አሸባብና የፑንትላንድ መንግስት | አፍሪቃ | DW | 11.12.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አሸባብና የፑንትላንድ መንግስት

የፑንትላንድ ባለስልጣናት ለሀገሪቱ ፀጥታ ከፍተኛ ስጋት አስከትሏል ባሉት ታጣቂ ቡድን አሸባብ ጥቃት መሰንዘር ጀመሩ። ከደቡብ ሶማሊያ የወደብ ከተማ ኪስማዮ ከወራት በፊት የተሳደደዉ አሸባብ በሰሜን ሶማሊያዋ ራስገዝ ግዛት ፑንትላንድ ከዋና ከተማ ጋሮዌ አቅራቢያ የሚገኘዉን ተራራማ አካባቢ ጠንካራ ይዞታዉ አድርጎ ሰፍሯል።

Karte Puntland

Karte Puntland

የፑንትላንድ መንግስት የጥቃት ርምጃዉን የጀመረዉ ከሰላሳ በላይ የመንግስት ወታደሮች በአካባቢዉ ከተገደሉ በኋላ ነዉ። ተንታኞች እንደሚሉት ይዞታዉን ላለመልቀቅ የዛተዉ አሸባብ በፑንትላንድ የሞት ሽረት ጥቃቱን ማጠናከሩ አይቀርም ይህም ለሀገሪቱ ከፍተኛ ስጋት ነዉ።
የአሸባብት ተዋጊዎች በአዲስ ምሽግነት በሰፈሩባት ራሷን ነፃ መንግስት  አድርጋ በሰየመችዉ በሰሜን ሶማሊያ ግዛት ፑንትላንድ ዉጥረት መስፈኑን  ነዉ ዘገባዎች የሚያመለክቱት። የፑንትላንድ የፀጥታ ሚኒስትር ኻሊፍ ኢሴ ሙዳን እንደሚሉትም በዋና ከተማ ጋሮዌ በሚገኝ የጦር ሰፈር ቢያንስ 20 የመንግስት ወታደሮች ተገድለዋል፤ የአሸባብ ተዋጊዎች ሳይቀብሩት እንዳልቀሩ የተጠረጠረ ፈንጂ ተሽከርካሪያቸዉን ሲያጎን ለአስር ተጨማሪ ወታደሮች ህልፈተ ህይወት ምክንያት ሆኗል። የፑንትላንድ መንግስት አሁን ታጣቂዎቹን በአዲስ ጦር ሰፈርነት ከያዙት  ባሪ ግዛት ዉስጥ ከሚገኘዉና ጋልጋላ ከተሰኘዉ ተራራማ አካባቢ ጠራርጎ ለማስወጣት ከፍተኛ ጥቃት መሰንዘር ጀምሯል።

ሆኖም ከዋና ከተማ ጋሮዌ ሰሜን ምስራቅ አካባቢ የተደላደለዉ አሸባብ በቃል አቀባዩ አብዲ አሊ ሺሬ በኩል ይፋ ያደረገዉ ከያዘዉ ስፍራ ላለመልቀቅ ዉጊያዉን እንደሚያጠናክር ነዉ። ሼኽ አብዲሳማድ ሼኽ አብዲዋሃብ መቀመጫዉን መቃዲሾ ያደረገዉ ሳዉዝሊንክ የተሰኘዉ አማካሪ ድርጅት የምስራቅ አፍሪቃ ጉዳይ አዋቂ አሸባብ ፑንትላንድ ዉስጥ ስላለዉ ጠንካራ ይዞታ እንዲህ ይላሉ፤
«በጣም ጠንካራ የግንኙነት መረብ አላቸዉ። ስለዚህ ለፑንትላንድ ስጋት ናቸዉ። ለሶማሊላንድም እንዲሁ ያሰጋሉ። ሌላዉ ቀርቶ እነሱን ማደን ሁሉ አስቸጋሪ ነዉ የሚሆነዉ። አሁን ጥቃት አድርሶ የማምለጥን ስልት ሊከተሉ ነዉ። የመን ከሚገኘዉ አልቃይዳ ድጋፍ እያገኙ ነዉ።»
የሎንዶኑ አፍሪቃ ኮንፊደንሻል ጋዜጣ የፖለቲካና የኤኮኖሚ አርታኢ ፓትሪክ ስሚዝ፤ የዛሬ ሶስት ወራት ገደማ ከደቡብ ሶማሊያ ጠንካራ ይዞታዉ ኪስማዮ የለቀቀዉ ወዲህ አሸባብ ቋሚ የጦር ሠፈር ሳይኖረዉ ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ጥቃት የሚሰነዝር ኃይል ሆኗል ባይነዉ። ዮስት ሆኸንዶርን የብራስልስ የዓለም ዓቀፉ የቀዉስ መንስኤ አጥኚ ቡድን የሶማሊያ ጉዳይ ተመራማሪ ደግሞ አሸባብ ፑንትላንድ ላይ ያስከትላል ያሉትን ስጋት እንዲህ ይልፁታል፤
«ቀላል የማይባል ስጋት ያስከትላሉ። በአሁኑ ወቅት በሚንቀሳቀሱበት አካባቢም የፀጥታዉን ይዞታ አስቸጋሪ ያደርጉታል። ይህ በመሐመድ አቶም እና በአሸባብ ርዝራዦች መካከል ያለ ግኝኑኘት ነዉ።»
ሞሐመድ አቶም ፑንትላንድ የሚገኘዉ አሸባብ መሪ ነዉ። ናይሮቢ የሚገኙት ሌላኛዉ የሶማሊያ ጉዳይ ተንታን ራሺድ አብዲ ስለማንነቱ ያስረዳሉ፤
«ሞሐመድ አቶም የፑንትላንድ ተወላጅ ነዉ። በሰሜን ሶማሊያ አካባቢ ካለዉ ፑንትላንት ሶስት ዋነኛ ጎሳዎች መካከል ዋሰንጌል የተሰኘዉ ጎጥ አባል ነዉ። ከ2006 እስከ 2007ዓ,ም ከአሸባብ ጎን በመሆን ተዋግቷል። ወታደራዊ ጥንካሬዉን ለመመዘን በጣም ያዳግታል። አቶም የተካነ ተዋጊ ነዉ። ባለፉት ጊዜያት ደቡብ ሶማሊያ ዉስጥ የአሸባብ አዛዥ ነበር። በጠንካራ ተዋጊነቱ ዝና ያለዉ ነዉ።»  
ራሺድ አብዲ እንደሚሉትም ሞሐመድ አቶም አፍጋኒስታን ዉስጥ በአሸባሪነት ስልጥኗል። የፑንትላንድ ባለስልጣናት የአሸባብ ተዋጊዎች ከሰፈሩበት ጠንካራ ይዞታቸዉ እንዲለቁ ካልተደረገ፤ አካባቢዉን አፍጋኒስታን ዉስጥ እንዳሉት የአሸባሪ ማሰልጠኛ ጣቢያዎች ሊያደርጉት ይችላሉ ብለዉ ይሰጋሉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ
 

DW.COM