አስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የሂዩማን ራይትስ ዎች ማስጠንቀቂያ | ዓለም | DW | 01.11.2016
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁና የሂዩማን ራይትስ ዎች ማስጠንቀቂያ

ሂዩማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም ያወጣው መመሪያ የሰብዓዊ መብት ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቀ፡፡ መመሪያው የተለጠጡ እና አሻሚ አንቀጾችን ያካተተ ነው ብሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ “ትርጉም የሌለው፣ ህግ የመሰለ መፈክር ላይ የተመሰረተ ትንታኔ” ሲል የተቋሙን መግለጫ አጣጥሎታል፡፡ 

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:19
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:19 ደቂቃ

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዕይታ

ሂዩማን ራይትስ ዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ትናንትያወጣው 10 ገጽ የህግ ትንታኔ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣው የአዋጁ ማስፈጸሚያ መመሪያ በአምስት መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚደርሰውን ጥሰት ዘርዝሯል፡፡ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች እንዴት እንደሚጥስም አብራርቷል፡፡ በአለም አቀፍ ህግ መሰረት አንድ ሀገር አሳሳቢ ሁኔታዎች ሲገጥሟት በአስቸኳይ ጊዜ ድንጋጌ መሰረት የተወሰኑ መብቶችን ማገድ እንደምትችል የሚያወሳው ትንታኔው ነገር ግን ኢትዮጵያ በመመሪያዎቹ ላይ ያስቀመጠቻቸው እርምጃዎች ከተፈቀደው በላይ የተለጠጡ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ 

በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጉዳዮች ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ፌሌክስ ሆርን ኢትዮጵያ ሁከት እና የነብረት ውድመትን ለመከላከል አስቸኳይ ጊዜ ማወጇ ላይ ጥያቄ የላቸውም፡፡ የእርሳቸው ትችት የሚመጣው ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ህግ ከተፈቀደላት በላይ ተሻግራ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የሚያስከትሉ እርምጃዎችን በአዋጅ እና መመሪያ ውስጥ ማካተቷ ላይ ነው፡፡ ፌሌክስ በዓለም አቀፍ ህጎች መሰረት ድንገቴ እስሮች እና የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ገደብ ሊጣል እንደሚችል ያስረዳሉ፡፡   

“ኢትዮጵያ በሁኔታዎች አሳሳቢነት ላይ ተመስርቶ የተወሰኑ መብቶችን ማገድ ይፈቀድላታል፡፡ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው ሁከት እና ንብረት ማውደሙ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስከትሏል፡፡ ስለዚህ ያንን ልዩ ሁኔታ ለመፍታት የተወሰኑ መብቶችን ሊያግዱ ይችላሉ ነገር ግን እነሱ ያገዱት ሁሉንም ዓይነት መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች እና ነጻነቶችን ነው፡፡ የንብረት ወድመት በቁጥጥር ስል ለማዋል ከሚያስፈልገው በላይ እንደሄዱ ግልፅ ነው” ይላሉ ፌሌክስ፡፡   

እንደ ፌሌክስ አባባል በተለይ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ የተጣሉ ክልከላዎች የተለጠጡ እና ገደባቸውን አልፈው የሚሄዱ ናቸው፡፡ ከተለያዩ ቡድኖች ጋር የሚደረግ ግንኙነት ላይ የተጣለው ክልከላ፣ መቀመጫቸውን ውጭ ሀገር ያደረጉ ቴሌቪዥን ጣቢያዎችን መመልከት መከልከሉ እና ማህበራዊ ድረ ገጽ አጠቃቀም ላይ የተደረገው እቀባ የኢትዮጵያ መንግስት በዓለም አቀፍ ህጎች ከተፈቀደው በላይ ለመሄዱ ማሳያ ናቸው፡፡

የሂዩማን ራይትስ ዎች ትንታኔ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ላይ ስለተቀመጠው ዕገዳ ብዙ ቦታ ቢሰጥም በነጻነት የመሰብሰብ እና የመደራጀት መብቶች ላይ ስላለው ገደብም ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በዘፈቀደ ስለሚከናወን እስር እና በህግ መዳኘት አለመቻል እንደዚሁም በመመሪያው ጥሰት ይፈጽምባቸዋል ያላቸውን ትምህርት የማግኘት እና የስደተኞች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብቶች ላይ ያለውን ዕይታ አስቀምጧል፡፡ 

በመመሪያው የተካተቱት እርምጃዎች መንግስት ካለፈው ዓመት ጀምሮ ይወስዳቸው የነበሩ ህገወጥ ድርጊቶችን ህጋዊ ሽፋን ለማላበስ የተቀመጡ እንደሆኑ የሰብዓዊ መብቶች ተመራማሪው ይተቻሉ፡፡ “ብዙዎቹ የተቀመጡት ወይም የተዘረዘሩት ጉዳዮች ተቃውሞዎች ከጀመሩበት ከህዳር ወር አንስቶ ያሉትን ክልከላዎች ህጋዊ ሽፋን ለመስጠት እና በህዝቦች መሰረታዊ መብቶች ላይ የሚወሰዱ አፈናዎችን ለመቀጠል የተደረጉ ናቸው” ይላሉ፡፡    

የኢትዮጵያ መንግስት የሰብዓዊ መብት ተቋሙ ያወጣውን ሪፖርት “የተለመደ የፈጠራ ወሬ” ሲል ያጣጥለዋል፡፡ ዛሬ ስልጣናቸውን ለሌላ ተሿሚ ያስረከቡት የመንግስት የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ያወጣው ትንታኔ “ትርጉም የሌለው፣ ህግ የመሰለ እና መፈክር ላይ የተመሰረተ ነው” ብለዋል ትናንት ለዶይቸ ቨለ ምላሽ በሰጡት ቃለ ምልልስ፡፡

ፌሌክስ ለእንዲህ ዓይነቱ የመንግስት ምላሽ እንግዳ አይደሉም፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሳምንት በፊት እርሳቸውን እና መስሪያ ቤታቸውን የሚመለከት ነቀፋ በይፋ አውጥቶባቸው ነበር፡፡ “በነጻነት የሚቀርቡ መረጃዎችን ከማይታገሰው እና ተቃራኒ ሀሳቦች የሚያቀርቡ ዜጎቹን ከሚያስር መንግስት የሚጠበቅ ነው” የሚሉት ፌሌክስ መንግስት ሂዩማን ራይትስ ዎች ላይ ጣት መቀሰሩ “እርባና የሌለው” እና የእርሱንም “ተአማኒት” የሚሸረሽር ነው ይላል፡፡  

የኢትዮጵያ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ሶስት ሳምንታት አልፈዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ወደ ሁለት ሺህ ገደማ ተጠርጣሪዎች ተይዘው “ትምህርት እና የምክር አገልግሎት” ተሰጥቷቸው እንደተለቀቁ ከትላንት በስቲያ አስታውቋል፡፡ ወደ 400 ገደማ ሰዎች እጃቸውን መስጠታቸውንም ገልጿል፡፡ መንግስት “ጊዜያዊ ማቆያ” ሲል የሚጠራቸውን  እና ተጠርጣሪዎች በእስር ላይ ያሉባቸውን አምስት ቦታዎችም ከትናንት በስቲያ ይፋ አድርጓል፡፡

ሂዩማን ራይትስ ዎችን ጨምሮ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ስራ ላይ ከዋለ ጀምሮ “ቁም ስቅል”ን ጨምሮ በርካታ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደተፈጸሙ ይከሳሉ፡፡ ሀሳብን የመግለጽ፣ የመሰብሰብ፣ የመደራጀት እና መሰል መብቶች ላይ የደረሱ ሁነቶችንም ይዘረዝራሉ፡፡ አቶ ጌታቸው ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለህብረተሰቡ እፎይታን አምጥቷል ባይ ናቸው፡፡ 

የመንግስት ቃል አቃባዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ህግን የተከተለ ነው ቢሉም ሂዩማን ራይትስ ዎች ግን በአዋጁ ውስጥ ከዓለም አቀፍ ህጎች ጋር የሚጻረሩ አሻሚ አንቀጾች እንዲከለሱ ወይም እንዲሰረዙ አሳስቧል፡፡ ፌሌክስ መንግስት ለተቃውሞ የወጡ ዜጎቹን ጥያቄ ከማፈን ይልቅ ተገቢውን መፍትሄ እንዲፈልግ ይመክራሉ፡፡    

 

ተስፋለም ወልደስ

አዜብ ታደሰ
 

Audios and videos on the topic