አብራሪ አልባ አውሮፕላን ጥቃትና አሸባብ | አፍሪቃ | DW | 16.03.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አብራሪ አልባ አውሮፕላን ጥቃትና አሸባብ

የዩኤስ አሜሪካ አብራሪ አልባ አውሮፕላኖች በኬንያ የዌስት ጌት የገበያ ማዕከል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ባሉት የአሸባብ አመራር ላይ ጥቃት ፈጸሙ። በጥቃቱ የአሸባቡ መሪ መሞቱን የዜና ወኪሎች ቢዘግቡም: ዜናው እስካሁን በይፋ አልተረጋገጠም።

የአሜሪካን ጦር ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ሐሙስ የአሸባብ ከፍተኛ አመራርን በአብራሪ አልባ አውሮፕላን ጥቃት ሳይገድሉ እንዳልቀረ አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል። ከሌሎች ሁለት የአሸባብ ታጣቂ ቡድን አባላት ጋር በመኪና ጉዞ ላይ የነበረው አዳን ጋራር የተባለ የአሸባብ አመራር የጥቃቱ ዒላማ ነው ተብሏል። ጥቃቱን የፈጸሙት የአሜሪካን ጦር አባላትም ይሁኑ የሶማልያ መንግስት እስካሁን በጉዳዩ ላይ በይፋ መግለጫ አልሰጡም። አንድሪውስ አታ አሳሞሃ በጸጥታ ጥናት ተቋም የደቡብ አፍሪቃ ቢሮ ተንታኝ ናቸው።

«አሁን የምናውቀው አዳን ጋራር የተባለው ግለሰብ የጥቃቱ ዒላማ እንደነበር ነው። አዳን ጋራር ናይሮቢ የዌስት ጌት የገበያ ማዕከል የተፈጸመውንና 67 ሰዎች የተገደሉበትን ጥቃት ያቀነባበረ ሰው ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኬንያ እና በሌሎች የምስራቅ አፍሪቃ የተፈጸሙ እና የከሸፉ ጥቃቶችን የሚያስተባብር የአሸባብ ቁልፍ አመራር ነው።»

የአሜሪካን ጦር ከመስከረም ወር ጀምሮ በአሸባብ ላይ ጥቃት ሲፈጽም ይህ አራተኛ መሆኑ ነው። ዩ.ኤስ. አሜሪካ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1993 ዓ.ም. በሶማልያ ሁለት የጦር ሄሊኮፕተሮች ተመተው ከወደቁ እና 18 ወታደሮች ከሞቱ በኋላ እግረኛ ጦር ለማዝመት ፈቃደኛ አትመስልም። ቢሆንም በጅቡቲ ከሚገኘው ሌሞኒየር የጦር ሰፈሯ እና በኢትዮጵያ ከሚገኝ አነስተኛ የአውሮፕላን ማረፊያ በመነሳት ሶማሊያን ትሰልላለች። የጸጥታ ተንታኙ አንድሪውስ አሳሞሃ የአብራሪ አልባ አውሮፕላኖቹ ጥቃት የአሸባብን አመራር ዒላማ በማድረጋቸው ታጣቂ ቡድኑን ማዳከሙን ያስረዳሉ።

«እስካሁን ከተደረጉት ጥቃቶች መካከል አህመድ ጎዳኔን ዒላማ አድርገው ተሳክቶላቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው የአሸባብ አመራሮች ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል። የአሜሪካ አብራሪ አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት የአሸባብ ከፍተኛ አመራሮች ላይ ዒላማ ያደረገ አካሄድ ይከተላል። ይህም ዒላማዎቹን በማስወገድ የአሸባብን አደረጃጀት የማፈራረስ እና ቡድኑን የማዳከም እቅድ ነው። አህመድ ጎዳኔ ከተገደለ በኋላ እንኳ ቡድኑ ከፍተኛ የተቀባይነት ማጣት ገጥሞታል። ጥቃቶቹም እንደ ቀድሞው ስኬታማ መሆን አልቻሉም።»

እንደ አንድሪውስ አታ አሳሞሃ ገለጻ አሸባብ አህመድ ጎዳኔን በቀላሉ መተካት አልቻለም። ቡድኑም የጥቃት መንገዱን ሙሉ በሙሉ ቀይሮ ሽብር እና የደፈጣ ጥቃትን መምረጡን አሳሞሃ ተናግረዋል። ትናንት መጋቢት ስድስት እንኳ ኬንያ ከሶማልያ በምትዋሰንበት የማንዴራ ግዛት በተፈጸመ ጥቃት አንድ ሰው ሲገደል ሶስት ሰዎች መቁሰላቸውን አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ዘግቧል።አንድሪውስ አሳሞሃ በአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ «አሚሶም» እና የሶማልያ መንግስት ወታደሮች ከምድር፤ በአሜሪካ አብራሪ አልባ አውሮፕላኖች ከሰማይ ጥቃት የሚሰነዘርበት አሸባብ ዛሬም አስፈሪ መልክ እንዳለው ያምናሉ።

«ዛሬም ቢሆን አሸባብ በሶማልያ፤ኬንያ አልያም በቀጠናው ሃገራት አሰቃቂ ጥቃት ለመፈጸም ብዙ ሰው አያስፈልገውም። የቤት ውስጥ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን መስራት ይችላሉ። 'ኤ.ኬ. 47' በተባለው መሳሪያ አስከፊ ጥቃት መፈጸም ይችላሉ። ስለዚህ አሁንም አሸባብ ቀጠናውን የማተራመስ አቅም አለው።»

እሸቴ በቀለ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic