አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያምና የቀጠለው እስራት፣ ግድያ | የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት | DW | 17.03.2018
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

አርቲስት ፍቃዱ ተ/ማርያምና የቀጠለው እስራት፣ ግድያ

ባለፍነው ቅዳሜ ሞያሌ ከተማ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸመውን የግድያ ጥቃት በተመለከተ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በርካታ አስተያየቶች ተሰጥተዋል።  ከግድያው ባሻገር ሰዎች ለስደት እና ለእስር መዳረጋቸውም አነጋጋሪ ኾኗል። ለታዋቂው የጥበብ ሰው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሕክምና ትብብር መጠየቁም ሌላዉ ጉዳይ ነው።

ሣምንቱ የተንደረደረው ያለፈውን ሳምንት አስደንጋጭ ክስተት በማንገብ ነበር። ባሳለፍነው ቅዳሜ ከኬንያ ተጎራባቿ የሞያሌ ከተማ ነዋሪዎች በመከላከያ ሠራዊት ግድያ እንደተፈጸመባቸው መገለጡ በርካቶችን አስደንግጧል። ግድያውን ተከትሎ በዐሥር ሺህዎች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ወደ ጎረቤት ሃገር ኬንያ ተሰደዋል። ግድያ እና እስራቱ መቀጠሉን የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች መነጋገሪያ አድርገውታል። በኢትዮጵያ የቴአትር እና ጥበባዊ ሥራዎች ዘርፍ ከፍተኛ ከበሬታን የተጎናጸፈው አንጋፋው አርቲስት ፍቃዱ ተክለ ማርያም ሁለቱ ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ መኾናቸው እና ርዳታ ሊደረግለት እንደሚገባ መገለጡም ሌላኛው መነጋገሪያ ነበር። ለአንጋፋው አርቲስት ርዳታ ከሚያስተባብሩት መካከል አንዱን አነጋግረናል። 

ባሳለፍነው ሳምንት መገባደጃ ቅዳሜ እለት በርካቶችን ያስደነገጠው ዜና በሣምንቱም መነጋገሪያ ኾኖ ነው የሰነበተው።  የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሞያሌ ከተማ ነዋሪዎችን በጥይት ከመግደላቸው ባሻገር በርካቶችን ያስደነገጠው መንግሥት ግድያው በስህተት የተፈጸመ መኾኑን በሀገሪቱ ዋናው የቴሌቪዥን ጣቢያ መናገሩ ነበር። የኢትዮጵያ ብሮድካስት ኮርፖሬሽን ማለትም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፦ «በሞያሌ አካባቢ አምስት የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተሳሳተ መረጃ ይዘው ባደረጉት እንቅስቃሴ የ9 ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በ12 ሰዎች ላይ የመቁሰል አደጋ ደርሷል» ሲል ያተተበት የቪዲዮ ምስል በርካቶች ዘንድ ደርሷል። 
የአሮሚያ ክልል የፍትህ ቢሮ የኮሙኒኬሼን ጉዳዮች ኃላፊ አቶ ታዬ ዳንዳኣ በበኩላቸው ግድያው በተፈጸመ ማንግስት «የምን ስህተት? ሊሆን አይችልም!» ሲሉ በፌስቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። «ትናንት ሞያሌ ላይ ከ10 ያላነሱ ንፁሐን ዜጎች ሲገደሉ ከደርዘን በላይ ቆስለዋል። ወንጀሉን የፈፀሙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ናቸዉ» ብለዋል። «ኮማንድ ፖስት ደግሞ "ጭፍጨፋዉ የተፈፀመዉ በስህተት ነዉ" ይላል ያሉት አቶ ታዬ «ይህ በንፁሐን ደም መቀለድ ነዉ!» ሲሉ አክለዋል።  

አቶ ታዬ ጽሑፋቸውን ሲቀጥሉ፦ «በጠራራ ፀሓይ ያን ያህል ህዝብ መፍጀት ፈፅሞ በስህተት ሊሆን አይችልም» በማለት ነው። ግድያውም «በኮማንድ ፖስቱ የበላይ ኃላፊዎች ታቅዶ የተፈፀመ የጅምላ ጭፍጨፋ ስለመሆኑ ጥርጥር የለዉም» ብለዋል። «ከመነሻዉ አዋጁን አጭበርብረዉ ያሳለፉት ለዚሁ ነበር። ተጠያቂነት ካለ የላይኞቹን ማየት ነዉ! በነገራችን ላይ በኮማንድ ፖስት የላይኛዉ ኮሚቴ ዉስጥ አንድም ኦሮሞ አልተካተተም። ይህ ለምን ሆነ? በቂ ምክንያት ይኖረዋል» ሲሉ ጽሑፋቸውን በጥያቄ አጠቃለዋል።  

አቶ ታዬ ትናንት ማለትም ሐሙስ ለእስር መዳረጋቸው በትዊተር እና ፌስቡክ ገጾች ላይ በስፋት ተነግሯል። እሸቱ ሆማ ቄኖ፦«ታዬ ደንደአ የተሸወደው ለዘመናት አስረው ካሰቃዩት አውሬዎች ጋር ለመሥራት ሰተት ብሎ የገባ ዕለት ነው። ዞምቢ ሁሌም ዞምቢ ነው» ሲል ትዊተር ላይ ጽፏል። 

እምቢበል ኢትዮጵያ የሚል የፌስቡክ ገጽ ላይ የቀረበ የጽሑፍ መልእክት ደግሞ የአቶ ታዬ እሁድ ዕለት በፌስቡክ ያቀረቡት ጽሑፍ ተያይዞበታል። የእምቢበል ጽሑፍ ላይ፦ «ሕዝብ ሲጎዳ ለሕዝብ ለመቆም ሰው ሆኖ መፈጠር ብቻ በቂ ነው» የሚል ጽሑፍ ይነበባል። «ግድያው ስህተት አይደለም በማለታቸው ለእስር የተዳረጉት አቶ ታዬ ደንዳአ» ከሚል ጽሑፍ ጋር የዩቲውብ የቪዲዮ ምስል በትዊተር ገጹ ያያዘው ደግሞ እሸቱ ቀጸላ ነው።

ሞያሌው ከተማ ውስጥ በስህተት ነው የተገደሉት ከተባሉት ሟቾች መካከል የ10 ዓመት ልጅ እንደሚገኝበት የሚያሳይ ፎቶግራፍም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ይታያል። እዮብ መሣፍንት ትዊተር ላይ፦ «በሞተር ሳይክል የሚሄድን ወጣት ቁም ብለህ ከቆመልህ በኋላ እጁን ወደላይ አድርጎ ፈትሸህ ምንም እንዳላያዘ አረጋግጠህ እዛው መሀል አስፓልት ላይ በጥይት ከደፋኸው ስህተት ሳይሆን ማን አለብኝነት ነው» ሲል ጽፏል። አባንጋ ድሬ፦«ነገስ የት ይሆን?» ሲል ጠይቋል። «አውቆ መሳሳት!ያሳዝናል» የፍሬው መልእክት ነው። 

«ለእናንተ የንፁሐን ሕይወት ቁጥር ብቻ ነው። "ስህተት" ያላችሁት አውሬነት ስንት ልብ እንደሚሰብር፤ የስንቱን ቤተሰብ ሕይወት እንደሚያናጋ፤ ስንት ከጥላቻ ጋ ሲታገል የሚኖር ትውልድ እንደሚያፈራ ምን ገዷቹ» ያለችው ደግሞ ሙኒራ ናት። አስተያየቶቹ በትዊተር የተሰጡ ናቸው። በፌስቡክ በስፋት ከተሰራጩ መልእክቶች መካከል፦ «በሞያሌ ቦረና ዞን አሁንም ውጥረት መኖሩ ታወቀ» «ሞያሌ አነባች» የሚሉ መልእክቶች ይገኙበታል። ቲጂ የአርበኞች ልጅ የሚል የፌስቡክ  ገጽ ላይ «ሞያሌ በገዛ ሀገራቸው መቀመጫ ያጡት ወገኖቻች ተሰደው ወደ ኬንያ እያመሩ ነው!» ብላለች። 

Äthiopien Jubiläum 60 Jahre National Theater

አርቲስት ፈቃዱ ተክለማርያም በብሔራዊ ቴአትር 60ኛ ዓመት በዓል ወቅት

በሞያሌ የተፈጸመውን ግድያ ተከትሎ የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከስምንት ሺህ እስከ ሃምሳ ሺህ እንደሚደርሱ ዓለም አቀፍ የማሰራጪያ ጣቢያዎች መረጃን ያጣቀሱ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ዘገባዎች ይጠቁማሉ። 

ታዋቂው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሁለት ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጪ መኾናቸው ትናንት በጋዜጣዊ መግለጫ መነገሩ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት መነጋገሪያ ኾኗል። 

«ታላቁ የጥበብ ሰው አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም ሁለቱ ኩላሊቶቹ ከጥቅም ውጭ ሆኑ!»  በርካቶች የተቀባበሉት መልእክት ነው። ለአርቲስቱ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና በተለያዩ መንገዶች ድጋፍ እንዲደረግ በአስተባባሪነት በተዋቀረው ኮሚቴ በምክትል ሊቀመንበር እያገለገለ የሚገኘው የሮኆቦት ፕሮሞሽን ባለቤት ኃይሉ ከበደን አነጋግረናል።  
 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሸዋዬ ለገሰ

Audios and videos on the topic

ተዛማጅ ዘገባዎች