«አብን» በክልሉ የተፈፀመዉን ግድያ አሳዣኝ ሲል በፅኑ አወገዘ | ኢትዮጵያ | DW | 24.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

«አብን» በክልሉ የተፈፀመዉን ግድያ አሳዣኝ ሲል በፅኑ አወገዘ

የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ክርስቲያን ታደለ እንደሚሉት ፓርቲያቸው ግድያው በትክክል ተጣርቶ ምክንያቱ በግልጽ እስካልታወቀ ድረስ የፌደራል መንግሥት እና አንዳንድ ያሏቸው ወገኖች የሚያሠራጩት ዘገባ የችኮላ ወይም ሆን ተብሎ የሚደረግ ነው ብሎ ያምናል

በአማራ ክልል የሚንቀሳቀሰው የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ /አብን/ ባለፈው ቅዳሜ ባህርዳር እና በአዲስ አበባ ውስጥ የደረሰውን ግድያ አወገዘ። ለሟች ቤተሰቦችም ሀዘኑን ገለጸ። ግድያና ሴራው መንግሥት እንዳለው መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ነው ብሎ እንደማያምን ፓርቲ አስታውቋል። /አብን/ ባለፈዉ ቅዳሜ ምሽት በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር አምባቸዉ መኮንንና በሌሎች የክልሉ ባለስልጣናት የተደረገዉ ግድያ አሳዣኝ ሲል በፅኑ አወገዘ። የአብን ቃል አቀባይ አቶ ክርስቲያን ታደለ በተለይ  ለዶይቼ ቬለ  «DW»  «በወንድሞቻችን ላይ የተፈፀመዉ ግድያ በግለሰብ አመራሮች ላይ የተፈፀመ ብቻ ሳይሆን በመላዉ የአማራ ህዝብ ላይ የተፈፀመ ነዉ» ብለዋል።
« ይህ ግድያ ግለሰብ አመራሮች ላይ ሳይሆን የአማራ ሕዝብ ላይ በሁላችንም ላይ የተፈፀመ ግድያ አድርገን የምንቆጥረዉ መሆኑን መግለፅ እፈልጋለሁ። ከዚህ ጋር ተያይዞ መንግሥት በተለያዩ መግለጫዎቹ መፈንቀለ መንግሥት እንደተካሄደ አድርጎ መግለጫዎችን እየለቀቀ ነዉ፤ ወንድሞቻችንን ገድለዉ በእኛዉ ወንድሞች ሞት መሞሸር የሚፈልጉ የጠላት ኃይሎች የተለያየ መረጃ በመልቀቅ በአማራዉ መካከል ያለዉን ዉስጣዉ አንድነት ለመቦርቦርና ለመሸርሸር የተለያየ መረጃ ሊለቁ ይችላሉ። መንግስት በቂ ጊዜ ወስዶ የወንጀሉን ምንጭ እና ሰንሰለት የማጥናት በቂ የሆነ መረጃ ተገኝቶአል ብሎ በትክክለኛ ጊዜ የመልቀቅ ሃላፊነት የሚሰማዉ የመንግሥት ርምጃ ነዉ ብለን እናስባለን።»  
 እንደ አቶ ክርስቲያን ከክልሉ አመራሮች መካከል ጥሩ ይሰራሉ የተባሉ አመራሮችን ነጥሎ መግደል በክልሉ ህዝብ መካከል ያለዉን አንድነት ለመሸርሽር የታሰበ ይመስላል። በፌደራል መንግስት በኩልም ድርጊቱን በችኮላ «መፈንቅለ መንግስት ነዉ»  ከማለት ይልቅ ጉዳዩን ጊዜ ወስዶ በጥልቀት በመርመር የወንጀል ሰንሰለቱን የፀጥታ ሀይሎች እንዲያጣሩት ቢደረግ የተሻለ እንደነበር አብራርተዋል።ፓርቲያቸዉ በጉዳዩ ላይ በቂ መረጃ ለማግኜት ማጣራት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል። አብን ከክልሉ ገዥ ፓርቲ አዴፓ ጋር እንዲሁም ከሀይማኖት አባቶችና ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር በመሆንም የክልሉን ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ለመጠበቅ እንደሚሰራ አቶ ክርስቲያን ገልፀዋል። የፌደራል መንግስት  የክልሉን የፀጥታ ሁኔታ ለማረጋጋት በሚል የፌደራል የፀጥታ ሀይሎችን በመላክ የክልሉን መንግስታዊ መዋቅርና የፀጥታ ሀይል እንዳይጋፋ ጥንቃቄ ሊያዸርግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።ቃል አቀባዩ ግድያዉ ለተፈፀመባቸዉ ወገኖች የተሰማቸዉን ሀዘን ገልፀዉ ለቤተሰቦቻቸዉም መፅናናትን ተመኝተዋል። ነጋሽ መሐመድ የአብን ቃል አቀባይ አቶ ክርስቲያን ታደለን በስልክ አነጋግሮአቸዋል።  


ነጋሽ መሐመድ 
ኂሩት መለሰ
 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች