አሳፋሪው የአውሮጳ የስደተኞች ፖሊሲ | ዓለም | DW | 09.10.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አሳፋሪው የአውሮጳ የስደተኞች ፖሊሲ

የአውሮጳ ህብረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች ትናንት ላግዘምበርግ ውስጥ በህብረቱ የስደተኞች ፖሊሲ ላይ ያካሄዱት ምክክር ካላንዳች ውጤት ነዉ ያበቃዉ። ስብሰባው ሚንስትሮቹ የህብረቱን የስደተኞች አቀባበል መርህ ሰብዓዊ ገፅታ ለማስያዝ የሚችሉበትን ዕድል ፈጥሮላቸው ነበር፣ ግን፣ በአጋጣሚው ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

default

ኡተ ሼፈር

አንዳንዴ ፖለቲካ እና ገሀዱ ሁኔታ ብዙም አይገናኝም፣ ይህ አባባል የላምፔዱዛውን የስደተኞች አደጋም ያረጋግጣል። ሊቀበሉት የሚከብድ ተፃራሪ ጉዳይ ነው። በአውሮጳ የባህር ጠረፍ እየሰጠሙ የሚሞቱት ስደተኞች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ በመጣበት እና በሰሞኑ አደጋም 300 ያህል ስደተኞች በሞቱበት ባሁኑ ጊዜ ይህ ዓይነቱ ችግር እንዳይነሳ የሚቻልበትን መፍትሔ ለማፈላለግ በላግዘምበርግ እና በብራስልስ በተመቻቸ አዳራሾች የሚሰበሰቡት ፖለቲከኞች ስብሰባቸውን አንዳችም ውሳኔ ሳያሳልፉ ማብቃቱን መርጠዋል። ይህ ሞራል አልባ እና አርቆ ማሰብ የተጓደለበት የፈሪዎች ተግባር ነው። ምክንያቱም አፍሪቃን እና አውሮጳን በሜድትሬንያን ባህር በምትገኘዋ የኢጣልያ የላምፔዱዛ ደሴት በኩል የሚለያየው የባህር ክልል ርቀት 100 ኪሎሜትር ብቻ ነው። ይህም የሰሞኑ ዓይነት አሳዛኝ አደጋ ነገም ሊከሰት እንደሚችል እና አውሮጳም እንደገና ማየት እንደሚገደድ አመላካች ነው።

ለማስታወስ ያህል ስደተኞቹ በየሀገሮቻቸው እየሸሹት ያለው ድህነት ራሳቸው የፈጠሩት ወይም የመረጡት ሳይሆን፣ የሙስና ፣ ጦርነት እና ሽብርተኝነት ውጤት ነው። አውሮጳውያን የሚከተሉት የንግድ ማከላከያ እና የግምሩኩ ፖሊሲ ለዚሁ ሁኔታ በተጨማሪ ተጠያቂ ነው።

በአሁኑ ጊዜ በሞሮኮ ወይም በሊቢያ በሕገ ወጥ መንገድ የሚኖሩትን ናይጀሪያውያን ወይም ሴኔጋላውያንን የማነጋገር ዕድል ያገኘ ግለሰብ እነዚሁ ስደተኞች የሆነውን ወጪ ከፍለው በጀልባ ወደ አውሮጳ መሻገር እንደሚፈልጉ ያውቃል። ከጥቂት ሣምንታት በኋላም በአውሮጳ የባህር ጠረፍ ማንነታቸው ሳይታወቅ ሰጥመው ሕይወታቸው የምታልፈው እነዚህ ግለሰቦች ምን ያህል ግራ መጋባታቸውንም በተጨማሪ ለመረዳት ይችላል። በትውልድ ሀገራቸው ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ሰርተው ማስተዳደር ቢችሉ ኖሮ ማንኛቸውም ይህን ዓይነቱን ጉዞ እንደማይጀምሩ ነው የሚናገሩት።

ስለሆነ በዚሁ ጉዳይ ላይ መወያየት አስፈላጊ ነበር። ግን፣ የአውሮፓ ህብረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሮች በላግዘምበርጉ ምክክራቸው ባሳለፉት ብቸኛው ውሳኔ በእንግሊዝኛ ምሕፃሩ ፍሮንቴክስ በመባል የሚታወቀው የአውሮጳውያኑ ጠረፍ ጠባቂ ወኪል ጀልባዎችን በኢጣልያ የባህር ጠረፍ ድንበር እንዲሰማሩ ማሰማራት ማለታቸው የሰውን ሰሜት የሚጎዳ ደንታ ቢስነት ሆኖ ታይቶዋል፣ ልክ አውሮጳ ራሷን ከአሸባሪዎች ወይም ከባህር ወንበዴዎች መከላከል ያለባት ይመስል።

የእነዚህ ስደተኞች ሁኔታ ሲታይ አውሮጳ የተገን እሰጣጥ እና የስደተኞች አቀባበል ፖሊሲውን እንደገና በጥንቃቄ ሊመለከት ይገባል። ይሁንና፣ የሰሞኑ ዓይነት የስደተኞች አደጋ እንዳይደገም ለማድረግ በአውሮጳ ማንም፣ ኢጣልያ እና ጀርመን ጭምር ሁነኛ ርምጃ ለመውሰድ አልፈለጉም።

የጀርመን የሀገር አስተዳደር ሚንስትር ሀንስ ዩርገን ፍሪድሪኽ በሕገ ውጦቹ ሰው አሸጋጋሪዎች አንፃር ትግሉ እንዲጠናከር እና ስደተኞቹ በሚመጡባቸው ሀገራት ያከውን ሁኔታ እንዲሻሻል ሀሳብ አቅርበዋል። ግን በዚሁ ነጥብ አኳያ ተጨባጭ ውሳኔ ከመጠቆም ተቆጥበዋል። እርግጥ፣ በአውሮጳ ትልቋ ሀገር ጀርመን ባለፈው ዓመት ከ70,0000 የሚበልጡ ተገን ጠያቂዎችን ብትቀበልም፣ ይኸው ቁጥር ከሕዝቧ ቁጥር እና ከሌሎች አውሮጳውያት ሀገራት ጋ ሲነፃፀር ያን ያህል አይደለም። በአንፃርዋ ስዊድን ሸክም ቢበዛባትም ብዙ ተገን ጠያቂዎችን በመቀበል ሰብዓዊ ኃላፊነትዋን በተሻለ መንገድ ትወጣለች። በአሁኑ ጊዜ ግዙፍ የስደተኞች ችግር እንዳለባት ያስታወቀችው ኢጣልያም ብዙ አትቀበልም። ይህ የሚያሳየው ሁሉም አውሮጳውያት ሀገራት ለራሳቸው በማሰብ ኃላፊነት የሚሰማው ሰብዓዊ የስደተኞች ፖሊሲ ለማውጣት አለመፈለጋቸውን ነው።

ኡተ ሼፈር

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic