አስከፊው የባርያ ንግድ በሊቢያ | አፍሪቃ | DW | 25.11.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አስከፊው የባርያ ንግድ በሊቢያ

በሊቢያ በ21ኛው ክ/ዘመን የባርያ ንግድ ተስፋፍቷል በሚል ሰሞኑን የወጣው ዜና ዓለም አቀፍ ቁጣ ቀስቅሷል። ይሁንና፣ ይኸው ሁኔታ በሊቢያ ብቻ ሳይሆን፣ በመላ ዓለም የሚታይ ክስተት መሆኑን በዓለም አቀፍ  ደረጃ የወጡ ዘገቦች ያረጋግጣሉ። በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓም ብቻ ወደ 40 ሚልዮን የሚጠጋ ህዝብ የዚሁ አስከፊ ንግድ ሰለባ ሆኗል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:13

« ባርነት በዓለማችን ቦታ የለውም።»

 «800 ዲናር! 1000 ዲናር! 1,100 ዲናር! ከዚህ የበለጠ የሚከፍል አለ?» ሻጭ እና ገዢ በ1,200 የሊቢያ ዲናር ወይም 800 ዩኤስ ዶላር ይስማማሉ። በዚሁ የንግድ ሂደት የተሸጠው መኪና ሳይሆን፣ ፍርሀት የሚታይባቸው ከሰሀራ በስተደቡብ የሚገኙ ሀገራት ተወላጆች የሆኑ ወጣት ወንዶች ናቸው። ይኸው በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም ሰዎች በባርነት እንደ እቃ ሲሸጡ የሚያሳይ በእጅ ስልክ የተነሳው ፎቶ ለአሜሪካውያኑ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ ሲ ኤን ኤን ከደረሰ በኋላ፣ ጣቢያው ስለዚሁ ታሪክ የማጣራት ስራ አካሂዷል። በርግጥም፣ የጣቢያው ጋዜጠኞች ሊቢያ ውስጥ ባሉ በተለያዩ የመሀል አገር ቦታዎች እና በባህሩ ጠረፍ አካባቢዎች የባርነት ንግድ እንደሚካሄድ ተመልክተዋል። አካባቢውን በሚገባ የሚያውቁ ሁሉ ወደ አውሮጳ ለመምጣት የሚፈልጉ ስደተኞች በጣም እንደሚበዘበዙ ከብዙ ጊዜ ወዲህ ለማጉላት የሞከሩትን ኢሰብዓዊ ድርጊት ድርጊት ጋዜጠኞቹ በመረጃ ሊያጋልጡ ችለዋል።

 
ይኸው ድርጊት በተለይ የምዕራብ አፍሪቃ ፖለቲከኞችን እጅግ አስቆጥቷል።  በሊቢያ ከሚገኙት ስደተኞች መካከል ብዙዎቹ  ከናይጀሪያ፣ ጊኒ፣ ቡርኪና ፋሶ፤ ወይም ከኮት ዲቯርም የሄዱ ናቸው። የኒዠር ፕሬዚደንት ማሀማዱ ኢሱፉ በሊቢያ ስደተኞቹ የሚገኙበትን እጅግ አስከፊ ሁኔታ አጥብቀው ነቅፈዋል። በሀገራቸው የሚገኙትን የሊቢያ አምባሳደርንም ወደ ቤተ መንግሥታቸው በመጥራት ስለስደተኞቹ አያያዝ ተቃውሟቸውን ገልጸዋል፣ ዓለም አቀፉ ፍርድ ቤትም በሊቢያ በስደተኞች የሚካሄደውን የባርያ ንግድ ጉዳይ እንዲመረምር ጠይቀዋል። 
በቡርኪና ፋሶም የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አልፋ ቤሪ ሀገራቸው በሊቢያ የሚገኙትን አምባሳደሯን ለምክክር ወደ መዲናይቱ ዋጋዱጉ መጥራቷን ለጋዜጠኞች ነግረዋል። ይኸው ጉዳይም የአፍሪቃ ህብረት በሚቀጥለው ሳምንት ህዳር 29 እና 30፣ 2017 ዓም በኮት ዲቯር በሚያደርገው የመሪዎች ጉባዔ ላይ እንደሚመከርበትም አስታውቀዋል። 


ይኸው በሊቢያ እየተካሄደ ያለው ሰዎችን በባርነት የመሸጡ ንግድ በኮት ዲቯርም ቢሆን ትልቅ ቁጣ ነው ያፈራረቀው። ኮት ዲ ቯር 155 ስደተኞችን፣ ከነዚህም 89 ሴቶችን እና ለአካለ መጠን ያልደረሱ ህፃናትን ባለፈው ሰኞ ማታ በአይሮፕላን ከሊቢያ ወደ አቢዦን መልሳለች። የኮት ዲ ቯር መንግሥት ተወካዮች በሊቢያ ስደተኞች የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ  ለጤናም አደገኛ መሆኑን ገልጸዋል። ኮት ዲቯር ከሊቢያ የመለሰቻቸው ዜጎቿ መደበኛውን ኑሮ መጀመር ይችሉ ዘንድ በአቢዦ በተከፈተው እና ከአውሮጳ ህብረት የፊናንስ ድጋፍ በሚያገኘው ማዕከል ውስጥ ስልጠና እንደሚያገኙ አመልክታለች።  
መንበሩ በኒው ዮርክ የሚገኘው የተመድ ዋና ጸሐፊ አንቶንዮ ጉተረሽም የሊቢያ መሪዎች ሰዎች በባርነት የሚሸጡበትን ድርጊት እንዲያጣሩ እና ተጠያቂዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርቡ  ባለፈው ሰኞ ተማፅነዋል።

በሊቢያ የሚገኙ አፍሪቃውያን ስደተኞች በባርነት ሲሸጡ በሚያሳዩት ዘግናኝ ቪድዮዎች ደንግጫለሁ። ይህን ኢሰብዓዊ ድርጊት አወግዛለሁ፣  ችሎታው ያላቸው አካላት በጠቅላላ ይህንን ድርጊት ባጣዳፊ እንዲመረምሩ እና ተጠያቂዎቹን ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቀርባለሁ። ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የተመድ መስሪያ ቤቶች በጠቅላላ ጉዳዩን እንዲመረምሩም ጠይቄአለሁ።»
ሀገራት ይህን ወንጀል በጋራ እንዲታገሉ እና የተመድ ፀረ አደንዛዥ ዕፅ እና ፀረ ወንጀል መስሪያ ቤት፣ በምህፃሩ ዩንዶክ ውልን እንዲደግፉ ዋና ጸሐፊው ጥሪ አቅረበዋል። 
« ባርነት በዓለማችን ቦታ የለውም። ሰዎች በባርነት መሸጣቸው በስብዕና ላይ ከሚፈጸሙት እጅግ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እና ወንጀሎች  መካከል ይቆጠራል። ሀገራት በጠቅላላ የተመድ በድንበር ተሻጋሪው ወንጀል ላይ የተመድ ያዘጋጀውን ውል እንዲቀላቀሉ እና ስለ ሰዎች ንግድ በተዘጋጀው እና በ2004 ዓም ተግባራዊ በሆነው ሰነድ እንዲስማሙ ጥሪ አቀርባለሁ። ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ይህን አስከፊ ድርጊት  እንዲታገል አሳስባለሁ።»


ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘው በተመድ የሚደገፈው የሊቢያ መንግሥት ይህ በሀገሩ ላይ የቀረበውን ወቀሳ ለማጣራት እንደሚፈልግ ገልጿል። ለዚህም፣ ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አህመድ ሜቲግ እንዳሉት፣  አንድ ኮሚሽን ይቋቋማል፣ ተጠያቂዎቹም ይቀጣሉ። 
በሊቢያ ካሉት ከምስራቅ አፍሪቃ ኤርትራውያንም ፣ ኢትዮጵያውያን እና እና ሶማልያውያንም በሰው አሸጋጋሪዎች አማካኝነት በኒዠር አጋዴዝ እና ሊቢያ በኩል ወደ አውሮጳ ለመግባት ይሞክራሉ።  ግን ይኸው ጉዟቸው አዘውትሮ ሊቢያ ሲደርሱ ያበቃል። የስደተኞቹ መከራ እጅግ አስከፊ መሆኑን የኮት ዲቯሩ ስደተኛ ሱሌይማን ከራሱ ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ገልጾታል።
« ሊቢያ ገሀነም እሳት ናት። ያልተረጋጋች ሀገር ናት። በሚሊሺያዎች እንዳትታገት እና እንዳትሸጥ ሁሌ በፍርሀት እና በስጋት ነው የምትኖረው።  እኔ ሊቢያ ውስጥ አራት ጊዜ ታስሬአለሁ።  በዚያ የእስር ቤት ኑሮ ቀላል አይደለም።  »
በዚሁ አካባቢ በሰዎች የሚደረገው ሕገ ወጥ  ንግድ ን የመታገሉ ጥረት ከብዙ ዓመታት ጀምሮ በተመድ አጀንዳ ቀዳሚውን ቦታ እንደያዘ ይገኛል።  ይሁንና፣ ይህ ነው የሚባል የተገኘ ውጤት የለም።  በአንጻሩ፣ ችግሩ በተለይ ካለፉት ዓመate ወዲህ ይበልጡን ተባብሷል። እንደ በሊቢያ ያሉት የተመድ ቢሮ ኃላፊ ኦትማን ቤልቤይዚ ከዶይቸ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።
« እየተነጋገርን ያለነው በሰው አሸጋጋሪዎች እንደ ዕቃ እየተሸጡ ስላሉ ስደተኞች ነው። ስደተኞቹ እስከ ሶስት ወር ድረስ በሊቢያ እስር ቤቶች በሚሊሹያዎች ተይዘው ይበዘበዛሉ። ችግሩ የኤኮኖሚ ስደተኞቹ አንድም ሰነድ ስለሌላቸው ወደ ሊቢያ በህጋዊ መንገድ ሳይሆን በሰው አሸጋጋሪዎች አማካኝነት የገቡ ናቸው። ከዚህ ሌላ ደግሞ  አዘውትረው ይታገታሉ፣ ቤዛ ካልከፈሉም ይሸጣሉ፣ ቁም ስቅል ያያሉ ወይም ይገደላሉ።»
ወደ አውሮጳ ለመምጣት የሚያስችለው ሕጋዊ መንገድ እስካልተቃለላቸው ድረስ፣ ወጣት አፍሪቃውያን አደገኛውን  ጉዞ መጀመራቸው አይቀርም፣ ምክንያቱም ከዚህ የተሻለ ሌላ መንገድ አይታያቸውም።  በዚህ ዓመት ብቻ በአይኦኤም ዘገባ መሰረት 160,000 ስደተኞች በሜድትሬንየን  ባህር በኩል አውሮጳ ገብተዋል። የተመድ የስደተኞች ጉዳይ ተመልካች መስሪያ ቤት እንደሚገምተውም፣  ሌሎች በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ስደተኞች ደግሞ ወደ አውሮጳ ለመምጣት በሊቢያ በመጠባባቅ ላይ ናቸው። አይኦኤም እንዳስታወቀውም፣  ካለፈው ጥር  ወር ወዲህ ወደ 3,000 የሚጠጉ ስደተኞች በአደገኛው የባህር ጉዞ ወቅት በሜድትሬንየን ባህር ሕይወታቸውን አጥተዋል።  
አርያም ተክሌ/አንቶንዮ ካሽካሽ

ልደት አበበ

Audios and videos on the topic