አርየል ሻሮን | ዓለም | DW | 13.01.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አርየል ሻሮን

አርየል ሻሮን።ሞቱ እንዳይባሉ ይተነፍሳሉ።አሉ እንዳይባሉ አይሰሙም፣ አይለሙም።ስምንት አመት።ሐኪሞች «ከስቃይ መገላገያ» በሚሉት ደንብ እንዳይረዷቸዉ «አይሁድ ነብስ አያጠፋም» የሚለዉ ሕግ አገዳቸዉ።እሳቸዉን ግን በነብስ አጥፊነት የሚወነጅሏቸዉ ብዙ ናቸዉ

ፍፃሜያቸዉም እንደ ሥብዕና ምግባራቸዉ ግራ አጋቢ ነበር።አርየል ሻሮን።ሞቱ እንዳይባሉ ይተነፍሳሉ።አሉ እንዳይባሉ አይሰሙም፣ አይለሙም።ስምንት አመት።ሐኪሞች «ከስቃይ መገላገያ» በሚሉት ደንብ እንዳይረዷቸዉ «አይሁድ ነብስ አያጠፋም» የሚለዉ ሕግ አገዳቸዉ።እሳቸዉን ግን በነብስ አጥፊነት የሚወነጅሏቸዉ ብዙ ናቸዉ።ቅዳሜ ጠዋት የሆስፒታሉ ባለሥልጣናት ለሕወታቸዉ «እንዳንበሳ እየታገሉ ነዉ» አሉ።አብዛኛ ሕወታቸዉንም እንዳበሳ ሲዋጉ ነበር የኖሩት።ምሳ ሠዓት ላይ የሆስፒታሉ ቃል አቀባይ ሚስተር ሻሮን «በሰላም አለፉ» አለ።ሠላም አዉርደዉ ግን አያዉቁም። ደፋሩን ግን አወዛጋቢዉን የእስራኤል የቀድሞ መሪ ላፍታ እንዘክራቸዉ።አብራችሁኝ ቆዩ።


እንደ ደፋር ወታደር ናቸዉ።ጀግና ደፈጣ ተዋጊ፥ እዉቅ ጄኔራል።

«የዮም ኩፑርን ጦርነት መጀመሪያ ላይ ካጋጠሙት እንቅፋቶች አዉጥተዉ ከግብፅ ጋር ኋላ ለሰላም ዉል ላደረሰዉ አስደናቂ ድል አብቅተዋል።ፍርሐት ብሎ ነገር አያዉቁም።አስቸጋሪ ዉሳኔዎችን ወስደዉ በፅናት ገቢራዊ አድርጓል።በሐገር የተደናቁ በዉጪ የተከበሩ ነበሩ።»

የእስራኤል ፕሬዝዳት ሺሞን ፔሬዝ።በዉጪ እንኳን ቢያንስ ፍልስጤሞች ጋ በተቃራኒዉ እንደ ፈሪ ምሕረት የለሽ ጨካኝ ሆነዉ ነዉ የሚታዩት።እንደ ሠላም ጠላት ነዉ የሚቆጠሩት።«ቡልዶዘር» ወይም የ«ቤይሩቱ» አራጅ እስከመባል የተወገዙ ጨካኝ ናቸዉ።አርየል ሻይነርማን፥ ሻሮን ወይም ኤሪክ።«ሻሮን ለስምንት አመታት ሲያጣጥሩ ቆይተዉ መሞታቸዉ ከፈጣሪ የመጣ ነዉ።ለሁሉም ፈላጭ ቆራጮች ምሳሌ የሚሆን ነዉ።የእኝሕ እጃቸዉ በሕዝባችን እና በመሪዎቻችን ደም የተዘፈቀዉ ወንጀለኛ ሞት ለፍልስጤም ሕዝብ ታሪካዊ ክስተት ነዉ።»

ደግሞ በተቃራኒዉ አፍቃሪ ነበሩ።«አንድ ቀን የብርቱካን ማሳችንን ዉሐ ሳጠጣ ቆይቼ ቀና ሥል አንዲት ልጃገረድ ከኛ እርሻ ጎን ያለዉን የአትክልት ሥፍራ ሥትኮተኩት አየሁ።እንደዛች ያለች ቆንጆ ከዚያ በፊት አይቼ አላዉቅም።» አሉ ሰዉዬዉ ኋላ።

ማርጋሊት ነዉ ስሟ።የሩሜንያ ስደተኛ ናት። አስራ-ስድስት አመቷ። የአስራ-ስድስት አመቷ የሮሜንያ ስደተኛ ከቤሎሩሱ ስደተኛ ቤተ-ሰብ ከተወለደዉ ወጣት ተዋጊ ልብ ገባች።ከዚያ በፊት በመሐሉም ግን ዉጊያ አለ።1953 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) እስራኤልን የሚያጠቁ የአረብ ደፈጣ ተዋጊዎችን የሚመታ ልዩ ኮማንዶ ጦር መሠረቱ።አንድ መቶ አንድ ጓድ አሉት።

በዚያዉ ዓመት ያኔ ዮርዳኖስ ከምታስተዳድረዉ ምዕራባዊ ዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ሠርገዉ የገቡ ሁለት አረቦች አንዲት የሁዲና ሁለት ልጆችዋን ገደሉ።ለወጣቱ የጦር መኮንን ጥሩ አጋጣሚ ነበር።አዲሱን ልዩ ኮማንዶ ጦራቸዉን ሁለቱ አረቦች ነበሩበት በተባለችዉ ከተማ አዘመቱ።አለቆቻቸዉ ያዘዟቸዉ አስር ተጠርጣሪ ቤቶችን እንዲያስሱ ነበር።ለማዘዝ እንጂ ለመታዘዝ አልተፈጠሩም። ከተማይቱን አተረማመሷት።አርባ-ሁለት ቤቶችን ደመሰሱ።በዮርዳኖስ መግለጫ መሠረት ሴትና ሕፃናትን ጨምሮ ስልሳ ዘጠኝ የዋሕ ሰላማዊ ሰዎችን ረፈረፉ።

የአረቦች ዉግዘት፥ የእስራኤል ደጋፊዎች የአሜሪካና የምዕራብ አዉሮጶች ወቀሳ ያየለባቸዉ የያኔዉ የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ቤን ጎሪዮን ለሻሮን ጥፋት በይፋ ይቀርታ መጠየቅ ነበረባቸዉ።ወጣቱን የጦር መኮንን ግን የገሰፀዉ አልነበረም።እንደ እምነት ፍልስና ተጋሪዎቻቸዉ ጥፋቱን እንደ ታላቅ ድል እያሰላሰሉ ተሞሸሩ።

ያቺን ቆንጆ ኮረዳ ጠቀለሉ።ጋሊ-በሚል ቅፅል ያቆለምጧት ያዙም።ግን እንደገና ጦርነት።1956 ግብፅ የሲዊዝ ቦይን መዉረሷን ለመበቀል ብሪታንያ፥ፈረንሳይ እና እስራኤል ግብፅን ሲወሩ ከወራሪዉ ጦር ወጣት አዛዦች አንዱ ሆነዉ ዘመቱ።እንደገና ዉዝግብ። በወረራዉ ድል በማግኘታቸዉ ተወደሱ።ያለቆቻቸዉን ትዕዛዝ ባለማክበራቸዉ ተወቀሱ።ከቤታቸዉ ግን ወቀሳዉን ማፅናኛ የድል ፌስታቸዉን ማጠናከሪያ ብስራት አገኙ።ባለቤታቸዉ ወድ ልጅ ተገላገሉ።ሥሙንም ጉር አሉት።እንደ አባት ተደሰቱ።በስድስተኛ ዓመቱ ግን ሐዘን።ባለቤታቸዉ ማርጋሊት በመኪና አደጋ ሞቱ።1962።እንደ አፍቃሪ ባል አዘኑ።

ግን ለሐዘን በቂ ጊዜ-የለም።ለጦርነት እንጂ።1967 ሌላ ጦርነት።ግብፅ ሲና በረሐ ሠፍሮ የነበረዉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሠራዊትን አባራ ጦሯን ከእስራኤል ጋር ወደሚያዋስናት ድንበር አዘመተች።ጎላን ኮረብታ ላይ የሠፈረዉ የሶሪያ ጦር በበኩሉ እስራኤልን በመድፍ ይቀጠቅጥ ገባ።ሰዉዬዉ ብረት ለበስ ክፍለ-ጦራቸዉን ይዘዉ ዳግም ከግብፅ ጦር ጋር ይተጋተጉ ያዙ።ሰኔ-አምስት።

ከአረር ጋር ሻምፓኝ፥ ቮድካ እና ካቭሌር ከታጨቀበት ታንካቸዉ ሆነዉ የሚያዙት ጦር የጠላቱን የመከላከያ ግንባር ሠብሮ ወደ ግብፅ ገሠገሠ።እሳቸዉም ድፍን አይሁድም፥ የእስራኤል አስታጣቂ ደጋፊዎችም ፈነደቁ።ከቴል አቪቭ እስከ ዋሽንግተን ታላቅ ድል።በስድስተኛ ወሩ ግን በመድፍ፥ ታንክ ጥይት አረብን ሲያረግፉ የኖሩት የጦር መኮንን ልጅ በጥይት ተገደለ።ጉር።

ከጓደኛዉ ጋር እንደ ወታደር ልጅ በአሮጌ ጠመንጃ ይጫወት ነበር።ጓደኛዉ ምላጭዋን ሳባት። ጉር ክፉኛ ቆሰለ።ሻሮን ታቅፈዉ ወደ ሆስፒታል ሲጓዙ ክንዳቸዉ ላይ ጋደም እንዳለ በዚያዉ ቀረ።አስራ-አንድ አመቱ ነበር።እንዳባት አዛኝ ናቸዉ።«የሐዘኑ ሕመም፥ ማብቂያ የለዉም።ሊድን አይችልምም።» ይሉ ነበር አቅላቸዉን እስከሳቱ ጊዜ ድረስ።

መፃናኛቸዉ አዲስ ፍቅራቸዉ ነበር።ጉር ከመሞቱ ከሰወስት ዓመት በፊት የመጀመሪያ ባለቤታቸዉን እሕት ሊልይን አግብተዉ ነበር።1963።ባመቱ ከቀድሞ አማቻቸዉና ከሁለተኛ ሚስታቸዉ የመጀመሪያዉን በሰወስተኛ ዓመቱ ሁለተኛዉን ወንድ ልጅ ወለዱ።አድናቂ ወዳጆቻቸዉ እንደሚሉት ሁለቱ ልጆች ጉርን ላጡን አባት ጥሩ መፅናኛ ነበሩ።የቀድሞ አማቻቸዉና ባለቤታቸዉም ሌሊም የቀድሞ ባለቤታቸዉ ምትክ፥ ጠንካራ ደጋፊቸዉም ሆኑ።

ሌሎች እንደሚሉት ግን የሌሎችን ተፈቃሪ ሚስት ልጆች ለመግደል-ማስገደል ሁለቴ ማሰብ አያስፈልጋቸዉም። መከላከያ ሚንስትር በነበሩበት ዘመን የእስራኤልን ጦር ወደ ሊባኖስ አዘመቱ።1982
«እዚሕ የመጣነዉ ለአንድ አላማ ብቻ ነዉ።አሸባሪዉን የፒ ኤል ኦ ፍልስጤም ድርጅትን ለማጥፋት ነዉ።»

ሻሮን አሸባሪን እንዲያጠፋ በሚል ሰበብ ባዘመቱት ጦር ሰብራ እና ሻቲላ የሚባሉትን የፍልስጤም ስደተኞች መንደርን መዉጪያ መግቢያ አስከበቡ።እስራኤል የምታስታጥቀዉንና የምታደራጀዉን የሊባኖስ ክርስቲያን ሚሊሻን ወደ ሁለቱ ሠፈራ መንደሮች አስገብተዉ ልጅ ካዋቂ ሳይለዩ ሰላማዊዉን ስደተኛ አስጨፈጨፉት።ከመስከረም አስራ-ስድስት እስከ አስራ-ስምንት በዘለቀዉ ዘመቻ ከሰባት መቶ እስከ ሰወስት ሺሕ አምስት መቶ የተገመተ የፍልስጤም ስደተኛ እና የሊባኖስ ሕዝብ ተረፈረፈ።ከብዙ ጫጫታ በሕዋላ ሻሮን ከመከላከያ ሚንስትርነቱ ሥልጣን ዞር ተደረጉ።በወንጀል የጠየቃቸዉ ቀርቶ ለመጠየቅ የቃጠ ዓለም የለም።ከጭፍጨፋዉ የተረፉ ፍልስጤሞች ግን ለመክሰስ ሞክረዉ ነበር።የሰማቸዉ የለም።ምክንያት አረባዊዉ ጋዜጠኛ ባሳም ካንተር እንደሚለዉ የአሜሪካ የማይነወጥ ድጋፍ ያላት ጠንካራ ሐገር ሐይለኛ ባለሥልጣንን ማን ደፍሮ ሊወነጅል።

«ምክንያቱም ሥልጣን ላይ ነበሩ።በዩናይትድ ስቴትስ መስተዳድሮች እና በዓለም አቀፉ ማሕበረሰብም እሳቸዉም ሆኑ እስራኤል ባጠቃላይ በሰብአዊ ፍጡር ላይ ለሚፈፅሙት ወንጀል ሽፋንና ድጋፍ ሥለሚሰጣቸዉ ነዉ።»

የግብርና ሚንስትር ሲሆኑ እንደ ጄኔራል በሐይል የያዙትን የፍልስጤም መሬት ለአይሁዶች ያከፋፍላሉ።የቤቶች ሚንስትር ሲሆኑ በሐይል በተያዘዉ ግዛት የአይሁድ ሠፈራ መንደር ያስገነባሉ።አንድ ነገር ግን ብዙ ጊዜ ሞክረዉ፥ አልመዉ አልተሳካላቸዉም።የፍልስጤም ነፃ አዉጪ ድርጅት ሊቀመንበር ያሲር አረፋትን ማስገደል።

በ1982 ሊቀመንበር ያሲር አረፋትን ለማስገደል አስራ-ሰወስት ጊዜ ሞክረዉ ነበር። አልሆነላቸዉም። አረፋት በአሜሪካኖችና በምዕራብ አዉሮጶች የተደገፈዉን የሠላም ስምምነት በመፈረማቸዉ የዓለምን ታላቅ የሠላም ሽልማት ኖቤልን ከተቀበሉ በኋላ እንኳን ለሻሮን መገደል የነበረባቸዉ አሸባሪ ነበሩ።

Kunst Installation Ariel Scharon

«ያሲር አረፋት አሸባሪ ብቻ ሳይሆን የጦር ወንጀለኛም ለመሆኑ ሁሉንም መመዘኛ ያሟላል።»

አረፋትን ለማጥፋት እንደዛቱ በሁለት ሺሕ ሁለት የአረፋትን ቢሮ በታንክ አስከብበዉ መዉጫ መግቢያ አሳጧች።የፍልስጤሞቹ የነፃነት ተፋላሚ እስካሁን ምክንያቱ በሚያወዛግብ በሽታ ታመዉ በቃሬዛ ከቢሯቸዉ እንደወጡ በዚያዉ ቀሩ።ለሻሮን በርግጥ ደስታ ነበር።ለመደሰት ግን ብዙ ጊዜ አላገኙም፥ እሳቸዉ ታመዉ ወደቁ።ሁለት ሺሕ ስድስት።


ግዙፉ፥ ወፍራሙ፥ ሐይለኛዉ የጦር ሰዉና ፖለቲከኛ ከአስራ-አራት ዓመታቸዉ ጀምሮ ዓለምን እንዳዛገቡ፥ እንዳከራከሩ ኖረዉ ስምንት ዓመት የማያዉቁትን ዓለም ተሰናበቱት።ዛሬ ተቀበሩ። ሰማንያ አምስት አመታቸዉ ነበር።ሥለ ማሕደረ ዜና አስተያየት የላካችሁልንን አመሰግናለሁ። ሌሎቻችሁም አስተያየታችሁን በደብዳቤ፥ በስልክ፥ በኢሜይል፥ በኤስ ኤም ኤስ ላኩልን።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic