አሳሳቢው የመኪና አደጋና መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ | ጤና እና አካባቢ | DW | 04.03.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ጤና እና አካባቢ

አሳሳቢው የመኪና አደጋና መንጃ ፈቃድ አሰጣጥ

በኢትዮጵያ በየእለቱ የሚከሰተው የመኪና አደጋ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በህብረተሰቡ ዘንድ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ይሰማሉ። ይህ የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ አሰጣጥ አጠያያቂነት አንዱ የአደጋው መበራከት እንደሆነም ይጠቀሳል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:28

በህብረተሰቡ ዘንድ የመንጃ ፈቃድ አሰጣጡ ላይ የሚነሱ ቅሬታዎች ይሰማሉ

የአሽከርካሪዎች ብቃት ማረጋገጫ በአዲስ አዋጅ መደንገጉን አቶ ዮሀንስ ለማ በፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን መንገድ ደህንነት ትምህርትና ግንዛቤ ዳይሬክተር ለDW ተናግረዋል። በአዋጁም የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ በአዲስ አሠራር ተተክቷል ብለዋል። የአሽከርካሪዉ እድሜ፣ የትምህርት ደረጃና የማሽከርከር ልምድ በዋናነት መሻሻል ተደርጎባቸዋል።  በዚሁ አዋጅ በአንድ ምድብ ውስጥ ከፍተኛውን የአሽከርካሪውን ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድ ለማግኘት የሚቻለው በዚያው ምድብ ውስጥ ካለው አነስተኛ የአሽከርካሪ ብቃት ማረጋገጫ ፈቃድን በቅድሚያ በማግኘትና በየደረጃው በማሳደግም ነው።

«የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደቱ ተገቢ እንዳልሆነ በተለያየ ጊዜያቶች ይነሱ ነበር። መሥሪያ ቤቱም ይህንኑ ጥናት ካደረገ በኃላ ይሰራበት የነበረውን የመንጃ ፈቃድ አሰጣጥ ሂደት አዋጅ ቁጥር 1074/2010 አጽድቆ አውጥቷል። በፊት በአንድ ጊዜ የአውቶቢስ መንጃ ፈቃድ ይያዝ ነበር አሁን ግን ደረጃ ጠብቆ የሚኬድበት የአሰራር ስርዓትን ፈጥረናል። የበፊቱ አዋጅ ከሚጭነው ጭነት አኳያ ልዩ ችሎታ ሊኖረው ስለሚጠበቅበት እንደጭነት ማመላለሻ ደረጃው /የህዝብ ማመላለሻ እንደ ህዝብ፣ የደረቅ ጭነት ማመላለሻ እንደ ጭነት፣ የፈሳሽ ጭነት ማመላለሻ እንደ ፈሳሽ/ ታሳቢ ተደርጎ ተቀርጾ ነበር። ማንኛውም አዋጅ ህብረተሰቡን ካልጠቀመ የማይሻሻልበት ምክንያት ስለሌለ ተሻሽሏል።»  

የመንጃ ፈቃድ የተግባር ስልጠናው ላይ እክል እንዳለው አቶ ዮሀንስ ጠቅሰው፤ በሕገ ወጥ መንገድ ሲሠሩ የተገኙ 40 የመንጃ ፈቃድ ማሰልጠኛ ተቋም እርምጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል።

«የንድፍ ሀሳብ ትምህርቱ ላይ እምብዛም ችግሮች አይስተዋሉም። የተግባር ትምህርቱ ላይ በአግባቡ ያለማሰልጠን ፣ ሰዓትን በአግባቡ አለመጠቀም፣ የቴክኒክ ሰዎች ከአስተማሪዎች ጋር በመሆን የሚፈጽሟቸው ገንዘብ የመቀበል ተግባሮች ነበሩ። በዚህም በህግ ተጠያቂ የተደረጉ አሰልጣኞችም የባለስልጣን መሥሪያ ቤቱ ሰራተኞች ይገኛሉ።»
የአመለካከትና የንቃተ ኅሊና ላይ መሠራት አለበት ይላሉ ኤዜድ ኬ የአሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋም ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮናስ ካሳዬ። በአሽከርካሪዎች የስነ ምግባር ችግር እንደሚስተዋል ይናገራሉ።

«በኛ ተቋም የሚሰጡ የስልጠና አይነቶች የስነ ባህሪ፣ ቴክኒክና መንገድ ስርዓት ነው። በስልጠናው ላይ የስነ ባህሪ ሰዓት ያንሳል ምክንያቱም ብዙዎቹ አደጋዎች የስነ ባህሪ ላይ ነው ችግሮች የሚፈጠሩ። በስነ ባህሪ ላይ ከተሰራ ብዙ አደጋዎች ይቀንሳሉ የሚል ሀሳብ አለኝ። ስልጠናው እንደየምድቡ ይለያያል። የክፍል 15 ቀን ነው። 20 ሰዓት መስክ ስልጠና ይወስዳሉ። ብቃታቸው በኛ ከተረጋገጠ በኃላ መንገድ ትራንስፖርት ባለሥልጣን ብቁ ናቸው ብሎ ማረጋገጫ ይሰጣል።» 

የሕግ ቁጥጥርና ክትትል ማነስ እንደሚስተዋልም አቶ ዮናስ ገልጸው በሚመለከታቸው አካላት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ይገልጻሉ።

ነጃት ኢብራሒም

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች