አሳሳቢው የላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት ይዞታ | ኢትዮጵያ | DW | 04.12.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኢትዮጵያ

አሳሳቢው የላሊበላ አቢያተ ክርስቲያናት ይዞታ

በላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስትያናት ላይ የሚታየውን የመሰነጣጠቅ እና የመፈራረስ አደጋ ለማስቆም መሰራት እንዳለበት ያካባቢው ነዋሪዎች እና የአብያተ ክርስትያናቱ  ቀሳውስት አሳሳቡ። ለዚህ የጥገና ስራ ያስፈልጋል የሚባለውን ብዙ ሚልዮን ብር ለማሰባሰብም ህብረተሰቡ  ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ተጠይቋል።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 03:03

«አደጋውን ለመከላከል ከሚያስፈልገው ገንዘብ እስካሁን የተገኘው 1/4ኛው እንኳን አይሆንም።»

የላሊበላን አቢያተ ክርስቲያናት ከመፍረስ ለማዳን መላው ኢትዮጵያውያን ሊረባረቡ እንደሚገባ ተጠየቀ፣ አቢያተ ክርስቲያናቱን ሙሉ በሙሉ ለመጠገን 300 ሚሊዮን ብር ያስፈልጋልም ተብሏል፣ እስካሁንም 70 ሚሊዮን ብር ከተለያዩ ተቋማት መሰብሰቡ ተገልጿል፣ ከዚህ በፊት ቅርሱን ለማዳን የተደረገው ሥራ ውጤታማ እንዳልነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ገልፀዋል፣ 
አብያተ ክርስቲያናቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የመሰነጣጠቅና የመፈራረስ አደጋ እየታየባቸው ነው፡፡ የላሊበላ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አበባው አመሬ እናዳሉት ከዓመታት በፊት አቢያተ ክርስቲያናቱን ከፀሐይና ዝንብ ይከላከላል ተብሎ የተገነባው መከላከያ ጥላ ቅርሱን ለበለጠ አደጋ አጋልጦታል።
የአካባቢው ህብረተሰብም አቢያተ ክርስቲያናቱ ከአደጋ እንዲጠበቁ በሰላማዊ ሰልፍ በጠየቀው መሰረትም መንግስት ቅርሶች እንዲጠገኑ ወስኗል።


በአብያተ ክርስቲያናቱ ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመከላከል 300 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ የአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ልማት ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ የሽዋስ ደሳለኝ ገልፀዋል።
በመሆኑም እስካሁን ከአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ሁለት ሚሊዮን፣ ከአማራ ክልል መንግስት 30 ሚሊዮን፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቤተክህነት 20 ሚሊዮንና ከፌደራል መንግስት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንና ህብረተሰቡም ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የገንዘብ እርዳታ ካደረጉት ተቋማት መካከል የአማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መኮንን የለውምሰን እንዳረጋገጡት የማንነታችን ማህተም የሆኑ ቅርሶችን ለመጠገን በሚደረገው ጥረት በማንኛውም መልኩ ድጋፋቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ።
ዓለምነው መኮንን

አርያም ተክሌ

ሸዋዬ ለገሠ

Audios and videos on the topic