አስከፊዉ የሰብዓዊ ቀዉስ በየመን | ዓለም | DW | 25.01.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አስከፊዉ የሰብዓዊ ቀዉስ በየመን

በየመን ከሚታየዉ ከፍተኛ የረሃብ ሌላ በኮሌራ የተያዘዉ እና የሚያዘዉ ሰዉ ቁጥር በሚሊዮን የሚቆጠር ሆንዋል። ለሕይወት አስጊ የሆነ ተላላፊ በሽታ በስርጭት ላይ መሆኑም እየተነገረ ነዉ። በዓመት 25,000 ሕጻናት ከተወለዱ በኋላ አልያም በተወለዱ በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ይሞታሉ። ሕጻናት ለእንቅልፍ ወደመኝታ የሚሄዱት እንደራባቸዉ ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:05

በየመን 80% ዉ ነዋሪ የአስቸኳይ ርዳታ ምግብን ይሻል።

 

ለዓመታት በዘለቀዉ ጦርነት ሰብዓዊ ቀዉስ ዉስጥ በተዘፈቀችዉ የመን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በረሃብና በተለያዩ በሽታዎች እየማቀቁ ይገኛሉ። የሐገሪቱ ሕዝብ ከረሃብና ከበሽታ ሌላ በሱዑድ አረብያዉ ጥምር ጦር ከአየር የሚደርሰዉ የቦንብ ድብደባ እየፈጀዉ ነዉ።  

ሕፃኑ በሰንዓ በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ጨቅላ ሕጻናት ከፍተኛ የሕክምና ክትትል በሚደረግላቸዉ ሳጥን ዉስጥ ተኝቶአል ። ቆዳዉ ላይ ጥንቶቹ መቆጠር እስኪችሉ ድረስ የከሳ ሕጻን የተለያዩ መድሐኒቶች እንዲያገኝ ሰዉነቱ ላይ ከተሰካካበት የመድሐኒት ማስተላለፍያ ቱቦዎች ሌላ በተደረገለት ሽንት ጨርቅ ተዉጦ ከከሳ ፊቱ ጋር በእድሜ የጠና ሰዉ አስመስሎታል። « ይጠንቀቁ ቀጥሎ የምታዩት ምስል እጅግ ሊስደነግጥ የሚችል ነዉ» ይላል ሕጻኑን በተንቀሳቃሽ ምስል ቀርፆ በየመን የሚታየዉን አሰቃቂ የሰብዓዊ ቀዉስ ይፋ ያደረገዉ ሮይተርስ የዜና አገልግሎት ባሰራጨዉ ዘገባ። በዚሁ የመረጃ ቪዲዮ ላይ አንድ እጅግ የገረጣና የከሳ ሕጻንም ይታያል

። በወቅቱ የመን ዉስጥ ያለዉን ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀዉስ በቃላት ለመግለፅ እጅግ ያዳግታል።  በየመን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ተጠሪ ሜርቲክሲል ሬላኖ እንደሚሉት ቀዉሱን ምናልባት ቁጥር ሊገልፀዉ ይችል ይሆናል።

«በአሁኑ ወቅት አንድ ሚሊዮን አምስት መቶ ሕጻናት በተመጣጣኝ ምግብ እጦት እየተሰቃዩ ናቸዉ።»  

በየመን በሚታየዉ ከፍተኛ ረሃብ ሰበብ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች በሞት አፋፍ ላይ ይገኛሉ። 28 ሚሊዮን ከሚገመተዉ የሐገሪቱ ሕዝብ  መካከል 80 % ዉ የአስቸኳይ ርዳታን ይሻል። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባልደረባ ቤቲና ሉሸር እንደሚሉት በዓለማችን ከፍተኛዉ ረሃብ የሚታይበት ቦታ የመን ነዉ።

«በዓለማችን ከፍተኛ የረሃብ ቀዉስ የሚታይበት ሐገር የመን መሆኑ የተረጋገጠ ነዉ። የወቅቱ የዓለማችን አስከፊ ቀዉስ። ይህን አስከፊ ቀዉስ ለመቅረፍ የሚደረገዉ ርምጃም አዳጋች ሆንዋል። በአሁኑ ወቅት ሚሊዮን የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ የርዳታ ምግብ ጥገኛ ናቸዉ። በርካታ ሕጻናት እና ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ነፍሰ ጡር እና የሚያጠቡ ሴቶች በተመጣጠነ ምግብ እጦት እየተሰቃዩ ነዉ። ይህ ሁሉ በመረጃ መዘርዝሩ ማየት ይቻላል።» 

በየመን በሁቲ አማፅያን እና በሳዉዲ አረብያ የሚደገፉት የፕሬዚዳንት አብድ ራቦ ማንሱር ሃዲ ጦር መካከል ለዓመታት የዘለቀዉ ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ በመሆኑ የሃገሪቱን ጉዳይ በቅርበት ለመከታል ከዉጭ ወደ ሃገሪቱ ታዛቢዎች መግባት አልቻሉም።

ሳዉዲ አረብያ የምትመራዉ ጥምር ጦር ለምሳሌ በገበያ ቦታ፤ ለሰርግ በተሰበሰቡ ሠዎች ላይ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት በመጣሉ በርካታ ሲቢል ነዋሪዎች ይገደላሉ። በየመን የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ተጠሪ ሜርቲክሲል ሬላኖ እንደሚሉት ድርጅታቸዉ ይህንን አይነቱን ጥቃት ይቆጣጠራል።

«የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ በየመን ይህን አይነት ጥቃቶች ሲደርሱ ይቆጣጠራል። ባለፉት ዓመታት ከ 5,000 በላይ ሕጻናት ተገለዋል አልያም ቆስለዋል።»

የርዳታ ምግብና የሕክምና ቁሳቁስ ያለምንም እክል ወደ የመን መግባት እንዲችል የተለያዩ የርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም ከጥቂት ጊዜ ጀምሮ ሳዉዲ አረብያም ይጠይቃሉ። ባለፈዉ ኅዳር ወር  በሁቲ አማፅያን እጅ ስር ወደ የሚገኘዉ የየመን ሰሜናዊ ክፍል ምንም አይነት የርዳታ ምግብና መድሃኒት እንዳይገባ በሳዉድ አረብያ የሚመራዉ ጥምር ጦር መከልከሉ ይታወቃል። በሳዉድ አረብያ የሚመራዉ ጥምር ኃይል በአሁኑ ወቅት በአካባቢዉ ላይ በሚገኘዉ አንድ ባህር ወደብ በኩል ለተወሰኑ ቀናት የርዳታ ቁሳቁስ እንዲገባ ቢፈቀድም የወሰነዉ የመጨረሻ ቀን ባለፈዉ ቅዳሜ ተጠናቆአል።  

በየመን ከሚታየዉ ከፍተኛ የረሃብ ሌላ በኮሌራ የተያዘዉ እና የሚያዘዉ ሰዉ ቁጥር በሚሊዮን የሚቆጠር ሆንዋል። ለሕይወት አስጊ የሆነ ተላላፊ በሽታ በስርጭት ላይ መሆኑም እየተነገረ ነዉ። በአብዛኛዉ ሲቪል ማኅበረሰቡን ክፉኛ እየጎዳ ያለዉ የየመኑ የርስ በርስ ጦርነት አሁንም መፍትሄ የሚያገኝ አይመስልም። የዓለም የምግብ ፕሮግራም ባልደረባ ቤቲና ሉሸር ፤

«በየመን እየሆነ ያለዉ ነገር ቃላት ሊገልፀዉ የማይችል አሰቃቂ ነገር ነዉ።»

 

አና ኦሲዉስ / አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

DW.COM

Audios and videos on the topic