን ይናገራሉ። ከኪነ-ጥበብ ዘርፎች ሥነ-ጥበብ፤ ድርሰት፤ ተውኔት፤ ሙዚቃ፤ ሥነ-ቅርፅ፤  ፣ የፊልም ጥበብ ግጥም ያካተተ ሲሆን የተለያዩ ነጥቦችና ከተለያዩ ሞያዎችና ክህሎቶች በመዉሰድ የሚበለጽግ ዘርፍም ነዉ። ኪነ-ጥበብ ከባህልና ከፍልስፍና ጋር ያለው ቁርኝት እጅጉን የጠበቀ መሆኑም እሙን ነዉ። ኪነ-ጥበብ በታሪክ፣ በአስተዳደር ርዕዮተ ዓለም መለዋወጥ፤ ክሰዉ ልጆች የእዉቀት ደረጃ መሻሻልና መበልፀግ ጋር አትኩሮቱና አገልግሎቱ እንዲሁም እይታዉ ተለዋዋጭ ነዉ። በዚህ መሰናዶ ጎንደር  አቦል ጥበብ የግጥም ስብስብ አባላት ከየእለት ሞያቸዉ ጎን ለጎን ወጣትን በማሰባሰብ በተለይ በሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ የሚያደርጉትን አስተዋፅኦ እናያለን! 

በጎንደር ከተማ የሚኖሩ ወጣቶች ናቸዉ። የከፍተኛ ትምህርታቸዉን አጠናቀዉ በጋዜጠኝነት በምህንድስና እንዲሁም በጠበቃ እና ሕግ አማካሪነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። በትርፍ ጊዜያቸዉ ደግሞ በከተማዋ የተለያዩ ኪነ-ጥበባዊ መድረኮች ላይ ይሳተፋሉ። ከሦስት ዓመት ገደማ « አቦል ጥበብ » በሚል ርዕስ የጀመሩት የግጥም መድረክ ምሽት የከተማዋን የሥነ ግጥም እና የሥነ ጽሑፍ አፍቃሪ በየወሩ አንድ ጊዜ ማሰባሰብ ጀምሮአል። ወጣት ፍቅር አዲስዘዉዱ  «አቦል ጥበብ» ከመሰረቱት ወጣቶች መካከል አንድዋ  ስትሆን  የአማራ መገናኛ ብዙኃን የእንጊሊዘኛ ክፍል ጋዜጠኛ ሆና በማገልገልም ላይ ትገኛለች።

«አቦል ጥበብ ከተመሰረተ ሦስት ዓመት አለፈዉ። ባለፈዉ ግንቦት ወር ሦስተኛ ዓመታችንን አክብረናል። የግጥም ምሽታችን በየወሩ የመጀመርያዉ አርብ እለት ነዉ። ስብስባችን በጣም የተለያየ ነዉ። አሁን እኔ ለምሳሌ ጋዜጠኛ ነኝ። መክት ጠበቃ ነዉ። ሰሎሜ ኢንጂኔር ነች። ለመኖር የምንሰራዉ የተለያየ ሥራ አለ። ሁላችንም የተለያየ የሞያ ዘርፍ ላይ የተሰማራን ሰዎች ነን። እኛን ያሰባሰበን ግጥም ነዉ። ያሰባሰበን ጥበብ ነዉ። አቦል ማለት የመጀመርያ ማለት ነዉ። ዝግጅታችንን አቦል ብለን የሰየምነዉ ከዚህ በፊት መድረክ ላይ በአይነታቸዉ ያልታዩ አቀረራረቦችን እና ጽሑፎችን ይዘን መድረክ ስለምንወጣ ነዉ። ለምሳሌ የጎንደር አካባቢን ባህል፤ ኪነ-ጥበብን ለመጠበቅ፤ የአካባቢዉን ሰዉ አስተሳሰብ አመለካከት እንዲሁም ባህሉን ለትዉልዱ የሚያሻግርበት መድረክ እንዲኖር ነዉ የተሰባሰብ ነዉ። ይሄንኑ እያስቀጠልን እስካሁን ድረስ አለን። አዳዲስ ልጆች ይመጣሉ፤ መድረክ ይለምዳሉ፤ ከድሮዎቹ ልምድ እየወሰዱ ሥነ-ፅሑፍን እየተማሩ ወደ መድረኩ ይመጣሉ፤ ራሳቸዉንም በክህሎት የሚያዳብሩበት መድረክ ነዉ። ወደ ፊት በመድረክ ይዘናቸዉን የምንቀርባቸዉን ግጥሞችም ሆኑ ጽሑፎች በ«ሲዴ» ወይምበመጽሐፍ ለማሳተም ሃሳብ አለን።  

 

በጎንደር ከተማ የሥነ ጽሑፍ ዝንባሌ ያላቸዉ ወጣቶች ተሰባስበዉ ትርፍ ጊዜያቸዉን ሥነ- ግጥሞቻቸዉን ለሌሎች ለማካፈል የተለያየ መጠርያን ይዘዉ በግጥም ምሽት መድረክ ማሳለፍ ከጀመሩ ከ 10 ዓመት በላይ እንደሆን የሚናገረዉ ወጣት መክት ካሳሁን ነዉ።  ወጣት መክት እንደሚለዉ ገና ተማሪ ሳለ ጀምሮ በግጥም ምሽት እንዲሁም በሌሎች የሥነጽሑፍ ዝግጅቶች ላይ ተሳታፊ እንደነበር ይናገራል። በአሁኑ ሰዓት በጥብቅና እና በሕግ አማካሪነት ሞያ የሚተዳደረዉ ወጣት ካሳሁን ከ«አቦል ጥቦል» ጥበብ ምሽት መስራችም ነዉ።

«አቦል ጥበብ» በኪነ-ጥበብ ዝግጅቱ ላይ በተቻለ መጠን ባህላዊ ክንዋኔን ያሟላ እንዲሆን ከአልባሳት ጀምሮ ክትትል የሚያደርግ ስብስብ ነዉ። ለከተማዋም አስተዋጽዖ አብርክቶአል። መክት ካሳሁን በመቀጠል የሚከተለዉን አስተያየት ሰጥቆአል።

«ሌላዉ  ባህላዊ ክንዉኖችንም እናደርጋለን። አቦል ከስሙም አንፃር አገራዊ ይዘት ያለዉ ስለሆነ ሃገርኛ ቃና ስለሆነ በመረሃ-ግብራችን ላይ የባህል ልብሶች እንዲለበሱ እንመክራለን፤ አቀራረቦች አገርኛ ይዘት ያላቸዉ ናቸዉ ለተመልካች የሚቀርቡት። ከዚህ አንፃር ለከተማዉም ሆነ ለነዋሪዉ መነቃቃርን የፈጠረ ነዉ። በአገሪቱ በነበረዉ የለዉጥ ሄደት፤ በትግሉ ሰዓትም ስብስቡ የራሱ አስተዋፅኦ የነበረዉ ነዉ። ይህን ስል ዝግጅቱ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለለዉጥ የሚያነሳሱ የሚገፋፉ ሥነ-ጽሑፎች እና ግጥሞች የሚቀርቡበት መድረክ ነዉ። »  

   

የግጥም ስብስቡን የሚመሩት ሰዎች በሥራ ምክንያት ከአካባቢዉን ለቀዉ ሲሄዱ ስብስቡን የሚመራዉ እያጣ መቋረጡም ሆነ ለስም መቀያየሩ ሌላ ምክንያት እንደሆን ጋዜጠኛ ፍቅርአዲስ ገልፃለች። ስብስቡ አደረጃጀት ጠንካራ ባለመሆኑ የሥነ- ጥበባዊዉ መድረክ ጠንካራ መሸጋገርያ ድልድይ ስላልነበረዉ ሌላ አዲስ መስራች መጥቶ እስኪመሰርተዉ ለተደጋጋሚ ጊዜ ተቋርጦ መቆየቱን አክላለች። ጥበብ ለአንድ ማኅበረሰብ ማስተዋያ ማያ መሆኑንም ትገልፃለች።  

«ጥበብ ለኔ እይታ ነዉ። በሌላ መንገድ ሲተረጎም ደግሞ የአንድ ማኅበረሰብ ፍልስፍና አስተሳሰብ እዉቀትና ክህሎት ለሰዉ የምታሳይበት ከተቻለ ደግሞ የማኅበረሰቡን ሕፀጽ የምትነቅሽበት ነዉ። ጥሩ የሆነ ባህልና እሴትን የምታስተዋዉቂበት ይበል ይቀጥል የሚባልበትም ነዉ።  ማኅበረሰቡን የሚጎዱ ነገሮች ሲፈፀሙ ደግሞ እንዲህ አይደረግም የምንልበት መሳርያም ነዉ። » 

ኪነ-ጥበብ ለማኅበረሰብ ቁልፍ መሳርያ እስከሆነ ድረስ ክህሎት ያላቸዉ ሴቶች በተሳትፎ እንዲሁም በታዳሚነት ቢገኙም ከቤተሰብ ጀምሮ ለአካባቢያቸዉ ብሎም ለሃገር ከፍተኛ ጥቅምን ሊያገኙ እንደሚችሉ ገልፃለች። እንደ ወጣትዋ ጋዜጠኛ ፍቅር አዲስ ፤ በዚህ የኪነ-ጥበብ ስብስብ ዉስጥ ተሳታፊ ሴቶችም ሆነ ከዝግጅቱ ታዳሚዎች መካከል በጣም ጥቂቶቹ ብቻ ሴቶች መሆናቸዉን ተናግራለች።  ይህ የሆነዉ ምናልባት ከቆየ ልማድ አልያም ከአጉል ባህል የመጣ ነዉ።   

« ይህ ብዙ ጥናት የሚያስፈልገዉ ይመስለኛል። ግን በኔ አመለካከት አስተዳደጋችን ራሱ ወደ ቤት እንጂ ወደ ዉጭ የሚጋብዝ ስላልሆነ እና ወደ ዉጭ የምናልባትም ምንም አይነት ስርአት ስለሌለ ነዉ ወጣ ወጣ ስትይም ከባህል እንደወጣሽ ነዉ የሚታየዉ እንደዉም አብዛኛዉን ጊዜ « ይህች ልጅ ተንቀለቀለች እንደሴት አርፋ አትቀመጥም ነዉ » የሚባለዉ። ይህ ማለት ማኅበረሰቡ ቀርጾ ባሳደገን መልኩ ነዉ የኛም ርምጃ ፤ በዚህ ምክንያት ይመስለኛል በኪነ-ጥበብ መድረክ ለመሳተፍ አልያም ለመታደም የማይመጡት። እነዚህ ወደዚህ የኪነ-ጥበብ መድረክ የማይመጡት ሴቶች ግን የእዉቀት አልያም የገንዘም እጥረት ኖሮባቸዉ አይደለም የማይመጡት።  ይህ ሁሉ የአስተዳደግ የመጣንበት የባህላዊ እና የማኅበራዊ ኑሮ ስርዓት ያመጣዉ ተፅእኖ ይመስለኛል።     

   

በሸኘነዉ በ 2010 ይሆናል ብለን ያላሰብነዉን የለዉጥ ጭላንጭ ል አይተን አዲሱን 2011 ዓመት ተቀብለናል፤ ያለችዉ ወጣት ፍቅርአዲስ፤ ኢትዮጵያ ላይ የነፈሰዉ የአንድነት የለዉጥ ንፍስ ወደኃላም ወደፊትም የመሄድ እድል አለዉና የኪነ-ጥበብ ሰዎች ለአንድነት ለፍቅር ብሎም ለአንድ ኢትዮጵያ መስራት እንደሚጠበቅባቸዉ ተናግራለች።  

« በ 2010 በጣም ብዙ ለዉጥ የሚመስሉ ንፋሶች ያየንበት ነዉ። በርግጥ ለዉጥ መምጣት አለመምጣቱን የምንወስነዉ ወደፊት ነዉ። ኢትዮጵያን ወይ ወደ ኋላ አልያም ወደፊት የሚወስዳት በጣም ወሳኝ ቦታ ላይ የተቀመጥንበት ጊዜ ይመስለኛል። የአንድነት ነፋሱ እንዳለ ሆኖ በጣም አስጊ የሆኑ እየሄድንባቸዉ ያሉ ነገሮች አስፈሪ ሆነዉ እየታዩ ነዉ። ለሃገሪቱ አንድነት ለፍቅር ለተሻለ ነገር ፤ የጥበብ ሰዎች የመፍትሄ ሃሳብ ማምጣት መጀመር አለባቸዉ።  አዲስ ዓመት ሲመጣ አዲስ ነገር ይጠበቃል እና አዲስ ነገር እናያለን ብዬ አስባለሁ። »

በመጨረሻ ሳልጠይቅሽ የማማላልፈዉ ነገር አዲስ ዓመት እንዴት አለፈ ጎንደር ከተማ አዲስ ዓመትን እንዴት ተቀበለችዉ?

« ጎንደር እንደሚታወቀዉ በጣም ብዙ የጎንደር ተወላጆች ከሃገር ዉጭ ነዉ የሚኖሩት። የዚህን ዓመት አዲስ ዓመት ለማክበር በጣም ብዙ ሰዎች ከዉጭ ሃገር መጥተዋል። አከባበሩ በጣም ደማቅ ነበር። እንደኔ ነዋሪዉ በተለይ ሁኔታ ነዉ ያከበረዉ ብዬ  መናገር እችላለሁ። አዝማሪ ቤቶች ሙዚቃ ቤቶች ከአፍ እስከጢማቸዉ ሞልተዉ ነበር። ድባቡ ደስ ይል ነበር።»  

በጥብቅና እና በሕግ አማካሪነት ሞያ የሚተዳደረዉ ወጣት መክት ካሳሁን እንዳለዉ በጥበብ ዝግጅቱ ላይ በተቻለ መጠን ባህላዊ ዝግጅትን ያሟላ እንዲሆን ከአልባሳት ጀምሮ ክትትል የሚያደርግ ስብስብ ነዉ፤ ለከተማዋም አስተዋፅኦ አበርክቶአል።

«አቦል ጥበብ» በአዲሱ 2011 ዓመት የመጀመርያ ዝግጅቱን ነገ አርብ መስከረም አራት ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል ጎንደር ከተማ «ቆብ አስጥል የባህል አዳራሽ» ደማቅ ዝግጅቱን ይዞ የጥበብ አፍቃሪዉን እንደሚጠብቅ አዘጋጆቹ ወጣቶች ተናግረዋል። ቃለ-መልልስ የሰጡንን በጎንደር ከተማ የአቦል ጥበብ ኪነጥበብ መድረክ አዘጋጆችን እያመሰገንን ፤ ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን ።  

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች