አሳሳቢው የኢትዮጵያ ድርቅ | ኢትዮጵያ | DW | 17.12.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አሳሳቢው የኢትዮጵያ ድርቅ

የኢትዮጵያ መንግስት በአስከፊው ድርቅ የተቸገሩ ዜጎችን ለመርዳት እየታገለ ይገኛል። በድርቁ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመሩ ምክንያት መንግስት ዓለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችን እገዛ ጠይቋል። ይሁንና እንደ ሶርያ ባሉ አገራት በተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ ምክንያት የዓለም አቀፍ አገዛ ለማግኘት ቀላል አልሆነም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 04:31
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
04:31 ደቂቃ

አሳሳቢው የኢትዮጵያ ድርቅ

በሰሜናዊ ኢትዮጵያ የትግራይ ክልል በትምህርት ቤት የእረፍት ሰዓት ህጻናት እግር ኳስ እየተጫወቱ ነው። ልጆቹ በሙሉ ጉልበትና ስሜት ሲጫወቱ የሚመለከቱት የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር አቶ ተስፋዬ በርሄ ግን በአገሪቱ የተከሰተው ድርቅ በተማሪዎቻቸው ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ አሳስቧቸዋል።

«የድርቁ ተጽዕኖ በዚህ አካባቢ በግልጽ ይታያል። አካባቢው በጣም ደረቅ ሆኗል። 250 ተማሪዎቻችን እስካሁን ትምህርታቸውን በአግባቡ ለመከታተል እየታገሉ ነው። እስካሁን ማንም አላቋረጠም። ነገር ግን ከመንግስት አሊያም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ተገቢውን እገዛ ካላገኘን ትምህርታቸውን ማቋረጥ ይጀምራሉ። አንዳንዶቹ እዚህ ለመድረስ እስከ 5 ኪ.ሜ. በእግራቸው ይጓዛሉ። ካለ ምግብ ይህንን ርቀት መጓዝ አይችሉም። ቁልቋል እንኳ ጠፍቷል። አንዳንድ ቤተሰቦች ልጆቻቸው በምግብ ለሥራ ፕሮግራም እንዲረዷቸው እና በለውጡ ምግብ እንዲያገኙ ልጆቻቸውን ከትምህርት ቤት ለማስወጣት እያሰቡ ነው።»

በዝናብ እጥረት ምክንያት ለአመታት ስትቸገር የቆየችው ትግራይ ዘንድሮም አስከፊ ድርቅ ገጥሟታል። በውቅያኖስ መሞቅ ምክንያት የተፈጠረው የኤል-ኒኖ ክስተት በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ከባድ ዝናብ ሲፈጥር እንደ ትግራይ ባሉት ደግሞ ድርቅን አስከትሏል።

ብዙዎች የዘንድሮው ድርቅ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከሞቱበት የ1977 ዓ.ም. ረሐብ የከፋ እንደሆነ ይናገራሉ። የዛኑ ያህል በርካቶች የዚህ ድርቅ ተጽዕኖ የ1977ቱ ዓይነት ቀውስ እንደማይደግም ለማሳየት እየሞከሩ ነው።ምክንያቱ ደግሞ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች የሚረዳው የኢትዮጵያ መንግስት ለተደጋጋሚ ድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች በምግብ እህል ራስን ለመቻል፤የምግብ ለስራ ፕሮግራሞች እና የቅድመ-ማስጠንቀቂያ ሥራዎች በወረዳዎች በመስራቱ ነው። የምግብ ለሥራ እቅዱ ግን ለሁሉም ተደራሽ አይደለም። በተለይ ህጻናት ልጆች ያሏቸው እናቶች አደጋ ውስጥ ናቸው።

«እናት የተመጣጠነ ምግብ ባለማግኘቴ ምክንያት ለልጄ የማጠባው በቂ ወተት የለኝም ትላለች። በጡቶቼ ወተት ስለሌለኝ ለልጄ የሆነ ነገር ስጠኝ ይላሉ። ይህንን ሲሉ መበሳጨት ብቻ ሳይሆን እያለቀሱ ነው። ከጡቶቼ ለልጄ የማጠባው ምንም የለኝም እያሉ ወደ እኛ የሚመጡ እናቶች በርካታ ናቸው። ነገሩ እየከፋ ነው። ይሁንና ምንም ልናደርግላቸው አንችልም።»

የ28 አመቱ ሰለሞን ስብሃት በኤርትራ ድንበር አቅራቢያ ከምትገኘው የአሊቴና ከተማ በሚገኝ የጤና ማዕከል ነርስ ነው። ሰለሞን በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ምክንያት የተጎዱ ህጻናትን የጉዳት መጠን ለማወቅ ኪሏቸውን ይመዝናል። የጤና ማዕከሉ እስካሁን በርካታ ህሙማን አልገጠሙትም። አሁን በህሙማን መኝታ ክፍሉ ውስጥ ሁለት ታካሚዎች ብቻ ይገኛሉ። ህመማቸው በቀጥታ ከድርቁ ባይገናኝም ሰዎች የተመጣጠነ ምግብ ካላገኙ የመታመም እድላቸው የሰፋ መሆኑን ሰለሞን ያስረዳል። ከህሙማኑ መካከል በፊኛ ኢንፌክሽን የታመሙት የአስር ልጆች እናት ይገኙበታል። ወ/ሮዋ የጠብታ መድሃኒት በክንዳቸው ላይ ተሰክቶላቸው ከአልጋቸው ጋደም ብለዋል።

«ልጆቼን ለመንከባከብ እና ለእነሱ ምግብ ለማቅረብ ስባዝን ደክሞኝ የታመምኩ ይመስለኛል። ባለቤቴ ሥራ የለውም። በእጅ የተሰሩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ ነው ቤተሰቤን የምደጉመው። ባለፈው አመት ትንሽ ምርት አግኝተን ነበር። በዚህ አመት ግን የዘራንው ሁሉ ምንም አላስገኘልንም። ለስምንት ልጆቼ ምግብ የማገኘው በምግብ ለሥራ ነው።

አሁን በኢትዮጵያ የተከሰተውን ድርቅ መንግስት በራሱ እንደሚቋቋመው ተናግሮ የነበረቢሆንም የአስቸኳይ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በእጥፍ ወደ 8 ሚሊዮን ሲጨምር ዓለም አቀፍ እገዛ አስፈልጎታል።

አንዳንዶች መንግስት በጊዜ ዓለም አቀፍ እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ «የኢትዮጵያ ሕዳሴ» ሐቲትን በማስቀጠሉ ላይ ትኩረት አድርጓል ሲሉ ይወቅሳሉ። ኢትዮጵያ በአማካኝ 10 በመቶ አመታዊ እድገት ላለፉት አስር አመታት ማስመዝገቧ የሚካድ አይደለም። ይሁንና አሁንም ስር የሰደደ ድህነት በአገሪቱ ይታያል። አሰቃቂ ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን የዘንድሮው ድርቅ ኢትዮጵያ በብቸኝነት ልትወጣው አትችልም። በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የአዲግራት ሐገረ-ስብከትን የመሰሉ ተቋማት በመንግስት ትከሻ ላይ የወደቀው ኃላፊነት ለማገዝ ዓለም አቀፍ እገዛ በማፈላለግ ላይ ይገኛሉ። አቶ ስብሐቱ ስዩም በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ-ክርስቲያን የአዲግራት ሐገረ-ስብከት የማህበራዊ ልማት አስተባባሪ ናቸው።

«የመረጃ መምታታት አለ። ትክክለኛው መረጃ በተፈለገው ጊዜ ለዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እየደረሰ አይደለም። መንግስት የራሱን ጥረት እያደረገ ነው። ከፍተኛ ድርቅ አለ። እንስሳት እየሞቱ ነው። ሰዎች እንደ 1977ቱ ባይራቡም ወደዚያው እየተጠጉ ነው። አስፈላጊው እርዳታ አሁን መድረስ አለበት። አለበለዚያ አገሪቱ ቀውስ ውስጥ ትገባለች። ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የሚያሳስበው ከሆነ በትክክለኛው ጊዜ መርዳት አለባቸው። ጊዜው ደግሞ አሁን ነው።»

ዘግይቶ የተሰማው የኢትዮጵያ መንግስት የእርዳታ ጥያቄ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስብስብ አሰራርና የወረቀት ሥራ ምክንያት ለመጓተት ተገዷል። ከዚህ በተጫማሪ አገሪቱ ዓለም አቀፍ እርዳታ ለማግኘት አስከፊ ሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ ከተዘፈቁት እንደ ሶርያ እና የመንን ከመሰሉ አገራት ጋር መፎካከር አለባት። በኢትዮጵያ በተከሰተው ድርቅ አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ የእርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር እስከ 15 ሚሊዮን ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማስጠንቀቁ አይዘነጋም።

ጄምስ ጄፍሪ/እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ

Audios and videos on the topic