አሳሳቢ እየሆነ የመጣዉ የፆታ ጥቃት በትግራይ  | ኢትዮጵያ | DW | 22.10.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኢትዮጵያ

አሳሳቢ እየሆነ የመጣዉ የፆታ ጥቃት በትግራይ 

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች በቂ ትኩረት ባለማግኘታቸው ተባብሰው መቀጠላቸው ተገለፀ፡፡ በፆታ ጉዳይ ያለው የተዛባ ማሕበራዊ ግንዛቤ ማረም ባለመቻሉና መንግስት ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ ችግሮቹ ተባብሰው እንዲቀጥሉ እንዳደረገ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:22

'ይኾኖ' በሚል ሀሽታግ የማሕበራዊ ሚድያ ዘመቻ እየተካሄደ ነዉ

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች በቂ ትኩረት ባለማግኘታቸው ተባብሰው መቀጠላቸው ተገለፀ፡፡ በፆታ ጉዳይ ያለው የተዛባ ማሕበራዊ ግንዛቤ ማረም ባለመቻሉና መንግስት ተገቢውን ትኩረት ባለመስጠቱ ችግሮቹ ተባብሰው እንዲቀጥሉ እንዳደረገ የሴቶች መብት ተሟጋቾች ይናገራሉ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የወጣው የማእከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመለክተወ በትግራይ ክልል 12 በመቶ ሴቶች በየዕለቱ ፆታዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ በክልሉ ከሚኖሩ ያገቡ ሴቶች መካከል 18.7 በመቶ በባሎቻቸው አካላዊ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 81 በመቶ በትግራይ ገጠር አካባቢ የሚኖሩ ሴቶች በወላጆቻቸው ወይም አሳዳጊዎቻቸው አልያም የቀርብ ሰው ተገደው ትዳር እንዲመሰርቱ ይደረጋል፡፡ እነዚህና ሌሎች ሁነቶች በክልሉ ሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች የከፋ መሆኑ ያመለክታሉ፡፡ 

በትግራይ ፆታ ተኮር ጥቃቶች ትኩረት እንዲያገኙ ከሚንቀሳቀሱ ሴቶች መካከል የሆነችው ዶክተር ሄለን ቴድሮስ በምትሰራበት መቐለ ሆስፒታል ሴቶች በባሎቻቸው፣ የፍቅር ጓደኛቸው አልያም ሌላ ሰው ጥቃት ደርሶባቸው ለህክምና እንደሚመጡ ትናገራለች፡፡ እንደ ዶክተር ሄለን ምልከታ በሁሉም የዕድሜ ደረጃ የሚገኙ ሴቶች ፆታዊ ጥቃት የሚፈፀምባቸው ቢሆንም ለአቅመ ሄዋን ባልደረሱ ሴቶች ላይ የሚፈፀም ጥቃት ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ መጥቷል ትላለች፡፡ 

በተለይም በትግራይ ገጠር አካባቢዎች ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ያለው ሁኔታ የከፋ ነው፡፡ በርካታ ሴቶች ከተደፈሩ በኋላ ደፋሪዎቻቸው እንዲያገቡ ይደረጋል፡፡ በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት በመቃወም ከሚንቀሳቀሱ መካከል የሆነችው ዳናይት መኮንን ጥቃቱ አሳሳቢ ከመሆኑም በተጨማሪ ፍትሕ ዙርያ ያሉ ክፍተቶች ችግሩ የተባባሰ አድርጎታል ትላለች፡፡ 

በትግራይ የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶች የሚቃወም እንዲሁም የሕብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ በማለም 'ይኾኖ' በሚል ሀሽታግ የማሕበራዊ ሚድያ ዘመቻ ሰሞኑን እየተደረገ ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ሌሎች መንገዶች በመጠቀም በፆታ ተኮር ጥቃቶች ዙርያ ግንዛቤ ለመፍጠር እንደሚሰሩ ያነጋገርናቸው የሴቶች መብት ተሟጋች እንስቶች ተናግረዋል፡፡

 

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ 
አዜብ ታደሰ

ተስፋለም ወልደየስ 
 

Audios and videos on the topic