አሳሳቢዉ የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታ | ባህል | DW | 27.04.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ባህል

አሳሳቢዉ የዴር ሱልጣን ገዳም ይዞታ

በዴር ሱልጣን ገዳም ባለን ይዞታ ላይ የሚታየዉ ሁኔታ በዚህ ክፍለ ዘመን መታየት የሌለበት ነዉ። ሁሉም ተባብረዉ የእኛን መጥፋት ነዉ የሚፈልጉት። ከጥቁር ሕዝብ መካከል በእስራኤል ይዞታ ያለን እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ነን። ይዞታችን በጎልጎታ ተራራ ላይ ብቻ ሳይሆን በቀድሞ ጊዜ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ የሰሩት ብዙ ሕንፃና ንብረት አለን።»

አውዲዮውን ያዳምጡ። 15:37

«ሁሉም ተባብረዉ የእኛን መጥፋት ነዉ የሚፈልጉት»


« ዴር ሱልጣን ታሪካዊ ቅርስ እንደመሆኑ የዓለም ሕዝብ ቅርስ ነዉ። እያጠበብነዉ ኢትዮጵያ ስንመጣ ደግሞ እምነት ላለዉ ሁሉ የኢትዮጵያ ቅርስ ነዉ። ስለዚህ በስልጣን ላይ ያሉ የመንግሥት ሰዎች ያላቸዉን የግል የሃይማኖት አመለካከት ትተዉ ከሚያዳክሙት በሃገር ቅርስነት በታሪካዊ ንብረትነቱ አስፈላጊነት ሊሰሩ ከሚገባቸዉ አንዱ አስገዳጅ ሥራ ይሄንን መሆኑን አዉቀዉ እስከዛሬ ችላ ያሉትን ነገር በመፀፀት እንደገና በመነሳሳት ከእስራኤል መንግሥት ጋር በመነጋገር ቀዳሚ አጀንዳቸዉ በማድረግ ጉዳዩን በመንግሥት ደረጃ በግድ መነጋገር ያስፈልጋል።»

 
በቅድስቲቱ አገር በኢየሩሳሌም ክርስቶስ የተሰቀለበት፤ የተቀበረበት፤ እንዲሁም የተነሳበት ስፍራ ተብሎ በሚታመንበት በጎልጎታ ተራራ ላይ የሚገኘዉ በዴር- ሱልጣን ገዳም የኢትዮጵያ ይዞታ፤ በመፈራስ ካሳሰባቸዉ ኢትዮጵያዉያን መካከል በእስራኤል ነዋሪ የሆኑት አቶ ደረጀ ወንዳፍሪ መኳንንት ናቸዉ። ባለፈዉ ሰሞን ኢየሩሳሌም የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ያስተባበሩት ሠልፍ በጠቅላይ ምኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጽ/ቤት ፊት ለፊት ተከናውኗል። ሰላማዊ ሰልፉ በዴር ሡልጣን ገዳም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ይታደሳል ሲል የእስራኤል መንግሥት የሰጠውን ተስፋ ይጠብቅ፣ ገዳሙን እናድስ፣ እስራኤል የሚኖሩ ቤተ-እሥራኤላውያንም የኢትዮጵያ ቅርስ እንዲጠበቅ ከኢትዮጵያውያን ጎን ኾነው ትብብር ያድርጉ ሲሉ ጠይቀዋል። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በዴር ሱልጣን ገዳም ነዋሪ የነበሩትና ወደ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ገዳም የተዛወሩት አባ ገብረ ስላሴ ተስፋ፤ የዴር ሱልጣን ነገር የተወሳሰበ ነዉ ይላሉ። 
«የዴር ሱልጣን ጉዳይ አስቸጋሪና የተመሰቃቀለ ነዉ፤ የሆነ ሆኖ የቦታ ጥገና አለ ። ጎልጎታ ላይ ጥገና አለ። ከቤተ-ክርስትያን በላይ ሰዎች ሲገነቡ ፤ የኛ የሚካኤል ቤተ-ክርስትያን ተሸነቆረ፤ በዚያ ምክንያት በቀጣይ ሰዉ ላይ ይደረመሳል በሚል ሚካኤል ቤተክርስትያን ። እናም ይህ የተበሳዉ ቤተ -ክርስትያን ቀዳዳዉ በአስቸኳይ እንዲደፈን እና ገብተን አገልግሎት እንድንሰጥ የእስራኤል መንግሥት እንዲተባበር ነዉ፤ ጠቅላይ ምኒስትሩ ቢሮ ፊት ለፊት ሠላማዊ ሰልፍ የተደረገዉ።» 
ምክንያቱ በርግጥ በምን ምክንያት ነዉ የሚካኤል ቤተ -ክርስትያን የተሸነቆረዉ?


«እንግዲህ የጎልጎታ ባለይዞታዎች የስድስት ሃገራት አብያተ ክርስትያናት ናቸዉ። ከስድስቱ መካከል አንደኛዉ እኛ ነን። የጎልጎታ አባል የጎልጎታ ባለይዞታዎች ነን። ከስድስቱ መካከል ሦስቱ ታላላቆች ግሪክ፤ ላቲን እና አርመን ሲሆኑ ፤ መለስተኛ አብያተ ክርስትያናት ተብለዉ የሚመደቡት ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ- ክርስትያን ፤ የግብጽና የሶርያ ናቸዉ። የጎልጎታ ቀራንዮ በእነዚህ በስድስቱ የተያዘ ነዉ። እነዚህ ስድስቱ ሲስማሙ ነዉ እዚያ ላይ እድሳትም የሚሰራም ካለ መሰራት የሚችለዉ። በአሁኑ ጊዜ በግሪክ ሃላፊነት ግሪክ ጠይቃ ጎልጎታ ጣርያዉ እየተሰራ ነዉ። ከተጀመረ ስድስት ዓመት ሞልቶታል። ይህ ጣርያዉ እየተሰራ ሳለ ነዉ የሚካኤል ቤተ- ክርስትያን ግርግዳዉ የተሸነቆረዉ። ቤተክርስትያኑ ያረጀ ስለሆነ ሸክሙ ስለበዛበት ነዉ የተሸነቆረዉ። በዚህ ምክንያት ነዉ ችግሩ የጀመረዉ።» 
እንዲያም ሆኖ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያዉያን ዴር ሱልጣን የሚገኘዉን የሀገራቸዉን ይዞታ ለማደስ ቢጠይቁ ይሁንታን አላገኙም። እንደሚሰማዉ መፀዳጃ ቤቱ ዉኃ ያስፈልገዋል የመብራት አገልግሎትም የለም ። የመግብያዉ በር ሁሉ ማርጀቱ ተነግሮ ነበር፤ ግን አሁንም ፈቃድ አላገኘም። የእዚህ ጉዳይ መሠረታዊ ችግር ምን ይሆን?  
«መሠረታዊዉ ችግር የኛ ነዉ ማለታቸዉ ነዉ። ኢትዮጵያዉያኑ የኛ ጥገኞች ናቸዉ፤ እኛ ነን ኃላፊዎች ነን ባይ ናቸዉ። ቤተ-ክርስትያኑ ያለኛ ፈቃድ ሊታደስም ሆነ ሊሰራ አይችልም ነዉ። በጥንት ጊዜ ሀገራችን ኢትዮጵያ በሌሎች እምነት ተከታዮች ተከባ ሳለ፤ ከኢትዮጵያ ወደ ኢየሩሳሌም ለመምጣት የባህር በር ተዘግቶ ነበር። በዚያን ወቅት በኢትዮጵያ ያሉት የእምነት ተከታዮች ሳይመጡ ሲቀሩ ኢየሩሳሌም የነበሩት በጎልጎታ የሚገኘዉን ርዕስታችንን ጠባቂ አባቶች በበሽታ እና በእርጅና ሲያልቁ የተለያዩ አብያተ ክርስትያናት የኢትዮጵያን ይዞታ ተቀራመቱት። በብዛት ግን የወሰዱት ግብፆች ናቸዉ ። ግብፆች እኛ ኃላፊዎች ነን በኛ ሥር ነዉ 1600 ዓመት የኖሩት ብለዉ በብዛት የወሰዱት እነሱ ናቸዉ። የኛ ባዶ ሲቀር ሌሎችም እንደ አቅማቸዉ ወስደዋል።»                   
የኢትዮጵያ ንግሥት ሣባ ኢየሩሳሌም በሄደችበት ግዜ እስዋን የተከተሉ ሰዎች ያረፉበት ነበር በሚባለዉ በዚሁ በቅዱሱ ስፍራ ጎልጎታ የሚገኘዉ በዴር-ሱልጣን ገዳም ስያሜዉ በጥንት ዘመን በአረቦች የተሰየመና «የንጉሥ ገዳም» የሚል ትርጉም እንዳለዉ ስለገዳሙ  የሚያዉቁ ይናገራሉ። በዴር-ሱልጣን ገዳም የግሪክ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የሮማን ካቶሊካዉያን ቤተክርስትያን፤ የሶርያ ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የአርመን ኦርቶዶክሶ ቤተክርስትያን፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን እና የግብጽ ኮፕት ቤተክርስትያን ይገኙበታል። ግብፆች የኛ ነዉ ብለዉ የኢትዮጵያ ይዞታን ይዘዉ የሚገኙበት ዋና ምክንያት ሲሉ የተረኩልን በገዳሙ የሚገኘዉን የኢትዮጵያን ይዞታ ለማደስ የተቋቋመዉ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ደረጀ ወንዳፍሪ መኳንንት ናቸዉ።

 
«ቀደም ባሉት ዘመናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ- ክርስትያን ፓርትርያርክ ገንዘብ ደሞዝ እየተቆረጠለት ከግብጽ መጥቶ ነበር የሚያገለግለዉ። ይህ ለረጅም ዘመን ከተካሄደ በኋላ በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ሁኔታዉ ተቋርጦ ከራሳችን አባቶች፤ የራሳችን ፓትርያርክ ተመርጦ ሥራዉን ተረክቦአል። እነሱ በዚህ ምክንያት ስላለን ሁኔታ ቀርቦ የማወቅ እድል ነበራቸዉ። እና በኢየሩሳሌም ገዳማትም ያዉቁ ነበርና ያንን ወደ እጃቸዉ ለማስገባት የተለያየ እቅድና ዘዴ ሲጠቀሙ ነበር። ኢትዮጵያ በተለይ በዘመነ መሳፍንት ተካፋፍላ በነበረበት ወቅት ላይ እዚህ በኢየሩሳሌም ለሚገኙት መንፈሳዉያን አባቶች ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ድጋፍ ስለተቋረጠ ያንን አጋጣሚ እነሱ ያዉቁ ስለነበር አንድ መነኩሴ የሚመስል ሰላይ አስርገዉ አስገቡ። እሱ ግን እዚያ ሆኖ ገዳሙን ወደ እጃቸዉ የሚያዛዉሩበትን መንገድ ሲያጠና ሲሰራ ነበር የቆየዉ። ግብፆቹ ደግሞ አረብ እንደመሆናቸዉ መጠን በቋንቋ በደንብ መግባባት ይችላሉ። እንደገና ደግሞ ሀገሪቱ በቱርክ ቅኝ ግዛት ሥር ስለነበረች ቱርኮችም ከግብፆች ጋር የሃይማኖት ተመሳሳይነትና ተቀራራቢነት ስላላቸዉ እነዚህ እነዚህን አጋጣሚዎች ተጠቅመዉ ወረርሽኝ ገብቶ ነበርና ያንን ወረርሽኝ ለማጥፋት እንዳይዛመት ማፅዳት አለብን ብለዉ፤ መነኮሳቱን አሶጥዋቸዉ። በገዳሙ ገብቶ ሲያጠና የነበረዉን ግብፃዊ የባለቤትነት ማረጋገጫ ሰነድና መጻሕፍትን ልዩ ልዩ መዛግብትን በሽታዉን በማጥፋት ሰበብ አቃጠሉት። ኢትዮጵያዉያን የመንፈስ አባቶችንም መግባት አትችሉም ብለዉ አስወጥዋቸዉ። ቦታችን እስኪመለስልን ድረስ ለጊዜያዊ መጠለያ ብለዉ ያቋቋሙት ቦታ ላይ፤ ነዉ እስካሁን የሚገኙት እንጂ ዋናዉ ቀዳሚዉ ቦታ በነዚሁ በግብፆች ተቀምጠን ተወስዶ በእጃቸዉ ነዉ። ግብጻዉያን ብቻ ሳይሆኑ አረመኖችም በተለያየ ዘዴ ቀምተዉ ወስደዉ አሁንም እየተጠቀሙበት ይገኛሉ።»  
ኢትዮጵያዉያን ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ ሲጠይቁ ዘመናት አልፎአቸዋል። ነገሩ ፖለቲካዊ ሁኔታም ይታይበታል፤ ያሉን በዝያዉ በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘለቀ ወንድም አገኘሁ ናቸዉ።  
«ባለፈዉ ጊዜ ብቻ ሳይሆን የዛሬ 30 ዓመትም በፊት እንዲሁ ቤቱ ይታደስልን ሲሉ ኢትዮጵያዉያን በሰላማዊ ሰልፍ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያዉያኑ ገዳም ሲታይ የቀበሮ ጉድጓድ ነዉ የሚመስለዉ። በዚህ በምንኖርበት ክፍለ ዘመን የሰዉ መኖርያ አይደለም። ሁሉም ተባብረዉ የእኛን መጥፋት ነዉ የሚፈልጉት። ከጥቁር ሕዝብ መካከል በእስራኤል ይዞታ ያለን እኛ ኢትዮጵያዉያን ብቻ ነን። ይዞታችን በጎልጎታ ተራራ ላይ ያለዉ ብቻ ሳይሆን ፤ በቀድሞ ጊዜ ነገሥታቱ እና መኳንንቱ የሰሩት ብዙ ንብረት አለ።»     
ነገሩ የፖለቲካዊ እንደምታ አለዉ በሚለዉ ሃሳብ በእስራኤል ነዋሪ የሆኑት እና በቋንቋ ምርምር ተቋም ዉስጥ የሚሰሩት ሃዋዝ ኢሳያስ ናቸዉ።
« እስራኤል ከግብፅ ጋር ያላት ድንበርተኝነት፤ የሃማዝም ጉዳይ አለ። እስራኤል የበለጠ ተጠቃሚነትዋ ከግብጽ ስለሆነ ነዉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት ጫን አድርጎ፤ ባለፉት ሰነዶች ላይ ተመስርቶ ጥያቄዉን ቢያቀርብ ኖሮ ምናልባት በእስራኤል በኩል ተቀባይነት ይችላል። ወይም ደግሞ እስራኤል ይዞታዉን ለግብፅ አሳልፋ መስጠት ፈልጋ ከሆነ ጥያቄዉ ይህን እንዳታደርግ ጫና ሊፈጥርባት ይችላል ብዬ አስባለሁ።»

 
አባ ገብረስላሴ ተስፋ በበኩላቸዉ በርግጥ እስራኤል ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ባለዉለታም ነች፤ ብለዋል። 
«እስራኤል በርግጥ ለኛ ለኢትዮጵያዉያን ባለዉለታ ነዉ። አሁን የተሸነቆረዉ ቤተ- ክርስትያን እና ሌላዉ መድሐኒያለም ሁለቱ ቤተ- ክርስትያኖች፤ ተዘግተዉ ከኖሩ በኋላ እስራኤል በስድስቱ ቀን ጦርነት ጥንታዊትዋ ኢየሩሳሌምን ሲይዙ ያንን ቁልፉን ለና እንድንጠቀምበት ሰጥተዉናል። የሰጡንም መገፋታችንን አዉቀዉ ነዉ። ይደግፉናል ማለት ነዉ እስራኤሎች/ የዝያን ጊዜ ታድያ አባቶች ጠራርገዉና ዉስጡን አድሰዉ እስከዛሬ ድረስ እየተቀደሰበት ይገኛል ማለት ነዉ። እና እስራኤሎች ባለዉለታም ናቸዉ። » 
የኢትዮጵያን ይዞታ ለማስጠበቅ የተመሰረተዉ ኮሚቴ አባል አቶ ደረጀ ወንዳፍሪ መኳንንት እንደሚሉት ግብፆቹ የኢትዮጵያን ይዞታ ጠቅለዉ ለመዉሰድ ሙከራ ማድረጋቸዉ ከኢትዮጵያ መንግስት በኩል ቸልተኝነት በታየቱ ነዉ። 
«ግብፆቹ ይኽን ነገር ለማድረግ ከሚያጠናክራቸዉ ነገሮች አንዱ የእስራኤል መንግሥት ፖሊሶችን የመደበዉ ለግብፆቹ በቋንቋ ቀረብ ያሉ ሰዎችን ነዉ። ለምሳሌ ከግብጽ የመጡ ይሁዳዉያን ሊሆኑ ይችላሉ፤ ወይም ደግሞ እዚሁ የአረብ እስራኤሎች ሊሆኑ ይችላሉ፤ አረበኛ የሚያዉቁ ከኛ የበለጠ እነሱን የሚያዉቁና የሚቀርቡ ለነሱ ሊያደሉ  የሚችሉ ሰዎችን ነዉ እዛ ላይ የመደቡት።

አሁን የፈረሰዉን የቅዱስ ሚካኤል ቤተ-ክርስትያንን ለማደስ በተዘጋጀንበት ጊዜ ያለኛ ፈቃድ የሚል ነገር አመጡ። ከኢትዮጵያ በተለይም ከመንግሥት በኩል ይህን በተመለከተ ትኩረት የሚሰጥ አካል ስለሌለ እስራኤሎቹ ደግሞ እንደ ዲፕሎማት ከዚህም ከዝያም ጋር መጋጨት ስለማይፈልጉ መሃል ላይ ቆመዉ፤ ዉሳኔ ስላልሰጡ እስካሁን ድረስ በእንጥልጥል ይገኛል። በአጋጣሚ የእስራኤሉ ፕሬዚደንት በሚቀጥለዉ ሳምንት ኢትዮጵያን ለመጎብኘት ስለሚሄዱ እዚያም ላይ በማንሳት ጉዳዩን በመንግስት ደረጃ በግድ መነጋገር ያስፈልጋል። ሁለተኛ ሕዝቡ በቅርስነቱ እንዲሁም ልዩ ልዩ እምነቶችም ጭምር መንግሥት ይሄንን በተመለከተ ትኩረት ሊያደርግ የሚገባዉን ሥራ እንዲሰራ፤ በሰላማዊ ሰልፍም ይሁን በተለያየ መንገድ ለመንግሥት አቤቱታና ጩኸት ማሰማት ይገባዋል። በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኽዶ ቤተ-ክርስትያን ቁንጮ ሲኖዶሱ ስለሆነ፤ ሲኖዶሱ በበቂ ሁኔታ በጉዳዩ ላይ አልሰራም የሚል እምነት አለን። በዚህም በሲኖዶሱ ላይ ግፊት ማድረግ ይገባል። ሌላዉ በጣም ትኩረት የማደርገዉ ባሳለፍናቸዉ 20 ዓመታት በላይ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስትያን ትርጉም ያለዉ ስራ እየሰራ የሚገኝዉ የማኅበረ ቅዱሳን ስለሆነ፤ ማኅበረ ቅዱሳን አባላት በያሉበት የጉዳዩን አሳሳቢነት ሰምተዉ በሃገር ዉስጥ ለቅርስ ለንብረት መጠበቅ የሚያደርጉትን አይነት እንቅስቃሴ በዚህ ገዳም ጉዳይም እንዲያደርጉ ማሳሰብ እፈልጋለሁ። »  
በኢየሩሳሌም ነዋሪ የሆኑት አቆ ዘለቀ ወንድሙ በበኩላቸዉ ችግሮቻችን ለመፍታት ጀምረን ከዳር የማድረስ ችግር አለብን፤ ሌላዉ መንግሥትም ቢሆን መቶ ችግራችን ይይልን ሲሉ ጠይቀዋል።
 «እኛ ችግራችን እንጀምራለን እንተዋለን። ዓለም ዉስጥ ምሁራን አሉ ጠበቃ አለ፤ የሀገር ታሪክ አዋቂ ብዙዎች አሉ፤ እነሱን እንኳ አስተባብሮ በአንድ አድርጎ ወደተግባር መግባት ነዉ ያቃተዉ እንጂ አንድ ምዕራፍ ያገኝ ነበር። መንግሥታዊ መዋቅሩም ቢሆን በዉጭ ጉዳይ ምኒስትሩ አማካኝነት ይጎብኙልን፤ ይታይልን። ሁሉም በየፊናዉ ቢሄድ ፤ ይህ ነገር አንድ መፍትሄ ያገኛል። »  
የበሂንሪታ ሂዞልድ የምርምር ተቋም ዉስጥ የሚያገለግሉት ሃዋዝ ኢሳያስ በበኩላቸዉ ለእዚህ ታሪካዊ ቦታ ጥበቃ ጥሪን ማሰማት እፈልጋለሁ ብለዋል። 


«ይህ ቅርስ የኢትዮጵያ ታሪክ ነዉ። ኢየሩሳሌም የዓለም ማዕከላዊ ቦታ ናት። ስለዚህ ማንኛዉም አካል ሲኖዶሱም ቢሆን ኅብረተሰቡም ቢሆን፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢሆን ባለዉ ድርሻና መብት መሰረት የድሮ ሰነዶችን በትክክል አዘጋጅቶ ጠበቃን በመወከል ይሁን፤ በሌላም ሁኔታ፤ ይህን ጉዳይ ወደ ጥንት መሰረቱ እንዲመልሱ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ»   
በዴር ሱልጣን ጉዳይ የኢትዮጵያ መንግሥት ከጃንሆይ ጊዜ ጀምሮ ጥረት ያላደረገ ያልደከመ የለም ያሉት አባ ገብረ ስላሴ ተስፋ፤ ለችግሩ እልባት ተስፋቸዉ ፈጣሪ ብቻ ነዉ ብለዋል።  

 


አዜብ ታደሰ 


ሸዋዬ ለገሠ
 

Audios and videos on the topic