አብራሪ ለመኾን ብስኩት ሽያጭ | አፍሪቃ | DW | 21.03.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አብራሪ ለመኾን ብስኩት ሽያጭ

ሼፓንግ ራሌሆኮ በሚያበሩ ዐይኖቿ ሰማዩ ላይ ተክራለች። ሰማዩ ላይ አነስተኛዋ ሴስና አውሮፕላን እየበረረች ነው። አንድ ቀን እዚህች አውሮፕላን አብራሪ ክፍል ውስጥ መቀመጥ የልጅነት ምኞቷ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:53

ስትመኘው የነበረውን ሞያ ከግብ ልታደርስ ጫፍ ደርሳለች

የአውሮፕላን አብራሪነት ስልጠና እጅግ ብዙ ገንዘብ ያስወጣል። ያም በመኾኑ አያሌ ህጻናት የልጅነታቸው ሕልም መክኖ የሚቀርበት አጋጣሚ በርካታ ነው። ሼፓንግ ራሌሆኮ ግን ገና የአራት ዓመት ህጻን ልጅ ሳለች ጀምሮ ታልመው የነበረውን ከግቡ ለማድረስ እየተጣጣረች ነው። በትርፍ ጊዜዋ ብስኩቶችን እና ኬኮችን እየጋገረች በመሸጥ የማይኾን ይመስል የነበረውን ግን ዕውን እንዲኾን ልታደርግ ነው። ከአክስቷ ጋር ለወራት ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰአት ብስኩቶችን እና ኬኮችን እየጋገሩ ምኞቷን አሳክታለች። እናም ብስኩት እና ኬኮቿን የሚገዙ በእጅ አዙር ስልጠናዋን አገዙ ማለት ነው። እናም የ23 ዓመቷ ወጣት በእርግጥም ከልጅነቷ አንስቶ ስትመኘው የነበረውን ሞያ ከግብ ልታደርስ ጫፍ ደርሳለች።

ሼፓንግ ራሌሆኮ በሚያበሩ ዐይኖቿ ሰማዩ ላይ ተክራለች። ሰማዩ ላይ አነስተኛዋ ሴስና አውሮፕላን እየበረረች ነው። አንድ ቀን እዚህች አውሮፕላን አብራሪ ክፍል ውስጥ መቀመጥ የልጅነት ምኞቷ ነው። የበረራ ትምህርት ቤቷ መለያ ልብስ ለብሳለች። በረዥሙ የተሠራችው ሹሩባዋ ጀርባዋ ላይ ተዘርግቷል። ከልጅነቷ አንስቶ ሕልሟ አንድ ቀን አውሮፕላን አብራሪ መኾን ነው።

«በዓለማችን ኹሉ ከሚገኙ ቢሮዎች ምርጡ እይታ ያለበት ነው። በመጀመሪያ አውሮፕላን አብራሪ ክፍል ውስጥ እንዳለው እይታ የሚኾን የለም። በዚያ ላይ አብዛኛውን ጊዜ ኹሉንም ነገር የምትቆጣጠረው አንተው ነህ። በቃ ዝም ብሎ በጣም ደስ የሚል ነው።»

ሼፓንግ ይኽን ሕልሟን ከ4 ዓመቷ አንስታ ላለፉት 20 ዓመታት ግድም ደጋግማ ሳታየው ነበር ማለት ይቻላል። ፕሪቶሪያ አቅራቢያ ከሚገኘው የመኖሪያ ከተማዋ አውሮፕላን ለማብረር እያለመች ነው እንደ እናቷ በምታያቸው አክስቷ ቤት ያደገችው። ከልብ የምትወዳቸው አክስቷ ገንዘብ የማይገዛውን ፍቅር እየለገሱ አሳድገዋታል። ያም ብቻ አይደለም። እማዬ ብላ ይምትጠራቸው አክስቷ ሕልሟ ዕውን እንዲኾን ከጎኗ ኾነው ደግፈዋታል። ሼፓንግ አውሮፕላን አብራሪነት መሰልጠን ከፍተኛ ወጪ እንዲሚያስጠይቅ አልጠፋትም፤ ግን ደግሞ መፍትኄውም አልተሰወራትም። ብስኩት እና ኬኮችን መጋገር ድሮም ጀምሮ ትወዳለች እና ቀጣዩን አሰበች። 

«እቤት እግሬን ዘርግቼ በመቀመጥ ዕድሌን ማማረር እንደሌለብኝ ወሰንኩ። ይልቊንስ ምኞቴን ለማሳካት መጣር እንዳለብኝ ውሳኔ ላይ ደረስኩ። እናም ለምን ብስኩት እና ኬክ መጋገር አልጀምር አልኩ። እናቴ ማእድ ቤት ውስጥ በጣም ጎበዝ ናት። ኹሉንም ነገር ከእሷ ነው የተማርኩት። ኬኮችን ጋግሬ በመሸጥ የሚኾነውን ማየት እፈልጋለሁ ብዬ ስነግራት ሙሉ በሙሉ ነው በሐሳቤ የተስማማችው። አብራሪ ለመኾን ማንኛውንም ነገር ማድረግ ነበረብኝ።»

የአብራሪነት ሕልሟን ዕውን ለማድረግም ዘወትር ሌሊት ዘጠኝ ሰአት ከአልጋዋ መነሳት አለባት። ተነስታም ኬኮችን ትጋግራለች። ኬኮቹን እየሸጠች የምታገኘውን ገቢም የአውሮፕላን አብራሪነት ሞያንለመሰልጠን በትጋት ታጠራቅማለች። የ23 ዓመቷ ደቡብ አፍሪቃዊት ምን ማድረግ እንዳለባት እና የት መድረስ እንደሚገባት ጠንቅቃ ታውቃለች። የግል አውሮፕላን አብራሪነት ፈቃድ ለማግኘት መንገዱን ጀምራዋለች። ከኹለት ዓመት በኋላ የንግድ አውሮፕላን በረራ ፈቃድ አገናለሁ ብላም ነው የምትተጋው። ዋና ሕልሟ የበረራ ሰአቶችን ሰብስባ በስተመጨረሻ ሙሉ ለሙሉ አውሮፕላን መኾን ነው። 

«ለብዙዎች ትልቊ ሕልም ኤርባስ አለይም ቦይንግ አውሮፕላኖችን ማብረር ነው። እኔ ራሴ ትልቅ አውሮፕላን ጣቢያ ብሠራ ደስ ይለኛል፤ አውሮጳ ውስጥ በሚገኝ የበረራ ጣቢያ እሠራለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ኤርባስ 737 እና 747ን ማብረር እፈልጋለሁ።»

የምንጓዘው ከጆሐንስበርግ ወደ ፍራንክፉርት ነው፤ አብራሪያችሁ ሼፔንግ ራሌሆኮ ነኝ የሚለውን ድምጽ ከአውሮፕላን አብራሪ ክፍል ለመንገደኞች የምታሰማበትን ቀን እንደናፈቀች ነው። ሼፔንግ ኬክ እና ብስኩቶቹን እየሸጠች ራሷን በመደገፍ እስካኹን የአንድ ዓመት የበረራ ስልጠናዋን አጠናቃለች። የረዥም ዘመን እቅዷ ግቡን ከመታ ከደቡብ አፍሪቃ ጥቂት ሴት አብራሪዎች አንዷ ትኾናለች። ሼፔንግ ይህ ሕልሟ አንድ ቀን ዕውን ይኾንና እዚህ ያደረሷትን ኬኮች እና ብስኩቶችም ለአውሮፕላን ተሳፋሪዎቿ ማደሏ ሩቅ እንደማይኾን እየቀለደች ተናግራለች። ከቀልዷ ባሻገር ግን ሴስና አውሮፕላን ላይ ተሳፍራ አየሩን ለመቅዘፍ የመጓጓት ቊርጠኝነቷ ይነበባል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ ያና ጌንት

 

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች