አባይ፤ ኢትዮጵያ እና ግብፅ | አፍሪቃ | DW | 20.02.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አባይ፤ ኢትዮጵያ እና ግብፅ

የአባይ ወንዝ ውሃን በመጠቀሙ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያና ግብጽ መካከል የነበረው የኃይል ሚዛን ወደ ኢትዮጵያ እያደላ መሆኑ ተነግሯ። ግብጽ ከአባይ ወንዝ የምታገኘውን ጥቅም ማጣት አትፈልግም። የኢትዮጵያና ግብጽ ፍጥጫ ምሥራቅ አፍሪቃን ይበልጡን ያልተረጋጋ አካባቢ እንዳያደርገው ያሰጋል።

The Blue Nile falls are known in the Amharic language as Tis Isat (the water that smokes). +++CC/Mark Abel+++ am 10.2010 aufgenommen am 01.2011 hochgeladen Lizenz: http://creativecommons.org/licenses/by-nc-sa/2.0/deed.de http://www.flickr.com/photos/markabel/5174843555/

ከሰላሳ አምስት ዓመታት በኋላ የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት ህዝቦች ከስምንት መቶ ሚሊዮን በላይ እንደሚሆኑ በቅርቡ በጀርመን የሳይንስና ፖሊሲ ጥናት ተቋም የወጣ አንድ ጥናታዊ ጽሁፍ አመልክቷል። የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራትም የሕዝቦቻቸውን የውሃ፣ የምግብና የኃይል ፍጆታ ማሟላት ስላለባቸው፣ የአባይ ወንዝና የኢትዮጵያ ተፈላጊነት ከመቼውም በላይ እየጨመረ ሄዷል ይላሉ በተቋሙ የሚሰሩ ተመራማሪ ቶቢያስ ፎን ሎሶቭ። በአባይ ወንዝ ላይ ለዘመናት በቆየው የግብጽ የበላይነት ላይ በወቅቱ ለውጥ እየታየበት ያለው ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው የኢኮኖሚ እድገት ባስገኝው ለውጥ ነው ይላሉ ሚስተር ቶቢያስ ሎሶቭ፣

«ከጥቂት ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ በግልጽ እድገት እያሳየች ነው። አዲሷ የኢትዮጵያ አጋር ቻይናም ኢትዮጵያ የውሃ ሐብቷን የመጠቀም ግቧን በይበልጥ እንድታስፈጽም እየረዳቻት ነው። እኚህ ሁለት ምክንያቶች ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶቹን እንድታቅድና እንድታስፈጽም ያስችሏታል። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ እንዲህ ላሉ ፕሮጀክቶች በቂ ገንዘብ ይጎድላት ነበር።»

ሎሶቭ እንዳስረዱት፣ ኢትዮጵያ በኢኮኖሚው ብቻ ሳይሆን በፖሊቲካውም ዘርፍ በምሥራቅ አፍሪቃ ዋና ተዋናይ ሆናለች። ሰላም አስከባሪ ኃይሎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ እንዲሁም በዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪቃን በመወከል የተጫወተችው ሚና የሀገሪቷን አስፈላጊነት አጉልቶዋል። ሽብርተኝነትን በመከላከሉ ተግባርም ላይ ኢትዮጵያ ከምዕራብ ሀገራት ጎን ትሰራለች። ግብጽም ብትሆን ከአረቡ አብዮት በኋላ በተፈጠረው አለመረጋጋት በምሥራቅ አፍሪቃ የነበራት የፖሊቲካ ተፅዕኖ ቀንሷል። በአባይ ወንዝ አጠቃቀም ንትርክ ላይ ብዙውን ጊዜ ከግብጽ ጎን የምትቆመው ሱዳንም ከደቡብ ሱዳን ጋር ባለው ውዝግብ እና በዳርፉር ግጭት የተነሳ ይዛው የነበረው ሚና እየቀነሰ መጥቶዋል።

የውሃ ፍላጎት መጨመር፣ የኢኮኖሚ እና የፖሊቲካዊ እድገቶች ኢትዮጵያ ዓላማዋን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንድታራምድ አስችሏታል። ሰባ አምስት በመቶ የውሃ አቅርቦቷን ከአባይ የምታገኘው ግብጽ ይህን አካሄድ እንደ ቀላል ስለማትመለከተው፣ በዚሁ ረገድ የምትከተለው ማንኛውም ፖሊሲ ምሥራቅ አፍሪቃን የበለጠ እንዳትረጋጋ ሊያደርግ እንደሚችል ሚስተር ሎሶቭ ይገምታሉ።

« በአባይ ውሃ ሰበብ ቢያንስ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት እየታየ ያለው ውዝግብ፣ በተለይም በኢትዮጵያ ግብጽ መካከል አዲስ ውጥረትን ማስከተሉ አይቀርም። ይህ ደግሞ አከባቢው ይበልጡኑ እንዳይረጋጋ ያደርገዋል። ውዝግቡ ወደ ለየለት ጦርነት የሚያመራ አይመስልም። ነገር ግን ውጥረቱ ለአከባቢው አለመረጋጋት የበኩሉን ድርሻ ያበረክታል።»

ሰማኒያ በመቶ የአባይ ውሃ የሚፈሰው ከኢትዮጵያ ቢሆንም ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነውን የምትጠቀመው ግብጽ ናት። የግብጽ ህልውና የተመሰረተው በአባይ ወንዝ ላይ ነው። ኢትዮጵያም ብትሆን ከምድሯ የሚፈሰውን ውሃ መጠቀም ትፈልጋለች። ሁለቱን ፍላጎቶች ማስታረቅ የሚቻለው በተለይ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ትብብር ሲኖር ነው እንደ ሚስትር ቶቢያስ ፎን ሎሶቭ አስተያየት፣

«እኔን የሚታየኝ አንዱ መፍትሔ በዋና ሀገራት ማለትም በኢትዮጵያ፣ በግብጽ እንዲሁም በሱዳን መካከል የኃይሉን ምንጭ፣ የኢኮኖሚውን ፣ እንዲሁም የቴክኒካዊውን ዘርፎች በተመለከተ የሚኖረው ትብብር ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ግብጽ ፍላጎታቸውን ሁሉ ሊያሟሉ የሚችሉት በቴክኒካዊ መፍትሔዎች ላይ አብረው ሲሰሩ ነው።»

የምሥራቅ አፍሪቃ ሀገራት የአባይ ተፋሰስ ሀገራት የስምምነት እቅድ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈልጋሉ፣ ይህ ሊሆን የሚችለው ግን ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት መስማማት ሲችሉ መሆኑን ሚስተር ሎሶቭ አስረድተዋል። ሆኖም በወቅቱ ሁሉንም ሀገራት ያቀፈ ስምምነት ሳይሆን በሀገራት መካከል የሚደረግ ስምምነት ትኩረት ማግኘት እንደሚገባ ይነገራል። እንደ ሚስተር ሎሶቭ አስተሳሰብ፣ ለምሳሌ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል የሚደረግ ስምምነት የጋራ የኃይል ገበያና የጋራ የመስኖ እርሻ ፕሮክቶችን ማጠቃለል ይችላል። እና ምሥራቃውያን በዚህ ዘርፍ ትብብራቸውን ማሳየት አለባቸው።

ግብጽ ዛሬም እአአ በ1929 የተፈረመው የቅኝ ግዛት ስምምነት ቀጣይነት እንዲኖረው ነው የምትፈልገው። ሱዳንም ብትሆን እአአ በ1959 በግብጽና ሱዳን የተፈረመው የአባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነት እንዲቆይ ትፈልጋለች። ሌሎች የአባይ ተፋሰስ ሀገራት ግን የስምምነቶቹ አካል አልነበሩም። እአአ በ1999 የአባይ ዉሃን በፍትሐዊ መንገድ ለመጠቀም፣ ሁሉን የአባይ ተፋሰስ ሀገራትን ያጠቃለለ ስምምነት ለመድረስ የሚረዳ አንድ እቅድ ቢቀርብም ግብጽና ሱዳን እቅዱን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም።

ገመቹ በቀለ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic