አሳሳቢው የአፍላቶክሲን የምግብ ብክለት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 29.03.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አሳሳቢው የአፍላቶክሲን የምግብ ብክለት

አፍላቶክሲን የተባለው ጎጂ ንጥረ ነገር በአነስተኛ መጠን በሰብል ምርቶች ውስጥ እንደሚገኝ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ በቅርቡ የተካሄዱ ጥናቶች እና የላብራቶሪ ውጤቶች ንጥረ ነገሩ በምግቦች ላይ በከፍተኛ መጠን እንደታየ አመላክተዋል፡፡ ካንሰር አማጪ ነዉ የሚባለዉ አፍላቶክሲን በምግቦች በከፍተኛ መጠን መገኘቱ አሳሳቢ እንደሆነ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡

አውዲዮውን ያዳምጡ። 09:34

ንጥረ ነገሩ የጤንነት አደጋዎች ደቅኗል

ወይዘሮ መሠረት ገብረ ጊዮርጊስ ነጋዴ ናቸው፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ከምግባቸው የማይለዩትን በርበሬ ባህር አሻግረውታል፡፡ የገዙትን ዛላ በርበሬ አስፈጭተው፣ አሽገው እና በመጠሪያቸው የተሰየመውን መለያ አስለጥፈው ለአውሮጳ ገበያ ማቅረብ ከጀመሩ ሦስት ዓመት አለፋቸው፡፡ ንግዳቸው እየደራ የሚልኩትም የበርበሬ መጠን እየጨመረ በቶን የሚመዘን ሆነ፡፡ ጀርመንን ዋና መዳረሻ አድርገው የጀመሩት ንግድ ወደ ጎረቤት ኔዘርላንድስም ተስፋፋ፡፡

ባለፈው ጥር መገባደጃ ወደ ጀርመን የላኩት በርበሬ ያልጠበቁት ዕጣ ገጠመው፡፡ የጀርመን የምግብ ደህንነት ተቆጣጣሪዎች አይገባም ብለው ወደ ኢትዮጵያ መለሱት፡፡ ምክንያቱ አፍላቶክሲን ከተባለው ንጥረ ነገር ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ወይዘሮ መሠረት የሆነውን ያስረዳሉ፡፡

“ወደ ጀርመን ስንልክ አፍላቶክሲን አስመርምረን ነው የምንልከው፡፡ ከአፍላቶክሲን ነጻ የሚል ሌላ የምርመራ ውጤት ቢኖረውም እዚያ ለማረጋገጥ ብለው እነርሱ ይመረምሩት ነበር፡፡ አሁን ግን እርሱን ለማስቀረት ብለው ኃላፊነቱን ከሚመጣው ሀገር እንዲወሰድ በማለት በታኅሳስ 2008 አዲሰ ሕግ አውጥተዋል፡፡ የጤና ሰርተፍኬት [ይኑረው] የሚል ሕግ አውጥተዋል፡፡ ያ የጤና ሰርትፍኬት እያንዳንዱ የተመረመረ ኪሎ በርበሬ ከአፍላቶክሲን ነጻ መሆኑ ለማረጋገጥ በሚል ነው አዲስ ያወጡት ሕግ፡፡ ጃንዋሪ 31 ወደዚያ የተላከ 900 ኪሎ በርበሬ ነበር፡፡ ከዚያ ወረቀት አላሟላም ብለው መለሱት።” ይላሉ ወይዘሮ መሠረት፡፡ 

ኑሯቸውን ባህር ማዶ ላደረጉ ኢትዮጵያውያን ሊሸጥ ታሰቦ ወደ አውሮጳ የተላከ በርበሬ በአፍላቶክሲን ጦስ የመመለስ እጣ ሲገጥመው የወይዘሮ መሠረት የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ዘገባዎች አንደሚጠቁሙት ከኢትዮጵያ ወደ እንግሊዝ የተላከ በርበሬ አፍላቶክሲን “በከፍተኛ መጠን ተገኝቶበታል” ተብሎ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡ አውሮጳውያን የምግብ ደህንነት ተቆጣጣሪ ባለሙያዎች እንዲህ ጥብቅ ምርመራ ሲያደርጉበት የቆየው አፍላቶክሲን ምንድነው? አመጣጡስ ከየት ነው? በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ስለ ዕጽዋት በሽታ የሚያስተምሩትና የሚመራመሩት ዶክተር አለማየሁ ጫላ ምላሽ አላቸው፡፡

“አስፐርጂለስ የሚባል ፈንገስ አለ፡፡ አፍላቶክሲን ፈንገስ ወይም ሻጋታ የሚያመርተው ሜታቦላይት ነው፡፡ አስፐርጂለስ የሚባለው ሻጋታ ወይም ፈንገስ የተለያዩ እጽዋትን ያጠቃል፡፡ አዝርዕት፣ ጥራጥሬን እና ሌሎችንም ሰብሎች ያጠቃል፡፡ እርሱ በሚያጠቃ ጊዜ ነው ይህንን አፍላቶክሲን የሚባለውን ኬሚካል የሚያመርተው፡፡ መርዝ እንበለው፡፡ መርዛማ ነገር ነው፡፡ ይሄ ሻጋታ (ፈንገሱ) አፈር ውስጥም ያለ ነገር ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን ኦቾሎኒ በሚተከልበት ጊዜ ዘሩ መሬት ውስጥ ነው ያለው፡፡ ከዚያ የኦቾሎኒውን ዘር ያጠቃል፡፡ በዚያ ያው ወደ ጎተራ ይገባል ከጎተራም አልፎ ለሰው ሲሸጥ አብሮ ይሸጣል፡፡ በአፈር ውስጥ ይኖራል እንደገና በንፋስም ተይዞ ወደ ሌሎች አካባቢ ሊሰራጭ ይችላል።” 

ስለ ጉዳቱ ደግሞ ተከታዩን ብለዋል፡፡ 

“ሰዎች በዚህ በአፍላቶክሲን የተበለከለ ምግብ ጥርጥሬንም ሊሆን ይችላል በሚበሉ ጊዜ መጠኑ ከበዛ በሰዎችም በእንስሳትም ላይ በሽታ ያስከትላል፡፡ በሽታ ከማስከተል በተጨማሪ የሰውነት በሽታ የመቋቋም ኃይል ስለሚቀንስ ሰዎች ለተለያዩ በሽታዎች እንዲጋለጡ ያደርጋል፡፡ በዚህም ጉበት ሄፒታተስ በሚባል በሽታ ይጠቃል፡፡ ለካንሰርም የተጋለጡ ይሆናሉ።” 

አፍላቶክሲን እንደበርበሬ እና ለውዝ ባሉ ምርቶች ላይ ቢገኝም በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስሙ የገነነው ከወተት ጋር ተያይዞ ነበር፡፡ የዓለም አቀፉ የእንስሳት ምርምር ኢንስቲትዩት (ኢልሪ) የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የወተት ናሙና በመውሰድ ባደረገው ጥናት በአውሮጳ እና በአሜሪካ ከተቀመጠው ልክ በላይ የአፍላቶክሲን መጠን ማግኘቱን አሳውቋል፡፡ ላሞቹ የሚመገቡት የእንስሳት መኖ ከፍተኛ የአፍላቶክሲን መጠን በውስጡ እንደያዘም ጥናት አመላክቷል፡፡ 

ጉዳዩ በመገናኛ ብዙሃን ሰፊ ሽፋን በማግኘቱ በወቅቱ በወተት ተጠቃሚዎች ዘንድ ጥርጣሬ ነግሶ ከርሟል፡፡ የወተት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ ካሉ ወተት አቅራቢዎቻቸው የሚቀበሉትን መጠን በመቀነሳቸው የገበያ መቃወስ ተፈጥሮም ነበር፡፡ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በሕዝብ ዘንድ ተፈጠረ ያሉትን ግርታ ለማጥራት ጥናቱን ያደረጉትን ባለሙያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ እንዲሰጡ በማድረግ ጭምር ለማስተባበል ሞክረዋል፡፡ እንደ መከራከሪያ ያነሱት ነጥብ ደግሞ በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታ “በአሜሪካ እና አውሮጳ የደረጃ ሚዛን መለካት የለበትም” የሚል ነበር፡፡ 

ኢትዮጵያ ከጎርጎሮሳዊው 2015 ጀምሮ ለተወሰኑ ምርቶች የአፍላቶክሲን የደረጃ መለኪያዎች አውጥታለች፡፡ የላብራቶሪ ባለሙያዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ በየጊዜው በሚያደርጉት ምርመራ በርካታ የምግብ ውጤቶች በደረጃው ከተቀመጠው መጠን በላይ አፍላቶክሲን በውስጣቸው ያገኛሉ፡፡ አቶ ሄኖክ አሻግሬ ብሌስ አግሪፉድ ላብራቶሪ ሰርቪስ በተሰኘ የግል የምግብ ደህንነት ፈታሽ ድርጅት ውስጥ የኬምስትሪ ላብራቶሪ ኃላፊ ናቸው፡፡ ድርጅታቸው የአፍላቶክሲን ምርመራ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከስድስት ዓመት በፊት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የምርመራ ውጤቶቻቸው ተመርኩዘው ስለአፍላቶክሲን መስፋፋት ይህን ያጋራሉ፡፡ 

“የአፍላቶክሲን ብክለት ትልቅ ችግር ነው፡፡ በምግብ እና የእንስሳት መኖ ተዋጽኦ በምትላቸው ምርቶች ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚታይ በካይ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ምግብን ስናይ በአፍላቶክሲን የተጠቁ ምግቦች ከምትላቸው ውስጥ ከጥርጣሬ ምርቶች በቆሎ፣ ከቅባት እህሎች ውስጥ ለውዝ እንዲሁም ከቅመማ ቅመም ውስጥ በርበሬ፣ ሚጥሚጣ የመሳሰሉት በተደጋጋሚ መመረዝ ከሚታይባቸው ምርቶች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ለእንስሳት መኖ አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ ምርቶች ላይ ይህ መመረዝ ይታያል።” 

በምግቦች ውስጥ ያለው የአፍላቶክሲን መጠን በዓለም አቀፍ ደርጅቶችና በተለያዩ ሃገራት ከተቀመጠው ልክ በላይ መገኘት በላብራቶሪ ምርመራዎች ብቻ አይደለም የተደረሰበት፡፡ በኢትዮጵያ ባሉ ዩኒቨርስቲዎች ውስጥ የሚያስተምሩ የዕጽዋት በሽታ ተመራማሪዎች በተለያዩ የእርሻ ውጤቶች ላይ ባደረጉት ጥናት ተመሳሳይ መደምደሚያዎች ላይ ደርሰዋል፡፡

በሰመራ ዩኒቨርስቲ የአፕላይድ ማይክሮ ባይሎጂ መምህር የሆኑት አቶ ኤፍሬም ጉቺ በለውዝ ምርት ላይ ጥናት አድርገዋል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የተከናወነውና በዓለም አቀፍ የምርምር መጽሔቶች ላይ የታተመው ይሄ ጥናት በምሥራቅ ኢትዮጵያ የለውዝ ምርት ላይ መጠኑ ከፍተኛ የሆነ አፍላቶክሲን እንዳለ ገሃድ አውጥቷል፡፡ አቶ ኤፍሬም ጥናታቸውን የት አካባቢ ላይ እንዳከናወኑ በመዘርዘር ይጀምራሉ፡፡ 

“ምስራቅ ሐረረጌ ባቢሌ፣ ፈዲስ እና ጉርሱም በጣም የታወቁ ናቸው በለውዝ ምርት፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርት ራሱ ከእነዚህ ከሦስቱ ቦታዎች ነው ግምት የሚወሰደው፡፡ በጥናቱ ያገኘሁት አፍላቶክሲን ከፍተኛ ነው፡፡ መጠኑ ላይ ከእርሻው፣ ከክምችቱ፣ከገበያ፣ ከቸርቻሪው እያልክ ስትሄድ ትልቁ መጠን የተገኘው ከክምችቱ ውስጥ ነው፡፡ ከመከማቻ ውስጥ የተገኘው 85 በመቶ ናሙና በአውሮጳ ኮሚሽን ደረጃ በላይ ነው ያገኘሁት፡፡ ቀጥሎ ከእርሻው ላይ ከተወሰደ ናሙና ነው፡፡ በመቀጠል በጀምላ ላይ የሚሸጡት ላይ ነው፡፡ መጨረሻ ላይ ደግሞ ቆልተው የሚሸጡ ቸርቻሪዎች ላይ ነው፡፡ ከእርሱ ላይ ትንሽ ተገኝቷል፡፡ እንደውም እኔ አስተያየት የሰጠሁት ያልተቆላውን  ከመብላት የተቆላውን መጠቀም ይሻላል ብዬ ነው።” ሲሉ በጥናታቸውን የደረሱበትን መደምደሚያ ያጋራሉ፡፡  

የአቶ ኤፍሬም ጥናት አፍላቶክሲን እንዲህ በመጠን በዝቶ ለውዝ ላይ የተገኘበትን መንስኤ ፈትሿል፡፡ በእርሻ ወቅት፣ በምርት አሰባሰብ እና ክምችት ላይ አፍላቶክሲንን ለሚያመነጨው ሻጋታ ወይም ፈንገስ ለመሰራጨት የሚያግዙ ሁኔታዎችን ነቅሶ አውጥቷል፡፡ አቶ ኤፍሬም “ለውዝ በሚኮተኮትበት ወቅት ከተጎዳ ፈንገሱን ለማሰራጨት ምቹ ይሆናል።” ይላሉ፡፡ ምርት ከተሰበሰበ በኋላ በውስጡ ያለው እርጥበት በአግባቡ ካልደረቀ፣ የተበላሸውን ካልተበላሸው ካልተለየ እንደዚሁም የሚከማችበት ቦታ ያለው የሙቀት መጠን ፈንገስ የማሰራጨት አቅሙን እንደሚያባብሰው ያስረዳሉ፡፡ 

ነጋዴዋ ወይዘሮ መሠረትም ከምርት መሰብሰብ በኋላ ያሉ ችግሮች በበርበሬ ላይም እንደሚስተዋል ያስረዳሉ፡፡ 

“እኛ ችግር የሆነብን ከእርሻው ከገበሬው ሲመጣ ጀምሮ ያለው ነው፡፡ በትራስንስፖርት ሲጓጓዝ ላይ ያለው ነው ዋናው ችግር፡፡ ሌላው ማከማቻ ላይ ነው፡፡ ከገበሬዎች ማሳ ከተማ ሲገባ ነጋዴዎቹ እንዳይደርቅ እያሉ ውኃ እያርከፈከፉ ነው የሚያመጡት፡፡ የዚያን ጊዜ ሙቀቱ፣ የጸሐይ እና የእርጥበት ነገር ሲያገኝ ሁልጊዜ ፈንገስ ያው ይራባል፡፡ ከዚያ ሻጋታ ይፈጥራል፡፡ ችግሩ እዚያ ላይ ነው።”   

በኢትዮጵያ በአፍላቶክሲን ጉዳይ ላይ ቀዳሚ ጥናቶች የተካሄዱት የዛሬ 35 ዓመት ግድም ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ አፍላቶክሲን በጥናት የተደረሰበት ደግሞ በ1960ዎቹ እንግሊዝ ውስጥ ተርኪ በሚባሉ የዶሮ ዝርያዎች ውስጥ ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ በኢትዮጵያ ተደጋጋሚ ጥናቶች ቢደረጉም ሁነኛ መፍትሄዎች ሲወሰዱ አይታዩም፡፡ ምክንያቱ ምን እንደሆነ እና ችግሩን ለማስወገድ እየተደረጉ ስላሉ ጥረቶች የሐዋሳው ዩኒቨርስቲ ዶክተር አለማየሁ ይዘረዝራሉ፡፡

“በአብዛኛው እስካሁን የዳሰሳ ጥናት ላይ ነው ትኩረቱ ያለው፡፡ ችግሩ ምን ያክል ነው የሚለው ራሱ በበቂ አልተጠናም፡፡ አልታወቀም፡፡ ግን ከዚህ ከዳሰሳ ጥናት በተጨማሪ ዩኒቨርስቲዎችም፣ የምርምር ተቋማትም የተለያዩ ችግሩን ለመቀነስ የሚያስችሉ ምርምሮች ይሠራሉ፡፡ አንዱ ይህንን ንጥረ ነገረ ወይም የሚያመርተውን አስፐርጂለስ የተባለውን ሻጋታ መቋቋም የሚችሉ የሰብል ዝርያዎችን ለማውጣት የተለያዩ ሙከራዎች እየተደረጉ ነው፡፡ ሌላው ደግሞ አርሶ አደሩ የሚከተለው የሰብል ስርዓት፣ የአስተራረሱ፣ በተለይ ደግሞ ምርትን የመሰብሰቡ፣ የመውቃት እና የማከማቸት ስርዓቱ ቢስተካከል እነዚህ ንጥረ ነገሩን የመቀነስ ውጤት ያመጣሉ።”  

በአፍላቶክሲን ላይ ጥናት ያደረጉም ሆኑ በምግብ ደህንነት ፍተሻ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች በአንድ ነገር ይስማማሉ- ከጉዳዩ አሳሳቢነት አንጻር “በቂ ትኩረት አልተሰጠውም” በሚለው፡፡ የላብራቶሪ ባለሙያው አቶ ሄኖክ “በስተመጨረሻ የእሳት ማጥፋት ሥራ ከመስራት” በቂ ቁጥጥር እንዲደረግ እንደዚሁም አስፈላጊው ዝርዝር መመሪያ እና ደንብ እንዲዘጋጅ ይመክራሉ፡፡ 

 

ተስፋለም ወልደየስ

ሸዋዬ ለገሠ
 
 

Audios and videos on the topic