አሳሳቢው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፀጥታ | አፍሪቃ | DW | 05.11.2015
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አሳሳቢው የማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ፀጥታ

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መዲና ባንጊ ሰሞኑን መልሶ ያገረሸዉን ሁከት እና ጥቃት ለማብቃት ይቻል ዘንድ በሃገሪቱ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ በመጠየቅ ትናንት በርካቶች አደባባይ ወጡ። የሃገሪቱ ባለስልጣናት እና በዚያ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጋድ ኃላፊም ጠይቀዋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:50
አሁን በቀጥታ እየተሰራጨ ያለ
03:50 ደቂቃ

ማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ

ይህ ጥያቄ የቀረበው ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ማንነታቸዉ ያልታወቀ ታጣቂዎች ባካሄዱት ጥቃት አምስት ሰዎች ከገደሉ እና ከአስር የሚበልጡ ካቆሰሉ በኋላ ነው። በሃገሪቱ ለተጓደለው ፀጥታ የሽግግሩ ምክር ቤት እንደራሴዎች መንግሥትን ተጠያቂ በማድረግ ይወቅሳሉ።

በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ መዲና ባንጊ ካለፈው ሳምንት ጥቃትና ግጭት በኋላ መረጋጋት የተመለሰ ይመስላል። ይሁንና፣ የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዚደንት ፍራንስዋ ቦዚዜ እአአ በ2013 ዓም በብዛት ሙስሊሞች የሚጠቃለሉበት የሴሌካ ቡድን ከስልጣን ከተወገዱ ወዲህ ወደ ጎን የተገለለው እና የጦር መሳሪያ ትጥቁን እንዲፈታ የተደረገው የመንግሥቱ ጦር እንደገና የጦር መሳሪያ እንዲታጠቅ በመጠየቅ ትናንት በመቶዎች የሚቆጠሩ በመዲናይቱ ባንጊ አደባባይ ወጥተዋል። በተቃውሞ ሰልፍ የተሳተፉት ፣ የሽግግሩ መንግሥት እንደራሴዎች ጭምር በሃገሪቱ በሀይማኖት ፀብ እና በፖለቲካ ዉዝግብ ሰበብየተስፋፋውን እና ካለፈው መስከረም ወር ወዲህ የ90 ሰዎችን ሕይወት ያጠፋውን የሚሊሺያ ግጭት እና አፀፋ ጥቃት ለማብቃት ይቻል ዘንድ የጦር ኃይሉ አስፈላጊው ትጥቅ እንዲቀርብለት ጠይቀዋል። በሃገሪቱ የተሰማራው በምህፃሩ «ሚኑስካ» የተባለው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጓድ የተሽከርካሪ አጀቡ በመዲናይቱ በፀረ ባላካ ሚሊሺያዎች ጥቃት እንደደረሰበት ያስታወቀበት ድርጊት ሁኔታው ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን አጉልቷል።

ተቃውሞ የወጡት የሽግግሩ ምክር ቤት ፕሬዚደንት አሌግዞንድር ንጌንዴ ለዚሁ ግጭት እና ጥቃት የሕዝቡን ደህንነት ዋስትና ያላረጋገጡትን የሽግግሩን መንግሥት ባለስልጣናት ተጠያቂ አድርገዋል።

« የሽግግሩ ምክር ቤት የሽግግሩ መንግሥት ከተቋቋመ አንስቶ የሃገሪቱን ፀጥታ ያለማስጠበቁ ድርጊት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ለላዕላዩ የመንግሥት አካል ከማጉላት ቦዝኖ አያውቅም። ፀጥታ ባስቸኳይ ማስከበር የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር መሆን አለበት። እና በወቅቱ ለተጓደለው ፀጥታ መንግሥት ኃላፊነቱን መውሰድ ይኖርበታል። »

መንግሥት ይህን ኃላፊነቱን አልተወጣም ያሉበትን ወቀሳ የሃገሪቱ ፍትሕ ሚንስትር እና የመንግሥቱ ቃል አቀባል ዶሚኒክ ሰይድ ፓንጊንዲ ትክክለኛ ያልሆነ ሲሉ አስተባብለዋል። የሽግግሩ መንግሥት ሃገሪቱን ለማረጋጋት እና ሰላም ለማስፈን የሚቻለውን ሁሉ ከማድረግ ተቆጥቦ እንደማያውቅ ነው ፓንጊንዳ ያስታወቁት።

Catherine Samba-Panza

ካትሪን ሳምባ ፓንዛ

« መንግሥት በወሰደው ርምጃ በመዲናይቱ ባንጊ ካሉት ሰፈሮች መካከል ስድስቱን አረጋግቶዋል። ሰላም መልሶ ለማስፈንም መስራቱን ይቀጥላል። »

የሽግግር ፕሬዝደንት ካትሪን ሳምባ ፓንዛ የተባበሩት መንግሥት ድርጅት ሰላም አስከባሪ ጓድ፣ « ሚኑስካ» ግጭቱን ማስቆም አልቻለም በማለት ወቅሰዋል። በማዕከላይ አፍሪቃ ሬፓብሊክ ግጭት እና ሁከቱን ለማብቃት ሲባል ባለፈው ሚያዝያ በናይሮቢ የተደረሰውን የሰላም ውል የፈረሙት የሽግግሩ መንግሥት ተቀናቃኞችም ለግጭት መቀጠል ተጠያቂ ናቸው ሲሉ የነቀፉት ፕሬዚደንቷ ስርዓት ለማስከበር ይችሉ ዘንድ የተመድ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ባለፈው ጥር ወር በሃገሪቱ ላይ ለአንድ ዓመት፣ እአአ እስከ ጥር ፣ 2016 ዓም የጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳም ጠይቀዋል። በዚያ የተሰማራው የተመድ ሰላም አስከባሪ ጋድ ኃላፊፓርፌት ኦናጋ አንያንጋ ም ቀደም ሲል ተመሳሳይ ጥሪ አሰምተዋል።

ይኸው በሃገሪቱየቀጠለው ሁከት ሊካሄድ የታቀደው አጠቃላይ ምርጫ ወደ ፊታችን ታህሳስ 13፣ 2015 ዓም እንዲተላለፍ አስገድዷል።

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic