አባይን በሙዚቃ | ጤና እና አካባቢ | DW | 05.07.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

አባይን በሙዚቃ

11 የአፍሪቃ ሃገራትን የሚያቋርጠዉ የአባይ ወንዝ ከዓለም ረዥም መንገድ የሚጓዝ ትልቅ ወንዝ ነዉ። በአባይ ተፋሰስ አካባቢዎች ዉኃ መሠረታዊ ጥሬ ሐብት ነዉ። ነገር ግን የተለያዩ ሃገራት ዉኃዉን እኩል ተጋርተዉ እንዳይኖሩ የፖለቲካ ጨዋታዉ ትልቁን ሚና ይዟል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:07

የአባይ ፕሮጀክት

ዘ ናይል ፕሮጀክት ወይንም የአባይ ፕሮጀክት የተሰኘ አንድ መርሃግብር ሙዚቃን መሣሪያ በማድረግ በአባይ ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ ሃገራት መካከል የተረጋጋ መግባባት እንዲፈጠር የማድረግ ዓላማ ይዞ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል።

«የናይል ፕሪጀክትን ከአምስት ዓመታት በፊት ነዉ የጀመርነዉ። በ2011ዓ,ም ከ11 የአባይ ተፋሰስ ሃገራት የሙዚቃ ሰዎችን አስተባብረን አብዛኞቹን እነዚህ ሃገራት የሚያቀራርብ ሙዚቃ መሥራት ጀመርን። ይህን ሙዚቃ በመጠቀምም ስለአባይ ተግዳሮቶች፤ እንደዜጋ እኛ ስለሚኖረን ሚና እንዲሁም ሲቪሉ ማኅበረሰብ ለተግዳሮቶቹ መፍትሄ ስለሚያፈላልግበት መንገድ የሚያመላክት ዉይይት መክፈት ነዉ።»

ሚና ጊርጊስ ግብፃዊ ነዉ። ግብፅ ዉስጥ ዋናዉ የዉኃ ምንጭ አባይ ነዉ። የሙዚቃ ባለሙያ የሆነዉ ሚና ጊርጊስ የሙዚቃዎቹ አዘጋጅና የናይል ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ ነዉ።

ትዉልደ ኢትዮጵያዊዉ አሜሪካዊ የሳክስፎን ተጫዋች ዳኒ መኮንን የፕሮጀክቱ የሙዚቃ ዳይሬክተር ነዉ። እሱ እንደሚለዉ የአባይ ተፋሰስ በተፈጥሮ አካባቢዉ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካዉም ዉስብስብ ስነምህዳር ያለዉ አካባቢ ነዉ።

«በተለይ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብፅ ስለዉኃዉ ባለቤትነትም ሆነ በዉኃ ምክንያት ስለሚመጣዉ ግጭት በአግባቡ ያዉቃሉ ብዬ አስባለሁ። ይህ ደግሞ ከአባይ ዉኃ የአንበሳዉን ድርሻ ለግብፅ ገጸበረከት አድርጎ ከሰጠዉ በ20ኛዉ ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ከተፈረመዉ የአባይ ዉኃ ድርሻ ዉል አንስቶ የሚታይ ነዉ።

አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ግድብ እየተገነባ ነዉ፤ ይህ ደግሞ አወዛጋቢ ነዉ። አካባቢዉ 400 ሚሊየን ሕዝብ የሚኖርበት ሰፊ ስፍራ ነዉ። ስለዚህ የሚያወላዳ ነገር የለም፤ ዉኃዉ በእኩልነት የተከፋፈለ አይደለም።»

የአባይ ዉኃ በአካባቢዉ ለሚገኙ ሃገራት ደረጃዉ ይለያል እንጅ እጅግ አስፈላጊ ሐብት ነዉ። እንደግብፅ ባሉት ሃገራት ሕዝቡ የአባይ ውኃ ከየት እንደሚመጣ የሚያዉቀዉ ነገር የለም። ግብፃዊዉ ጊርጊስ እንደሚለዉ አንድ የሚያዉቀዉ ነገር ግን አለ፤ ይኸዉም የአባይ ዉኃ የሀገሪቱ ሕይወት ድርና ማግ ነዉ።

«በአባይ ወንዝ ዳርቻ እንደ አደገ እንደማንኛዉ ግብፃዊ በየዕለቱ ወንዙን እንሻገራለን። ነገር ግን ዉኃዉ ከየት እንደሚመጣ በዉኃዉ ላይ ጥያቄ እስከተነሳበት ጊዜ ድረስ አስበን አናዉቅም። እንደሌሎች መሰል ወገኖቼ አባይ ከየትኛዉ ሀገር ተነስቶ ወደእኛ እንደሚፈስ፣ የመልክዓምድሩን ገፅታ፣ ያጠላበትን አካባቢያዉ ተፅዕኖና የመሳሰሉትን ይህን ጉዳይ መመርመር ከመጀመሬ በፊት አላዉቅም ነበር።»

ኬንያ ዉስጥ ያለዉ ደግሞ የተለየ ሁኔታ ነዉ። ካሲቫ ሙቱአ በናይል ፕሮጀክት ዉስጥ የምትጫወተዉ ሚና ጥንቃቄ የተሞላበት ነዉ። በሀገሯ ግሩም ከሚባሉት ጃዝ ተጫዋቾች አንዷ ስትሆን በዚህ የሙዚያ መሣሪያ ጨዋታ ዘርፍ ከተሳካላቸዉ ባለሙያዎች አንዷ ናት።

«ኬንያዉያን ራሳቸዉን የአባይ ተፋሰስ ሃገራት አካል አድርገዉ አያዩም። በግሌም ሦስት ወይም አራት ሃገራት የሚጋሩት የቪክቶሪያ ሐይቅ የአባይ ወንዝ ዋነኛ አካል መሆኑን በፍፁም አላዉቅም ነበር። ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ እንዲሁም ኮንጎ ስለአባይ ወንዝ ስናወራ ልናነሳቸዉ የሚገባ ሃገራት ናቸዉ። ምክንያቱም ከእዉነተኛ ምንጮቹ አንዱ የሚመነጨዉ ቡሩንዲ ዉስጥ ሲሆን ለዚህ ዉኃ መገኘት ትልቅ ሚና ይጫወታል። ከዚያም ወደ ኢትዮጵያ ይሄድና ከጥቁር አባይ ተጨማሪ ዉኃ ይሰበስባል። ከዚያም ጥቁር እና ነጩ አባይ አንድ ላይ ሆነዉ ወደ ግብፅ ይፈሳሉ። በዚህ ፕሮጀክት ዉስጥ ከገባሁ በኋላ ነዉ ስለ አባይ የነበረኝ አመለካከት በሙሉ የተቀየረዉ።»

ይህ ፕሮጀክት ሰዎች የአባይ ዉኃ ከሌሎች ጋር ሊጋሩት የሚገባ የተፈጥሮ ሐብት መሆኑን አስተዉለዉ ሰዎች የሚገባቸዉን እንዲያደርጉ ማበረታታት ዋና ዓላማዉ እንደሆነ የሚናገረዉ ደግሞ ዳኒ መኮንን ነዉ።

«እኛ በ11ዱም የአባይ ተፋሰስ ሃገራት የሚኖሩት ሕዝቦች የሆነ የጋራ ዜግነት ስሜት እንዲሰማቸዉ ለማድረግ ነዉ የምንሞክረዉ። እናም ይህን ማድረግ ከምንጠቀምባቸዉ መንገዶች አንዱ ደግሞ በሙዚቃ የምናደርገዉ ትብብር ነዉ።»

በዓለማችን የተከሰተዉን የአየር ንብረት ለዉጥ ተፅዕኖ በአሁኑ ወቅት በመጋፈጥ ላይ ካሉት መካከል አፍሪቃ አንዷ ናት። ካሲቫ ሙቱአ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የሙቀት መጠኗ እየጨመረ ለሄደዉ ዓለማችን አባባሽ ምክንያቶችን በየፊናዉ የሚያደርገዉ የመቆጣጠር ርምጃ ካልተሳካ የአፍሪቃ የወደፊት ዕጣ ምን ሊሆን ይችላል የሚለዉ እንደሚያሳስባት ትናገራለች።

«የአየር ንብረት ለዉጥ የሚያስከትለዉን በርካት ተጽዕኖ ተመልክቻለሁ። እያንዳንዱ ሰዉ የተባባሰዉ የሙቀት ሁኔታ ይሰማዋል። ወቅቶች ወትሮ የነበራቸዉ ገጽታ ተቀይሯል፤ ትንሽ ልጅ ሳለሁ ሰኔ እና ሐምሌ ወር ላይ ናይሮቢ በጣም ይቀዘቅዝ ነበር። አሁን ግን እንዲህ አይደለም። አሁን ለምሳሌ ፀሐይ ነዉ። ይህ ደግሞ ግራ ያጋባል። አንድ የተሳሳተ ነገር መኖሩንም ያመላክታል።»

በአባይ ተፋፈስ አካባቢ ሚና ጊርጊስ እንደሚለዉ ወትሮም የነበረዉን ችግር የአየር ንብረት ለዉጡ አባብሶታል። ይህም በዉኃዉ ድርሻ ምክንያት እንደሚፈጠር የሚሰጋዉ ግጭት የማይቀር የሕልዉና ጥያቄ አድርጎታል።

«በግብፁ የአባይ ዴልታ አካባቢ የሚታየዉ የዉቅያኖስ ዉኃ መጨመር የአየር ንብረት ለዉጥ ግልፅ ተፅዕኖ ነዉ። አንዳንዶቹም በአባይ ተፋሰስ አካባቢ የሚታዩት የዚሁ ተፅዕኖ ዉጤቶች አሁንም ምንነታቸዉ ያልተገለጸ ስጋቶች ናቸዉ። የአየር ንብረት ለዉጡ ብዙ ወይም ጥቂት ዉኃ ማምጣት አለማምጣቱን ገና አናዉቅም። ስለዚህ የአየር ንብረት ለዉጥ የሚኖረዉ ተፅዕኖ ከግምት አስገብቶ ሲታይ እነዚህ ሃገራት በፍትሃዊነት ለማግኘት የሚመኙት የዉኃ መጠን ትልቅ ጥያቄ ላይ ወድቋል።»

እሱ እንደሚያምነዉ ደግሞ ለዚህ መንግሥት ብቻዉን መፍትሄ መፈለግም ሆነ ማምጣት አይችልም።

«ለዚህ የግድ ግልጽ የሆነ መዋቅር ሊኖረን ይገባል፤ መንግሥት ብቻ ወይም ደግሞ አንድ ብቸኛ ተዋናይ የሚያደርገዉ ነገር አይኖርም፤ በየደረጃዉ የተለያዩ ባለድርሻዎች ሊኖሩ ይገባል። የየሃገራቱ ዜጎች፣ የግሉ ዘርፍ እና ሲቪል ማኅበረሰቡ ለዚህ ትርጉም ያለዉ ትልቅ አስተዋፅኦ ለማድረግ ይችላሉ ብለን እናስባለን። በዚህ በናይል ፕሮጀክት አማካኝነትም እነዚህ የተለያዩ ዘርፎች በዚህ ግዙፍ እንቆቅልሽ ዉስጥ እንዴት የበኩላቸዉን ማድረግ እንደሚችሉ እናመላክታለን።»

ከዉጭ የሚመጣ እርዳታን በተመለከተ የናይል ፕሮጀክት ዋና ሥራ አስኪያጅ የተፋሰሱ አካባቢ ሃገራት በተናጠል በሀገር ደረጃ ከሚስተናገዱ ይልቅ እርስ በርሱ እንደተያያዘ ስነምህዳር ቢታዩ ይመኛል።

«በዚህ አካባቢ ለማየት የምፈልገዉ ማንኛዉም ድጋፍ የሁለትዮሽ ባይሆን ይሻላል ብዬ አስባለሁ። የአዉሮጳ ኅብረትና የግብፅን ወይም የኅብረቱን እና የዩጋንዳን ወይም የኬንያን ግንኙነት በተናጠል የማጠናከር ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም የአዉሮጳ ኅብረትም ሆነ ሌላ ማንኛዉም አካባቢዉን መደገፍ የሚፈልግ አካል የአባይ ተፋሰስን እንደ አንድ አካባቢ በማሰብ በጋራ ቢደግፍ የተሻለ ነዉ ብዬ አስባለሁ።»

ሙቱአም በዚህ ሃሳብ ትስማማለች። ይህን እዉን ለማድረግ መወሰድ አለበት ስለምትለዉ ርምጃ ስታስረዳም።

«ሁሉም የሚጀምረዉ ከመነጋገር ነዉ። እኛም በመሠረታዊነት የምናደርገዉ ይህንኑ ነዉ። ሙዚቃ እናቀርብና ዘላቂ መፍትሄ ስለማምጣትም ሆነ በአሁኑ ጊዜ እየሆነ ስላለዉ ነገር ሁሉ እንዲገነዘቡ የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት እናነሳሳለን። በእዉነቱ አንዳች ነገር እየሠራን ነዉ። በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ሰዎች አንድ መሥራት ወይም ለመሥራት መሞከር አለባቸዉ።»

እናም ስለአባይ ዉኃ አንድ ነገር ለማድረግ የተፋሰሱ ሃገራት በትብብር መሥራት ይኖርባቸዋል። ልክ የናይል ፕሮጀክት ሙዚቀኞች በሙዚቃ ድግሳቸዉ እንደሚያደርጉት ማለት ነዉ። ሚና ይበጃል የሚለዉን የመፍትሄ ሃሳብ እንዲህ አቅርቧል።

«የሚያስፈልገን በናይል ተፋሰስ አካባቢ ሃገራት መካከል ፈጠራን መሠረት ያደረገ ድንበር ዘለል ትብብር ነዉ። እናም የእኛ ሙዚቃ ለችግሩ መፍትሄ ለማምጣት ያስችላል በሚል በተምሳሌትነት የቀረበ ነዉ። ከተለያዩ ሃገራት እነዚህ ሙዚቀኞች ሁሉ ከተለያዩ የሙዚቃ መሣሪያዎች፣ የተለያዩ የአጨዋወት ስልቶች፤ እንዲሁም የተለያዩ ቅላፄ እና ስኬሎች፤ በተጨማሪም ከተለያዩ ቋንቋዎች ጋር አምጥተን በማዋሀድ አንድ የአባይ ድምጽ ለማዉጣት የምናደርገዉ ጥረት የአጠቃላይ ወሳኝ የሆነ ለዉጥ ማሳያ ነዉ። የነዚህ የተለያዩ ሃገራት ዜጎችም የራሳቸዉ የሆነ አንድ ነገር ለመሥራት በጋራ ተነስተዉ መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ማሳየት የሚችልም አርአያ ነዉ።»

ሸዋዬ ለገሠ

ኂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic