አሜሪካ፤ ምርጫውና የኤኮኖሚው ፖሊሲ | ኤኮኖሚ | DW | 31.10.2012
 1. Inhalt
 2. Navigation
 3. Weitere Inhalte
 4. Metanavigation
 5. Suche
 6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

አሜሪካ፤ ምርጫውና የኤኮኖሚው ፖሊሲ

ዩ-ኤስ-አሜሪካ ውስጥ በፊታችን ማክሰኞ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል።

ዩ-ኤስ-አሜሪካ ውስጥ በፊታችን ማክሰኞ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይካሄዳል። በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማና በሬፑብሊካኑ ተፎካካሪያቸው በሚት ሮምኒይ መካከል እስካሁን ሲካሄድ በቆየው የምርጫ ትግል የአገሪቱን የኤኮኖሚ ፖሊሲ ያህል በጣም ያከራከረ ሌላ ጉዳይ የለም። የአገሪቱ ስራ አጥ ቁጥር አሁንም ከስምንት በመቶ አልወርድ ብሎና የመንግሥቱም የበጀት ኪሣራ ከባድ እንደሆነ መቀጠሉ ሲታሰብ እርግጥ ይህ አስደናቂ ነገር አይሆንም። በሌላ አነጋገር የኤኮኖሚው ፖሊሲ በምርጫው ውጤት ላይ የተለየ ወሣኝ ተጽዕኖ እንደሚኖረው ከወዲሁ ግልጽ ነው።

በሁለቱ ዕጩዎች በፕሬዚደንት ባራክ ኦባማና በተቀናቃኛቸው በሚት ሮምኒይ መካከል በኤኮኖሚ ፖሊሲ ረገድ ያለው ልዩነት የሰማይና የምድር ያህል ነው። በማሣቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት አንድሬያ ሉዊስ-ካምፕቤል በቅርቡ ከዶቼ ቬለ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ሁለቱን ፖለቲከኞች እንዲህ ነበር ሲያነጻጽሩት።

«በታክስና በወጪ በጀት ረገድ ትልቅ ልዩነት ነው ያለው። ፕሬዚደንት ኦባማ ከፍተኛ ገቢ ባላቸው ላይ ፌደራሉን የገቢ ግብር ለመጨመር ይፈልጋሉ። ሚት ሮምኒይ ደግሞ የሚመርጡት ግብሩ ከፍተኛ ገቢ ያላቸውን ጨምሮ ለሁሉም አሁን ባለበት ደረጃ መቀጠሉን ነው። በወጪ ረገድ ፕሬዚደንት ኦባማ ዋና ዋናዎቹን መንግሥታዊ የማሕበራዊና በጎ አድራጎት ፖሊሲዎች፤ ማሕበራዊ ዋስትናና ለአንጋፋ ዜጎች የተወጠነውን ሜዲኬርን ይዘው ለመቆየት ነው የሚፈልጉት። ሚት ሮምኒይ በአንጻሩ የምክትል ፕሬዚደንትነቱ ዕጩዋቸው ራያን ባቀረቡት ሃሣብ መሠረት እነዚህን ፕሮግራሞች ለመለወጥ ነው የሚሹት። ይህም የአሜሪካን መንግሥት ማሕበራዊ ወጪ በረጅም ጊዜ በሰፊው የሚቀንስ ነው»

ለነገሩ የሬፑብሊካኑ ወገን ዕጩ ሚት ሮምኒይ ስኬታማ የንግድ ሰውና የኩባንያዎች መድህን አድርገው ራሳቸውን ሲያቀርቡ አሜሪካ በወቅቱ ለምትገኝበት የኤኮኖሚ ቀውስ ምናልባት ለአንዳንዶች ሁነኛው ሰው መምሰላቸው አልቀረም። ታዲያ ይህ የሮምኒይ ዕምነት የሌሎችም ቢሆን ምርጫው አሁን ከወዲሁ አልቆለታል ለማለት በተቻለ ነበር።

ግን የወቅቱ ሃቅ ይህን አይመስልም። ባራክ ኦባማ ምንም እንኳ የአገሪቱ ኤኮኖሚ በጥሩ ሁኔታ ላይ ባይገኝም በአገር-አቀፍ ደረጃ በተካሄዱት በአብዛኞቹ የሕዝብ ዝንባሌ መጠይቅ ወጤቶች መሠረት ከሬፑብሊካኑ ተፎካካሪያቸው የተሻሉ ናቸው። ይህም በሁለት መንገድ ሊተረጎም ይችላል። ሚት ሮምኒይ የሬፑብሊካን ፓርቲያቸው ተቺዎች እንደሚሉት እስካሁን ለኦባማ የተሻሉት አማራጭ፤ ፕሮግራማቸውም ለአሜሪካ የሚበጀው መሆኑን ለሕዝብ በሚገባ ማስረዳት አልቻሉም ወይም ዴሞክራቶች እንደሚናገሩት መራጩ ሕዝብ የሮምኒይን ፕሮግራም ተረድቶ አልተቀበለውም ማለት ነው።

ያም ሆነ ይህ ሁለቱ ዕጩዎች በምርጫ ቅስቀሳቸው ከሚያነሷቸውን የኤኮኖሚ ፖሊሲ ነጥቦች ዓበይቱን ቀረብ አድርጎ ለመመልከት ያህል ባራክ ኦባማ በዓመት ከ 250 ሺህ ዶላር በላይ ገቢ ባለው ቤተሰብ ወይም ከ 200 ሺህ በላይ በሚያገኝ ግለሰብ ላይ ግብር ከፍ ለማድረግ ይፈልጋሉ። በሌላ አነጋገር ኦባማ የሚያቅዱት ለዚህ የሕብረተሰብ ክፍል የግብሩን መጠን ከ 35 ወደ 39,4 ከመቶ ለማሳደግ ነው። ይህ በባለጸጎች ላይ የሚደረግ የግብር ጭማሮ ደግሞ የተቀረውን ግብር ከፋይ ሕዝብ ድርሻ አሁን ባለበት መጠን ጠብቆ ለማቆየት በስራ ላይ እንዲውል ይታሰባል።

«ለመካከለኛው አሜሪካዊ የኦባማ ዕቅድ የወቅቱን የግብር መጠን ይዞ መቀጠል ማለት ነው። በባለጸጋው ላይ የሚጣለው ግብር በ4,4 ከመቶ መጨመር ወደ ፕሬዚደንት ክሊንተን ዘመን ደረጃ የሚመልስም ነው»

በካምብሪጅ የማሣቹሴትስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ ፕሬፌሰር አንድሬያ-ሉዊስ-ካምፕቤል እንደሚያስረዱት የኦባማ ዕቅድ ጥሩ ገቢ ላላቸው ለዘብ ያለ የግብር ጭማሮና ለአብዛኛው አሜሪካዊም ለውጥ የሌለበት ዕቅድ ነው።

ሮምኒይ በአንጻሩ ግብሩን በአጠቃላይ በሃያ ከመቶ እቀንሳለሁ ባይ ናቸው። በፔንሲልቫኒያ ዩኒቨርሲቲው የፊናንስ ፕሮፌሰር በሮበርት ኢንማን አባባል የሮምኒይ ዕቅድ ችግር ይህ የሃያ በመቶ ግብር ቅነሣ በምን እንደሚጣጣ የሚጠቁም አለመሆኑ ነው። ኢንማን በመሠረቱ የግብር ቅነሣውን ዕቅድ ይደግፋሉ። ሆኖም የሚያስረግጡት ሮምኒይ ይህን ለማድረግ በሌላ ቦታ ከፍተኛ የግብር ቅነሣን መሰረዝ እንደሚገደዱ ነው። በዚህ አካሄድ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ አሜሪካውያን ጠቃሚ የሆነው ከቤት ስራና ከማሕበራዊ መዋጮ የሚመለሰ ግብር እንደሚቀር ነው ካምፕቤል ደግሞ በፊናቸው የሚናገሩት።

«የሮምኒይና የራያን ዕቅድ ግብሩን ለአብዛኛው አሜሪካውያን ባለበት መጠን ማቆየትና ከፍተኛ ገቢ ላላቸው ደግሞ በጆርጅ ቡሽ ዘመን ከነበረውም የበለጠ የገቢ ግብር ቅነሣ ማድረግ ነው። ስለዚህም የሮምኒይ ዕቅድ የግብሩን ሸክም ከታላላቆቹ ይበልጥ በመቀነስ መካከለኛ ገቢ ባላቸው ላይ መጫን ይሆናል። ይሄ ፖሊሲ የሚያስከትለው ሌላው ነገር ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ዜጎች መጉዳት ነው። ለውጡ በቀላሉ እነዚሁ ጠቃሚ ድጎማ እንዲያጡ ያደርጋል»

ሮምኒይ ከዚህ ሌላ የውርስ ግብርን ለመሰረዝም ይፈልጋሉ። ኦባማ በበኩላቸው የዚሁኑ ግብር ከፍተኛ መጠን በ45 ከመቶ ለማቆየትና እስከ 3,5 ሚሊዮን ዶላር ንብረትን ደግሞ ከግብር ነጻ እንደሆነ እንዲቀጥል ለማድረግ ነው የሚሹት። ባራክ ኦባማ ከዚህ ሌላ የካፒታል ግብርን ወደ ሃያ ከመቶ ከፍ ለማድረግ የሚፈልጉ ሲሆን ሮምኒይ ይህንኑ በወቅቱ ባለበት 15 በመቶ መጠን አቆያለሁ ባይ ናቸው። ካምፕቤል እንደሚሉት በሮምኒይ ስር ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው ዜጎች የሚሰጠውን የግብር ተመላሽ ይቀነሳል። ይህ ደግሞ በዝቅተኛ ገቢ በሚተዳደሩት ላይ ግብርን የመጨመርን ያህል ነው።

የጤና ጥበቃ ፖሊሲን በተመለከተም ልዩነቱ ትንሽ አይደለም። የጤና ፖሊሲ ለነገሩ ማሕበራዊ ብቻ ሣይሆን የኤኮኖሚ ጉዳይም ነው። ከአሜሪካ አጠቃላይ በጀት ሃያ በመቶው አንድ-አምሥተኛው የሚወጣው ለጤና ጥበቃ ፖሊሲ ነው። ይህም አሜሪካ በዚህ መስክ ከየትኛውም አገር የበለጠ ወጪ እንዳለባት ያመለክታል። ግን የሚያሳዝነው ይህ ግዙፍ ወጪ እየተደረገም በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ አሜሪካውያን አሁንም የጤና ጥብቃ ዋስትና የሌላቸው መሆኑ ነው።

ሚት ሮምኒይ ባራክ ኦባማ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ያሰፈኑትን፤ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ መድህን ላልገቡ አሜሪካውያን ዋስትና የሚሰጥ የጤና ጥበቃ ለውጥ እንደሚያስወግዱ ለመራጮቻቸው ቃል ገብተዋል። የማሣቹሴትስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲቲዩት የፖለቲካ ፕሬፌሰር ካምፕቤል እንደሚናገሩት ከሆነ ይሄው ዕርምጃ ከስድሥት አሜሪካውያን አንዱ ያላንዳች የጤና ጥበቃ ዋስትና እንዲቀጥል የሚያደርግ ነው የሚሆነው።

ሮምኒይ ከዚህ ባሻገር የሚቀጥል የወቅቱን መንግሥታዊ የጤና እንክብካቤ ስርዓት የመለወጥ ዕቅድም አላቸው። እንደርሳቸው ከሆነ መንግሥታዊው የአንጋፎች የጤና ዋስትና ሜዲኬር በአንድ የክፍያ ዘዴ መተካት አለበት። በዚህ ዘዴ አንጋፋ ዜጎች የጤና ዋስትናቸውን በነጻው የመድህን ገበያ ላይ ራሳቸው ይከፍላሉ ማለት ነው።

እናም ካምፕቤል እንደሚሉት የግሉ ታሪፍ ከሚሰጣቸው ገንዘብ የበለጠ ከሆነ ልዩነቱን ከኪሳቸው መክፈል ግድ ሊሆንባቸው ነው። ይህ እርግጥ ያለማቋረጥ እያደገ የሚሄደውን የመንግሥት ወጪ ለመገደብ ፍቱን ዘይቤ ሊሆን ይችላል። ሆኖም ግን ከአሁኑ ከፍተኛ ወጪ ላለባቸው አንጋፎች ይብስ ሸክም የሚሆን ነው። ሮምኒይ መንግሥታዊውን የድሆች የጤና ጥበቃ ፕሮግራም የሜዲክኤይድ ድጎማም ለመቀነስ ያስባሉ። በወቅቱ ፕሮግራሙ የሚራመደው በዋሺንግተንና በፌዳራሉ ክፍለ-ሐገራቱ የጋራ ወጪ ነው።

በአሜሪካ ከፍተኛ ወጪ ከሚፈስባቸው ዘርፎች አንዱ የመከላከያው ዘርፍ ነው። የመከላከያው በጀት በወቅቱ ሃያ ከመቶ ገደማ ይጠጋል። ለንጽጽር አሜሪካ ባለፈው 2011 ያወጣችው የመከላከያ በጀት ከቻይኛ እንኳ በአምሥት ዕጅ ይበልጥ ነበር። ከዚሁ ወታደራዊ ልዕልና የተነሣ ዛሬ ኤኮኖሚው ብርቱ ቁጠባን በጠየቀበት ሰዓት የመከላከያው በጀት በዚህ መልክ ሊቀጥል አይችልም። ሆኖም ሮምኒይ ሆኑ ኦባማ በወታደራዊ ወጪ ረገድ ወሣኝ ቅነሣ የማድረግ ዕቅድ የላቸውም። በምርጫው ቅስቀሳው ሂደት ሮምኒይ ኦባማን የጦር ሃይሉን በማዳከም ሲወቅሱ ተሰምተዋል። ከአጠቃላዩ የአገሪቱ ብሄራዊ ምርት አንጻር አራት በመቶ የሚደርሰው በጀት ባለበት ይቀጥላል ነው የሚሉት። ይህ በተጨባጭ ሲሰላ የወጪ መጨመር ማለት ነው።

ካምፕቤል እንደሚሉት ብዙው ዜጋ የመከላከያው በጀት ምን ያህል እንደሆነ በሚገባ አያውቅም። ሆኖም ሕብረተሰቡ የጦሩ ዘርፍ ብዙ የሥራ ዕድልን የከፈተ በመሆኑና ወታደራዊ ልዕልናውንም ስለሚደግፍ ከፍተኛ ወጪ መደረጉን የሚቀበለው ነው። ያስገርማል ፔንታጎን ራሱ የማይፈልጋቸውን አንዳንድ የመሣሪያ ዘዴዎች ሊያስወግድ አልቻለም፤ ብሄራዊው ሸንጎ የሆነ እንደራሴው የመጣበትን የምርጫ አካባቢ የሚጫን ሆኖ ካገኘው በቬቶ ስለሚያግደው!

«የመከላከያ በጀት ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ጉዳይ ነው። በአንድ በኩል አሜሪካ ለመከላከያ የምታወጣው በጀት ሰላሣ ሃገራት በአንድ ተደምረው እንኳ አይደርሱበትም። እጅግ ግዙፍ ነው። ይሄ ታዲያ ለመዋቅራዊ ግንባታ ወይም ለማሕበራዊ ተግባር በስራ ላይ ቢውል ትልቅ ነገር በሆነ ነበር። ግን የመከላከያ ጉዳይ አሜሪካ ውስጥ ውስብስብ ባሕርይ ያለው ነገር ነው። የመከላከያ በጀትን መቁረጡ ቀላል ነገር አይደለም። ምክንያቱም ብዙ ተጠቃሚዎች አሉ። በአገሪቱ አካባቢ ብዙ የጦር ሰፈሮች፣ ወታደራዊ መዋቅሮች፣ መሣሪያዎችና ሌሎች ከመከላከያው ዘዴ ጋር የተያያዙ ነገሮች መኖራቸው መዘንጋት የለበትም። ስለዚህም ለውጥ ቢፈለግ እንኳ ብሄራዊው ሸንጎ ውስጥ መሰናክል ማጋጠሙ የማይቀር ነው»

የሆነው ሆኖ መጪው የአሜሪካ ፕሬዚደንት እንድ እስካሁኑ ሁሉ በተቀዳሚ የአገሪቱን የኤኮኖሚ ችግር የመታገል ብርቱ ፈተና ይጠብቀዋል። ከጆርጅ ቡሽ የደቀቀ ኤኮኖሚና ከባድ የዓለምአቀፍ ፊናንስ ቀውስ ቅርስ የተረከቡት ኦባማ በተለይም የሥራ አጡን ቁጥር በመቀነስና የኤኮኖሚውንም ቀውስ በጥቂቱም ቢሆን በማለዘብ የሚቻለውን ማድረጋቸውን ከዴሞክራቶች ባሻገር ብዙዎች መስክረውላቸዋል። በሌላ በኩል የሚት ሮምኒይ ፖሊሲ ቢመረጡ ምን ያመጣል፤ የዛሬ ሣይሆን የነገ ጥያቄ ነው። የፖለቲካ ፕሮፌሰሯ አንድሬያ-ሉዊስ-ካምፕቤል በበኩላቸው ኦባማ በባለጸጎች ላይ ግብር በመጨመር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የመንግሥት ወጪ ለመሸፈን ያላቸው ዕቅድ እንደሚሰምር ነው የሚመኙት።

መሥፍን መኮንን

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic

 • ቀን 31.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16Zjk
 • ቀን 31.10.2012
 • አዘጋጅ
 • ያትሙ ገፁን ያትሙ
 • Permalink https://p.dw.com/p/16Zjk