አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና የፓርላማ አባላት | ኢትዮጵያ | DW | 28.02.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እና የፓርላማ አባላት

የኢትዮጵያ የሕዝብ የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለሁለተኛ ጊዜ የተደነገገዉን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለማፅደቅ ወይም ለመጣል የፊታችን አርብ እንደሚሰበሰቡ ታዉቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:55

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ

የምክር ቤት አባላት አዋጁን ዉድቅ እንድያደርጉ ከአገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ጫና እያደረጉ ይገኛሉ። ለዚህም አንዱ ማሳያ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ የምክር ቤቱ አባላት የእጅ ስልክ ቁጥሮች ናቸዉ የተባለዉ ዝርዝር በማኅበራዊ መገናኛ እየተዘዋወረ እንደmሚገኝ ለመታዘብ ተችሏል።

በፓርላማ የአሮምያ ክልል በቡኖ-በደለ ዞን የጮራና ዴጋ ወረዳን ወኪል አቶ ሙስጣፋ ዋርቁ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ድምፅ ለመስጠት በይፋ ጥሪ እንደሌለ ተናግረዉ የአስቸኳይ ስብሰባዉም አርብ ይካሄዳል መባሉን ከአገር ዉስጥ መገናኛ ብዙኃን እንደሰሙ ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲፀድቅ የሚደግፍ እንዳለ ሁሉ የሚቃወምም አለ ያሉት አቶ ሙስጣፋ ዋናዉ ጉዳይ የአዋጁን አስፈላጊነት መዳሰስ መሆኑን ይናገራሉ።

አዋጁን ይቃወማሉ ወይስ ይደግፉሉ? ለሚለዉ ጥያቄ ተከታዩን ብለዋል:«በሕገ-መንግስታችን እንደሚታወቀዉ ፓርላማን ወክሎ ያለዉ አባል በሦስት ጉዳዮች ይመራል። እነሱም ለኦሮሚያ፣ ለሕዝቡና ለሕገ-መንግስቱ ታዓማኝ ሆኖ ነዉ። ዉሳኔዉም ይህንን  መሰረት አድርጎ ነዉ እንጅ ከሚነፍሰዉ ንፋስ ጋር በመንፈስ  አይደለም። የተጠቀሱትን ነጥቦች መዓከል አድርጎ ለአገሪቱ ሰላም የምያስፈልገዉ ላይ እኔም አንደ አንድ ግለሰብ ዝግጅት እያደረኩ ነዉ። ሰዉ በሰላም ወቶ እንዲገባ እንዲሁም የሕዝቡ ተሳትፎ በኤኮኖሚዉ ዉስጥ ከዚህ በላይ ጠንክሮ እንዲቀጥል ለማደርግ ነዉ። እናም  ይሄንን በመጥቀም ለመወሰን ዝግጅት አድርጌያለሁ የሚል ሃሳብ አለኝ።»

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ የጃርሶና የባቦ አከባቢ ተወካይ የሆኑት ወ/ሮ ዱሌ ተሰማ አርብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ ዉሳኔ ለመስጠት ጥሪ እንደደረሳቸዉ ይናገራሉ። በሕገ-መንግስቱ ዉስጥ በተዘረዘረዉ መልክ የአዋጁ አስፈላጊነት ምንድነዉ የሚሉት ነጥቦች ገና እንዳልደረሳቸዉ ወ/ሮ ዱሌ ይናገራሉ።

ወ/ሮ ዱሌ:  «በአሁኑ ጊዜ አዋጁ ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም፣ አገሪቱን እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰዉ ምንድነዉ? የሚለዉ እኛም እንደ ጥያቄ የያዝነዉ ጉዳይ ነዉ። ለዉይይትም ጊዜ ይሰጣችኋል ተብሏል። ስለዚህ ይህን አዋጅ ያዘጋጀዉ አካል የአገሪቱን ሁኔታ መሰረት አድርጎ ስያዘጋጅ፣ በአሁኑ ጊዜ አገሪቱን  ለዚህ ያጋለጠ ምንድነዉ? እዚህ ያደረሰዉስ  ምንድነዉ? አዋጁ ከፀደቀ ነዉ ወይስ ሳይፀድቅ ነዉ ሰላም  ሊያመጣ የሚችለዉ? ለእነዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት አዋጁ የተዘጋጀበት ምክንያት ቀርቦልን፣ እኛም መነሳት ያለበትን ጥያቄ አንስተን፣ የምናጣራቸዉ ጉዳዮች አሉን።»

ወ/ሮ ዱሌ የፓርላማ አባላት ህዝብን በመወከላቸዉ ሕዝቡ አዋጁን እየፈለገ ነዉ ወይስ አይደለም፣ ማህበረሰቡ የሚያነሳቸዉ ጥያቄዊችና የአዋጁ ተፆኖስ ምንድነዉ የሚለዉን በዚህ ዉይይት ላይ እንደሚያነሱ ይናገራሉ። ዉይይቱ መቼ እንደሚካሄድ ስጠየቁ፣ «በነገዉ እለት አዋጁን ያዘጋጀዉ አካል ማብራርያ ይሰጠናል ብለን እናስባለን። ስለዚህ የአዋጁ አዘጋጅ የሚያቀርበዉን ምክንያት በመዳሰስ፣ በተላለፈዉ አዋጅ ላይ የነበረዉ ድክመትና ጥንካሪ ምን እንደነበረ፣ አሁን ደግሞ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰን ምንድነዉ? የሚል ላይ ዉይይት ይካሄዳል። ከዛ አርብ ገብተን ድምፅ እንሰጣለን።»

የአስቸካይ ጊዜ አዋጁ ኮማንድ ፖስት ትላንት ባወጣዉ መግለጫ በፓርላማ አባላቶች ላይ ይደረጋል የተባለዉን ጫና «በቸልታ እንደማይመለከተው» እና የጫና የማድረጉ ቅስቀሳ ላይ የተሳተፉትን «ህጋዊ እርምጃ» እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

የዶይቼ ቬሌ ዋትስአፕ ላይ አንድ ግለሰብ «አዋጁን የማይደግፍ አገሪቱ ትርምስ ውስጥ እንድትገባ የሚፈልግ ሰው ብቻ ነው፣ ስልጣንም አይገኝም» ሲል አስተያየቱን በፅሁፍ ልኮልናል። ሌላ አስተያየት ሰጭ «ኮማንድ ፖስቱ ቋሚ ስራዉ ህዝብን መግደልና ማሰር፣ ማሰቃየት ነዉ። የአገሪቱ ደህንነት ያለዉ በህዝብ ተወካዮች እጅ ነዉ። «ካፀደቁት ለቀብር መዘጋጀት ነዉ» ሲል የተቃዉሞ አስተያየቱን ልኮልናል።

ሙሉ ዘገባዉን ለማዳመጥ ከላይ ያለዉን የድምፅ ዘገባ ይጫኑ።

መርጋ ዮናስ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic