አሸናፊው የማያጠራጥረው የሩዋንዳ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 03.08.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አሸናፊው የማያጠራጥረው የሩዋንዳ ምርጫ

በምስራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ርዋንዳ ነገ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። የሀገሪቱ መሪ ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ለ3ኛ ጊዜ እጩ ሆነው ቀርበዋል።  ከረዥም አመቱ መሪ ጎን ለምርጫ የቀረቡት ሁለት ተፎካካሪ እጩዎች ግን የማሸነፍ ተስፋቸው የተመናመነ ነው።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:53

የሩዋንዳ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ

12 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ምስራቅ አፍሪቃዊት ሀገር የርዋንዳ መሪ ፖል ካጋሜ የፕሬዚደንትነቱን ስልጣን ከጨበጡ 23 ዓመታት ተቆጠሩ።  ካጋሜ የመሩት ያማፅያን ቡድን በ1994 ዓም  በሀገሪቱ የተካሄደውን የጎሳ ጭፍጨፋ ማስቆሙ ለቡድኑ መሪ ካጋሜ ዝና አትርፎላቸዋል። ባለፉት አመታት በርዋንዳ የታየው የኤኮኖሚ እድገት እና መረጋጋትም ካጋሜን በተጨማሪ አስመስግኗቸዋል። ይህ ብቻም አይደለም፣ በትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ዘገባ መሰረት፣ ርዋንዳ ከአፍሪቃ ሙስና ካልተስፋፋባቸው ጥቂት ሀገራት ተርታ ትሰለፋለች። የ59 ዓመቱ የገዢው የርዋንዳ አርበኞች ግንባር፣ በምህፃሩ የ«RPF» መሪ በምርጫው ድል እንደሚቀዳጁ በርግጠኝነት ይናገራሉ።« የፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ስነ-ስርዓት መካሄድ ስላለበት ብቻ ይካሄዳል። ውጤቱ ግን ካሁኑ ይታወቃል። እዚህ የተሰበሰበው ህዝብን ስንመለከት ድላችን እርግጠኛ ነው። ምክንያቱም ይህ RPF ባለፉት አመታትም ሲያዝመዘግበው ለነበረው የሀገራችን የኤኮኖሚ እድገት መቀጠል እድል ከፋች ነው። »

Paul Kagame

የርዋንዳ መሪ ፖል ካጋሜ

 ካጋሜ ይህን ያሉት ከጥቂት ጊዜ በፊት በአንድ የምርጫ ዘመቻ ላይ ነበር። ይሁንና ፕሬዚዳንቱ ለውጥ ለሚሹ የርዋንዳ ዜጎች እድል መስጠት አልፈለጉም። ከፕሬዚዳንቱ ጋር በነገው  ዓርብ ዕለት ለሚፎካከሩት እጩዎች ማሸነፍ ቀርቶ ራሳቸውን በይፋ ለምረጡኝ ዘመቻ ማስተዋወቅ እንኳን አልተፈቀደላቸውም። እጩዎቹ የምረጡኝ ምስላቸውን እና መፈክራቸውን በሀገሪቱ መዲና ኪጋሊ በዋና ጎዳናዎች፣ ትምህርት ቤት እና ሆስፒታሎች እንዳይሰቅሉ ተከልክለዋል። ሌሎች በእጩነት መቅረብ የፈለጉ ተወዳዳሪዎች ቅድመ ሁኔታዎችን አላሟላችሁም በሚል በምርጫ ቦርዱ  ከውድድር ተገልለዋል። በነገው ምርጫ ሁለት እጩዎች  የመወዳደር እድል አግኝተዋል። እነሱም በግል የሚወዳደሩትፊሊፐ ምፓይማና እና የአረንጓዴ ፓርቲ አባል  ፍራንክ ሀቢኔዛ ናቸው። እጩው ፊሊፐ ምፓይማና ሙያቸው ጋዜጠኝነት ነው። « ከተመረጥኩ በተለይ ማህበረሰቡ በነፃ ሀሳቡን መግለፅ እንዲቻል አበረታታለሁ። የመገናኛ ብዙኃን እየሞከሩ ነው። ነገር ግን ህዝቡ አይደፍርም። ስለዚህ ሰዎች በህዝብ ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ቀርበው ስለችግራቸው በግልፅ የሚያወሩበት መድረክ እንዲከፈት አበረታታለሁ።»

Brüssel, Protest gegen Besuch von Paul Kagamé, Präsident Ruanda

ፖል ካጋሜ ብራስልስን ሲጎበኙ የገጠማቸው የተቃውሞ ሰልፍ

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሂውማን ራይትስ ዎች ባልደረባ ኢዳ ሳውየር በሀገሪቱ ነፃ የመገናኛ ብዙኃን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጨርሶ አይሰሙም ሲሉ ይተቻል። የካጋሜ መንግሥት በተቃዋሚዎቹ እና በተቺዎቹ ላይ በተደጋጋሚ የማሰር ወይም በስውር ወስዶ ግድያ እንደሚፈጽም በዜና ምንጮች  ይነገራል። ስለሆነም ለውጥ ፈላጊው ርዋንዳዊ ሌላ እጩ ለመደገፍ ፍርሃት አድሮበታል። እጩው ፊሊፐ ምፓይማና በምያማታ የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሂዱ የተገኙት 15 ሰዎች ብቻ  ሲሆኑ ከነዚህም መካከል አብዛኞቹ ህፃናት እንደነበሩ ተዘግቧል። የሌላኛው ተፎካካሪ እጩ ሀቢኔዛ ፓርቲ ባልደረባ የነበሩት አንድሬ ካግዋም ከሁለት ዓመት ወዲህ የት እንደደረሱ ሳይታወቅ እንደጠፉ ቀርተዋል። የለውጥ መልዕክት ይዘው የተነሱት የሀቢኔዛ የምረጡኝ ዘመቻ መሪ ቃል « ተስፋ» ነው።

Ruanda Wahlkampf | Grüne Partei, Präsidentschaftskandidat Frank Habineza

የአረንጓዴ ፓርቲ አባል እና ፕሬዚዳንታዊ እጩ ፍራንክ ሀቢኔዛ

«  ህዝቡ ከ 23 ዓመት በላይ በአንድ መንግሥት መመራት እንደማያስደስተው እናውቃለን።ህዝቡ አዲስ መንግሥት ይፈልጋል። በዚህም የተነሳ የምርጫው ጊዜ ሲደርስ፣ ምርጫው በሚስጢር ስለሚካሄድ፣ እንዲሁም፣ ህዝቡ ለውጥ እና ሰላማዊ ሽግግርን በጣም ስለናፈቀ  ይመርጠናል ብለን እርግጠኞች ነን።»

ለውጥ ለሚሹት ግን የነገው ምርጫ ተስፋ ሰጪ አይደለም። ለረዥም አመታት ሀገሪቱን የመሩት ፖል ካጋሜ ባለፉት ሁለት ምርጫዎች 95 እና 93 ከመቶ ድምፅ በማግኘት አሸንፈዋል። ህገ መንግሥቱ የፕሬዚዳንቱን የስልጣን ዘመን በሁለት የምርጫ ዘመን ቢገድብም፣ ካጋሜ ለተጨማሪ የስልጣን ዘመን እንዲወዳደሩ የቀረበው የህግ ረቂቅ ከሁለት ዓመት በፊት በተካሄደው ህዝበ ውሳኔ 98 ከመቶ ድምፅ በማግኘት ስላለፈ፣ የስልጣን ዘመኑን የሚመለከተው የህገ መንግሥት አንቀጽ ተቀይሯል። በዚህም መሰረት ካጋሜ ከፈለጉ እና ከተወዳደሩ የሚቀጥሉት 17 ዓመታትም ፕሬዚዳንት ሆነው መቆየት ይችላሉ።

ልደት አበበ

አርያም ተክሌ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች