1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ቴክኒክኢትዮጵያ

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች:አፍራህ ሁሴንና የፈጠራ ስራዎቿ

ዓርብ፣ ኅዳር 20 2017

አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI)ን ተጠቅማ የፈጠራ ስራዋን በመከወን ላይ የምትገኘው አፍራህ ሁሴን ደረጃዎችን መውጣት የሚችል የአካል ጉዳተኛ ወንበር (ዊልቸር)ከመስራት ጀምሮ የሌሎች የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤት ናት፡፡ ማየት ለተሳናቸው የሚረዳ ጽሁፍን ወደ ድምጽ መቀየር የሚችል ማንበቢያም ሰርታለች።

https://p.dw.com/p/4n9qn
አፍራህ ሁሴን ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሱመያ ሳሙኤል ጋር
አፍራህ ሁሴን ከዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች ዘጋቢ ሱመያ ሳሙኤል ጋርምስል Seyoum Getu/DW

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች:አፍራህ ሁሴንና የፈጠራ ስራዎቿ

አፍራህ ሁሴን ከእህቷ ሱመያ ሁሴን ጋር ሆነው ገና በታዳጊነታቸው የጀመሩት የፈጠራ ስራ ክህሎት አሁን አሁን ተስፋ ሰጪ እርምጃዎችን በመራመድ ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግሯታል፡፡ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በኤሌክትሪካል እና ኮምፒዩተር ምህንድስና የመጀመሪያ ድግሪ ተማሪ የሆነችው ወጣት አፍራህ፤ ዩኒቨርሲቲው ባላት የላቀ ክህሎት በሸለማት የማስተርስ ስኮላርሺፕ ፕሮግራም በኮምፒዩተር ምህንድስና የሁለተኛ ዓመት ተማሪም ናት፡፡
ወጣቷ ለቴክኖሎጂ እና ችግር ፈቺ የፈጠራ ስራዎች ባላት ቁርጠኛ አቋሟ አዎንታዊ ውጤት ያላቸው ተግባራትንም ትሰራለች፡፡ የ2024 የአርቲፊሻል ኢንተሌጅንስ ስኮላር የሆነችው አፍራህ የፈጠራ ብቃቷ እና ለዘርፉ ያላት ፍላጎት የተለያዩ ዓለማቀፍ ስብሰባዎች ተሳትፎን ከማመቻቸት ጀምሮ ከዓለማቀፍ ኢንደስትሪ መሪዎች ጋር እስከማስተዋወቅ የደረሰ በርካታ የስራ እና ክህሎት ግንኙነት እድልንም አመቻችቶላታል፡፡

አካል ጉዳተኞችን የሚያግዙት የእህትማማቾቹ ፈጠራ
ለቴክሎሎጂ ቅርብ የሆኑ ቤተሰቦቿ ለዚህ ፈጠራዋ መልካም እድል ሆኖላት እንዳሳደጓት የማትሸሽገው አፍራህ ከልጅነቷ ጀምሮ ለፈጠራ ቅርብ ሆና ማደጓንም ታብራራለች፡፡ ከመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷ ጀምሮ በዚህ የፈጠራ ስራዋ በመታወቅም በተለያዩ ጊዜያት የፈጠራ ስራ ውድድሮች ላይ እየተሳተፈች እራሷን በማብቃት መንገዱንም ተያይዛለች፡፡ ለትምህርቷ ያላት ቁርጠኛ ክትትል ለፈጠራውም ስኬት ጉልህ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ታብራራለች፡፡
በተለይም ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷ ጀምሮ በተለያዩ ባገኘቻቸው እድሎች የተከታተለቻቸው የስልጠና መርሃግብሮች ዛሬ ላይ እያሳካች ላለችው የፈጠራ ስራዎች ጉልህ አበርክቶ እንዳለውም እምነቷ  ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የቤተሰቦቿ እና የቀድሞ መምህራኖቿ አስተዋጽ የጎላውን ስፍራ እንደሚይዝ ታስረዳለች፡፡

GOM Äthiopien Oskills Gründerin Afrah Hussen
ምስል Seyoum Getu/DW


 የምታየው ተግዳሮቶች ለፈጠራዋ መነሻ ምክንያት ናቸው፡፡ ለአብነትም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘን ዊልቸር ስትፈጥር አካል ጉዳተኞች ደረጃን ለመውጣት የሚያሳልፉትን ብርቱ ፈተና መመልከት በቂዋ ነበር፡፡ 
በAI የሚንቀሳቀስ ደረጃዎችን መውጣት የሚችል የአካል ጉዳተኞች ወንበር (ዊልቸር) ከመስራት ጀምሮ ማየት ለተሳናቸው የሚረዳን ጽሁፍን ወደ ድምጽ መቀየር የሚችል መጽሃፍ ማንበቢያን ጨምሮ የበርካታ ፈጠራዎች ባለቤትም ናት፡፡

አፍራህ በፈጠራዋ በርካታ አገራዊ እና ዓለማቀፋዊ እውቅናዎችን አግኝታለች።  “AI for good” በተሰኘው የአርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ ጉባኤም ለመሳተፍ  ወደ ጄኔቫ እና ሌሎች የውጭ ሀገራት ከተሞች ተጉዛለች።  የ2024 “AI scholar” ለመባልም በቅታለች፡፡
በፈጠራ ስራው እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ ቀላል አልነበረም የምትለው አፍራህ በተጓዘችበት የመፍጠር መንገድ የሚገጥሙ ተግዳሮቶችን ይፈታል ብላም በማመን ከሌላኛዋ የፈጠራ ክህሎት ባለሙያ እህቷ ጋር በመሆን O-skills  የተሰኘ ቤተሙከራ እና ዎርክሾፕ ያለው የስልጠና ተቋምም ከፍተው ለበርካቶች አይን ገላጭ ሆነዋል፡፡
በተለይም በተለያዩ አገራት ለዎርክሾፕ በተዟዟረችባቸው አጋጣሚዎች አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስን ወደ አገሯ በማምጣት የጎላ ስራ ላይ እንዲውል ከማድረግ አንጻር ከፍተኛ ፍላጎት አድሮባታል፡፡ እሷ ያሳለፈችው የፈጠራ ጥረት ተግዳሮቶች እሷን በመሰሉ ላይ እንዳይደገም በማሰብም የተለያዩ የፈጠራ ስራ ግብዓቶችን በማሟላት O-skills የፈጠራ ክህሎት ማሰልጠኛ ማዕከልን ስለማጠናከር ታልማለች፡፡ 

ዝምታ ሰባሪ አዳጊ ሴቶች: የፈጠራ ክህሎት ኮከብ

#ዝምታሰባሪአዳጊሴቶች #GirlzOffMute

ሱመያ ሣሙኤል /ሥዩም ጌቱ

ልደት አበበ