አስራ አምስት አመታት መኖሪያ ቤት ጠብቀው ተስፋ የቆረጡት አዲስ አበቤዎች | ኤኮኖሚ | DW | 03.09.2020
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

አስራ አምስት አመታት መኖሪያ ቤት ጠብቀው ተስፋ የቆረጡት አዲስ አበቤዎች

በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብር ተመዝግቦ ለአመታት የጠበቀው ወንዴ የአዲስ አበባ አስተዳደርን "አማራጭ የመፍትሔ ውሳኔ" ከሰማ በኋላ "እኔ አቅም ካለኝ እነሱን ምን አስጠበቀኝ? ሰው አቅም ስላጣ ነው 20/80 የተመዘገበው" ሲል ለዶይቼ ቬለ ተናግሯል።አስተዳደሩ አቅምና ፍላጎት ያላቸው በማሕበር ተደራጅተው ቤት እንዲገነቡ ማቀዱን አስታውቋል

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:17

አስራ አምስት አመታት መኖሪያ ቤት ጠብቀው ተስፋ የቆረጡት አዲስ አበቤዎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለፈው ሳምንት በ20/80 እና 40/60 መርሐ ግብሮች ተመዝግበው የመኖሪያ ቤት ለማግኘት የሚጠባበቁ የከተማዋ ነዋሪዎች አቅሙ ካላቸው በማሕበር ተደራጅተው እንዲገነቡ ያቀረበው "አማራጭ የመፍትሔ ውሳኔ" እንደ ወንዴ እና ወይዘሮ ወይንሸት ላሉ ጠባቂዎች ተስፋ አስቆራጭ ሆኖባቸዋል።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው አቅሙ እና ፍላጎቱ ያላቸው ነዋሪዎች በማሕበር ተደራጅተው ከቀረቡ መንግሥት መሬት በነፃ እንደሚያቀርብ የባንክ ብድርም እንደሚያመቻች ተናግረዋል። ይኸ ግን አስራ አምስት አመታት የመኖሪያ ቤት ለጠበቀው የአዲስ አበባ ወጣት የሚታሰብ አይደለም።

"ለእኔ ይኸ አያስኬድም። እኔ አቅም ካለኝ እነሱን ምን አስጠበቀኝ? ሰው አቅም ስላጣ ነው 20/80 የተመዘገበው" የሚለው ወንዴ የከተማው አስተዳደር የመኖሪያ ቤት ግንባታ መርሐ-ግብሩን ባይሰርዝም ተስፋ አስቆራጭ ምልክት አድርጎ ቆጥሮታል። በግሌ ይሳካል ብዬ አላስብም። የግንባታ ግብዓቶች በጣም ውድ ናቸው። ምን አይነት ተቋራጭ ውል ገብቶ ነው ቤትን ያሕል ነገር ሰርቶ ለዚህ ሁሉ ሕዝብ እንዴት ነው የሚያስረክበው?" የሚሉት ወይዘሮ ወይንሸትም ተመሳሳይ ስሜት አላቸው።

በእርግጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አዲሱ ውሳኔ "መጠበቅ አልፈልግም፤ በራሴ ገንዘብ መሥራት እችላለሁ" የሚሉ ነዋሪዎችን ብቻ እንደሚመለከት የአስተዳደሩ የቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው አስረድተዋል። ይሁንና ቀድሞም በርካታ ጥያቄዎች በሚነሱበት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብር በታቀደው መንገድ እየሔደ እንዳልሆነ ጥቆማ ሰጥቷል። ለዚህም ተመዝግበው ለረዥም አመታት የጠበቁ የከተማው ነዋሪዎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምስክር ናቸው።

Äthiopien Hausbau

አዲስ አበባ ሲግናል አካባቢ የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶች

ወንዴ በኢትዮጵያ መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብር ተመዝግቦ ሲጠብቅ አስራ አምስት አመታት አለፉት። እንደ በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ሁሉ በ1990ዎቹ አጋማሽ በተጀመረው መርሐ-ግብር ቤት አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበረው። ለባለ አንድ መኝታ ቤት የተመዘገበው ወጣት አስፈላጊውን ክፍያ ለማሟላት ሲቆጥብ ቢቆይም ያሰበው አልተሳካም።

ለባለ አንድ መኝታ ቤት "በ1997 ዓ.ም. ነው የተመዘገቡት። ከዚያ በ2005 ዓ.ም. ነባር እና አዲስ ብለው ምዝገባ ጀምረው ነበር። እኔ ድጋሚ በነባር ተመዘገብኩ። በወር ቆጥቡ የተባልንው 274 ብር ነበር። በ2005 ከተመዘገቡት ቅድሚያ ይሰጣችኋል ተብለን ነበር። እስካሁን ድረስ ምንም የለም" ይላል ወንዴ።   

ከአንዴም ሁለት ጊዜ የተመዘገበው ወንዴ አሁን ተስፋ ቆርጦ የቆጠበውን ገንዘብ አውጥቶ ለሌላ ሥራ ሊያውለው ከጫፍ ደርሷል። ቀደም ብሎ ተስፋ የቆረጡ ጓደኞቹ ለተመሳሳይ ዓላማ የጀመሩትን ቁጠባ ሲያቋርጡ ታዝቧል። ከእንዲህ አይነት ውሳኔ እንዲደርስ የሚገፋው የጠበቀው የመኖሪያ ቤት የውኃ ሽታ ሆኖ መቅረቱ ብቻ አይደለም። በወንዴ አባባል ኑሮም ከእጅ ወደ አፍ ነው።

ወይዘሮ ወይሸት እንደ ወንዴ ሁሉ አስራ አምስት አመታት ገደማ ጠብቀዋል። ጠብቀው ጠብቀው ያሰቡትን የመኖሪያ ቤት አላገኙም። እርግፍ አርገው እንዳይተዉት ይጓጓሉ። ይሁነኝ ብለው እንዳይጠብቁ የሚሰሙት፤ የሚታዘቡት በየዕለቱ ከሚንረው የኑሮ ውድነት ተደማምሮ ተስፋ ያስቆርጣቸዋል። የአዲስ አበባዋ ወይዘሮም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በ1997 ዓ.ም. ይፋ ሲደረግ ተመዝግበው የነበረ ቢሆንም ከሰባት አመታት በፊት የ20/80 መርሐ ግብርን ተቀላቅለው ገንዘብ ይቆጥቡ ነበር።

"የኑሮ ውድነት አለ። ተከራይቼ ነው የምኖረው። ባለ ሁለት መኝታ ቤት ነው የተመዘገብኩት። አስራ አንድ ሺሕ ብር ቆጥቢያለሁ" የሚሉት ወይዘሮ ወይንሸት ተሳክቶ ዕጣ ቢወጣላቸው ኖሮ ከሚሰሩበት የመንግሥት ተቋም ያላቸውን ቁጠባ አውጥተው ሊከፍሉ አቅደው ነበር።   

የኢትዮጵያ መንግሥት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታን አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሳሉ ሲጀምር ውጥኑ ሰፊ እና ግዙፍ ነበር። መንግሥት ለመርሐ-ግብሩ ያዘጋጀው ሰነድ እንደሚያሳየው በወቅቱ አራት ሚሊዮን ከሚገመተው የዋና ከተማ ነዋሪ ሶስት ሚሊዮን የሚሆነው በተፋፈጉ፣ መዋቅራቸው በወዳደቀ፣ ንጽህናው የተጠበቀ የመጠጥ ውኃ እና የፍሳሽ ማስወገጃን የመሳሰሉ መሠረታዊ ግልጋሎቶች ባልተሟሉላቸው መኖሪያ ቤቶች ይኖሩ ነበር።  ይኸው ሰነድ እንደሚያሳየው ከአዲስ አበባ መኖሪያ ቤቶች 85 በመቶው መፍረስ አሊያም መታደስ የሚገባቸው ናቸው።

Äthiopien | Feche Housing Development project in Addis Abeba

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብር አቶ አርከበ እቁባይ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሳሉ የተጀመረ ነው

በቀድሞው ጠቅላይ ምኒስትር መለስ ዜናዊ ሐምሌ 10 ቀን 1996 ዓ.ም ተመርቀው በይፋ ለከተማዋ ነዋሪዎች የተላለፉት የቦሌ ገርጂ 700 የጋራ መኖሪያ ቤቶች ለአዲስ አበቤዎች ተስፋ የፈነጠቁ ነበሩ። በወቅቱ አዲስ አበባ ለነዋሪዎቿ ከሚያስፈጓት የመኖሪያ ቤቶች 300 ሺሕ ይጎድላታል፤ በየአመቱም ተጨማሪ 60 ሺሕ የመኖሪያ ቤቶች ያስፈልጓታል። ይኸ እንግዲህ የዛሬ 15 አመት በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ጥናት መሰረት መሆኑ ነው። የአዲስ አበባ ከተማ የሕዝብ ብዛት፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎት እና ኤኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ኹኔታ ባለፉት 15 አመታት ብዙ ተቀይሯል። በወቅቱ ተመዝግበው 15 አመታት መኖሪያ ቤት የጠበቁት ወይዘሮ ወይንሸት ግን በሒደት የታዘቡት ተስፋቸውን ነጥቋቸዋል።

"በበፊቶቹ ዕጣ የሚወጣው ለሚፈልጉት ሰው ነው። በብዛት በፖለቲካ ውስጥ ያሉ ናቸው ዕጣ የሚደርሳቸው። አሁንም የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ለውጥ ከመጣ በኋላ ምንም ነገር የለም። የፖለቲካ ችግር ስላለ ምንም የተሻለ ነገር እንደማይመጣ ስለምናውቅ በአሁኑ ሁለት አመት ብዙም አልቆጠብንም። የምዝገባ ሰነዳችን ግን አለ" ሲሉ ወይዘሮ ወይንሸት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ መርሐ-ግብር የነዋሪዎችን ችግር ከመፍታት ባሻገር የሥራ ዕድሎችን በመፍጠር ለድሕነት ቅነሳ ኹነኛ መሳሪያ ሊሆን ይችላል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። በመንግሥት ዕቅድ መሰረት ይኸው መርሐ ግብር የቁጠባ ባሕልን ለማዳበር፣ የከተማዋን ጭርንቁስ የመኖሪያ መንደሮች ይዞታ ለማሻሻል ብሎም ለመሬት አጠቃቀም ሥርዓት ለማበጀት ኹነኛ መላ ነው። ይሁንና የታቀደው በርካታ ፈተናዎች ገጥመውታል። ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ኤጀንሲ የፖሊሲ ትንተና ባለሙያ የነበሩት ወይዘሮ አዜብ ቀለመወርቅ ለበርካታ አመታት የተጠራቀመውን እና በየአመቱ የሚጨምረውን የመኖሪያ ቤቶችን ፍላጎት መፍታት በመንግሥት አቅም ብቻ የሚሞከር እንዳልሆነ ይናገራሉ። የኤኮኖሚ ባለሙያዋ እንደሚሉት ዕቅዱ የገንዘብ ፣ የሰለጠነ የሰው ኃይል እና የእውቀት ችግሮች አሉበት።

የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ሰናይት ዳምጠው አዲሱ መመሪያ በ2005 ዓ.ም. ተመዝግበው ለሚጠባበቁ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ተናግረዋል። የኤኮኖሚ ባለሙያዋ ወይዘሮ አዜብ ግን የመኖሪያ ቤት ችግርን ለመቅረፍ የግል ኩባንያዎች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዳቀደው የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች ማሕበራት ተሳትፎ እንደሚያሻ ይናገራሉ። 

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች