አሳሳቢው የማዕድን ዘርፍ አካሄድ | ኤኮኖሚ | DW | 19.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ኤኮኖሚ

አሳሳቢው የማዕድን ዘርፍ አካሄድ

ወርቅ፣ ኦፓል፣ ሳፋየር፣ ታንታለም፣ እምነበረድ እና የመሳሰሉትን ለውጭ ሀገር የምታቀርበው ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ ፍጆታ የሚሆኑ ሌሎችንም ማዕድናት ታመርታለች። ሀገሪቱ ሰፊ የማዕድን ሀብት ክምችት እንዳላት ቢነገርም በስፋት ጥቅም ላይ ሲውል ግን አይስተዋልም። ለገበያ የሚቀርቡትም ቢሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ማሽቆልቆላቸው ስጋትን አጭሯል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 10:09

አሳሳቢው የማዕድን ዘርፍ አካሄድ

የኢትዮጵያ የማዕድን ዘርፍ ልማት ታሪክ እዚህ ግባ የሚባል እንዳልሆነ ይነገርለታል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች እንደሚሉት አጭር ጊዜ ያለው ከመሆኑም ባሻገር በትክክልም ሀገሪቱ ካላት ገጸ በረከት ይልቅ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻለች ነው የሚወሱት። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ሀገሪቱ እያስተናገደች ያለችው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ዘርፉን በከፍተኛ ሁኔታ እየጎዳው እና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችም ማሽቆልቆል እየታየባቸው ስለመሆኑ ሲነገር ይሰማል።

ያለፉትን ስድስት ወራት የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶ/ር ይናገር ደሴ ወርቅን በተመለከተ ያቀረቡት መረጃ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። “ወርቅን በተመለከተ በ2006 አካባቢ ወደ ከወጪ ንግድ አኳያ ከቡና ንግድ ቀጥሎ 430 ሚሊዮን ዶላር ይገኝ ነበር። ባለፈው ዓመት ይሄ ወርዶ ወርዶ  ወደ 32 ሚሊዮን ዶላር ነው የሆነው። አሁን ባለው ሁኔታ  የኮንትሮባንድ ሰለባ ሆኗል። በዚሁ ከቀጠለ ከወርቅ የምናገኘው የውጭ ምንዛሬ ከጊዜ በኋላ ይኖራል ብሎ መገመት ያስቸግራል” ሲሉ ዶ/ር ይናገር የሁኔታውን አሳሳቢነት ጠቁመው ነበር።

የብሔራዊ ባንክ ገዢው ማዕድናትን ወደ ውጭ ሀገር ይልኩ የነበሩ ኩባንያዎች ችግር እንደገጠማቸውም በሪፖርታቸው አንስተዋል። “ትላልቅ ኩባንያዎች የተዘጉ፣ ለገንደቢ የመሳሰሉትን በተመለከተ የየራሳቸው ምክንያት አላቸው። እነዚህ ኩባንያዎች ያሉባቸውን ችግሮች በዝርዝር መፈተሽ፣ ማየት፣ ሰፊ ውይይት እና መግባባት ላይ መድረስ ያስፈልጋል” ብለዋል ዶ/ር ይናገር። 

ለመሆኑ የሀገሪቱ የማዕድን ዘርፍ ልማት የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማጠናከር አንጻር ምን ፋይዳ ያለው ነው? ዘርፉስ በትክክል እየተመራ ይሆን?። ሰለሞን ሙጬ ያዘጋጀው የኢኮኖሚው ዓለም መሰናዷችን ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሾችን ይዟል። የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡት።

ሰለሞን ሙጬ

ተስፋለም ወልደየስ  

 

Audios and videos on the topic