1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አሳሳቢው የውኃና የምግብ ጥራት

ሐሙስ፣ ጥር 30 2011

የታሸጉ ውኃና ምግቦች አመራረት እና አያያዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መሄዱን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ይናገራሉ። የምግብ እና ውኃ አምራቾች ችግሩ የምርቱ አቀማመጥ ነው ይላሉ። የምግብ እና መድሐኒት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ደግሞ ተገቢውን ቁጥጥር ለማድረግ የባለሞያዎች እጥረት እንዳለ ይገልጻል።

https://p.dw.com/p/3CrWg
Großbritannien Regal mit Konserven
ምስል Getty Images/J. Mitchell

የታሸገ ውኃና የምግብ ምርቶች በህብረተሰቡ ዘንድ በየጊዜው ቅሬታ እያስነሱ፤ ስጋትም እየፈጠሩ ነው። «DW» በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው እንደሚሉት ጥራቱ ባልተጠበቀ የታሽገ ምግብና ውኃ ምርት  ምክንያት አሳሳቢ የጤና ችግር እያጋጠመ ነው። አስተያየት ሰጭዎቹ ችግሩ እዚህ ደረጃ ላይ የደረሰው አመራረት እና አያያዛቸውን በሚመለከት መካሄድ ያለበት ቁጥጥር እየላላ በመሄዱ ነው ብለው ያምናሉ። የታሸገ ውኃና ምግብ አመራረት እና የጥራት ምዘና ምን ይመስላል ስንል የምግብና የውኃ ፋብሪካዎችን ጠይቀን ነበር። በምርት ሂደት ችግር መኖሩን የሚያሳይ መሳሪያ በመኖሩ የምርት ጥራቱ ላይ ችግር እንደሌለ የድሬደዋ የምግብ አምራች ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ደበበ ይናገራሉ። ሆኖም ከተመረቱ በኋላ የሚቀመጥበት ቦታ የምርቱ ጥራት ላይ ወሳኝነት እንዳለው ይገልጻሉ። ፋብሪካቸው ከእጅ ንክኪ ነጻ በሆነ መንገድ ውሃ እንደሚያመረት የፋም ውኃ ስራ አስኪያጅ አቶ ከማል በጅጋ ይገልጻሉ። ችግሩ የአመራረት ጥራት ችግር ሳይሆን በዋነኛነት በአቀማመጥ ወቅት የሚያመጣው ችግር እንደሆነ ገልጸው፤ ለዚህም በምርቱ ማሽጊያው ላይ እንዴት መቀመጥ እንዳለበት እንጽፋለን ብለዋል። ሆኖም ህብረተሰቡ ጥንቃቄ እንደማያደርግ ይናገራሉ አቶ ከማል። በአዲስ አበባ አንድ ተቋም በዓመት አራት ጊዜ ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ ተደንግጓል። ሆኖም በታሰበው መልክ ለመስራት ውሱን ባለሙያ በመኖሩ እንደማይከናወን አቶ ታደሰ ወርዶፋ የአዲስ አበባ የምግብ መድሃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን ምግብ መጠጥ ጤና ነክ ተቋማትና ኢንደስትሪዎች ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ ለ«DW» ገልጸዋል። “ከጤና ጋር የሚገናኙ የምግብና የመጠጥ ቁጥጥር ይደረጋል። አንድ ተቋም በዓመት አራት ጊዜ ቁጥጥር ቢደረግበት የሚል ስሌት አለ። ነገር ግን ጠብቆ መሄድ ያስቸግራል። ምክንያቱም ውስን ባለሙያ ነው ያለው። ያሉት ተቋማት እጅግ በርካታ ናቸው። ማምረቻዎቹ ከዚህ ችግር እርቀናል ሊሉ ይችላሉ። ምርታቸው በአግባቡ ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ ኃላፊነት አለባቸው።” ሰዎች ለየት ያሉ ስሜቶች ሲኖሯቸው ወደ ጤና ተቋም መሄድ እንዳለባቸው ዶ/ር አሚን መሐመድ «የኢትዮ ጠቢብ ጠቅላላ ሀኪም» ይመክራሉ። ለምሳሌ የምግብ መመረዝ ያጋጠመው በአስቸኳይ ህክምና ካልተደረገለት እስከሞት እንደሚያደርስ  ዶ/ር አሚን ይገልጻሉ። በተለይ ህጻናት በሽታ የመቋቋም አቅም ስለሌላቸው ለህይወታቸው አስጊ ሊሆን እንደሚችልም ዶክተሩ ጠቁመዋል። 

 

ነጃት ኢብራሂም

ኂሩት መለሰ