አሜሪካዊ ጡረተኛ ፖሊስ ከ1/1/1994 የሽብር ጥቃት በኋላ | 1/1994 | DW | 09.08.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

1/1994

አሜሪካዊ ጡረተኛ ፖሊስ ከ1/1/1994 የሽብር ጥቃት በኋላ

ግሌን ክላይን ይባላሉ። አሜሪካዊ ጡረተኛ ፖሊስ ናቸው።

default

አሜሪካዊው ጡረተኛ ፖሊስ ግሌን ክላይን

ከአስር ዓመት በፊት አሜሪካ ላይ በደረሰው የሽብርተኖች ጥቃት በርካቶች ከሚደረመሱት ህንፃዎች ሲሸሹ እሳቸው ግን ወደ ህንፃዎቹ ይሮጡ ነበር። የኒውዮርኩ ግዙፉ ዓለም አቀፍ የንግድ ማዕከል በአሸባሪዎች በተጠለፉ የማጓጓዣ አውሮፕላኖች ተመትቶ ከመንታ ህንፃዎቹ መካከል አንደኛው ህንፃ ሳይደረመስ በፊት ነበር በቦታው የደረሱት። ከጥቃቱ ዘጠኝ ወራት በኋላ ደግሞ ፍርስራሾቹን ለማፅዳት በቦታውም ተገንተዋል። እነዚህ ክስተቶች ታዲያ በህይወታቸው ላይ ታላቅ ለውጥ አስከትለዋል። ለውጡ ዛሬም ድረስ አብሯቸው እንደተከተላቸው ነው። ደወል

ቤቱ አሜሪካን ውስጥ በብዛት የሚታዩት መንደሮች ውስጥ እንደሚገኙ ቤቶች አይነት ነው።ከቤቱ ፊት ለፊት የሚገኘው መስክ ላይ የበቀለው ሳር አረንጓዴ ቀለም ጎልቶ ይታያል። አጥሩ ነጭ ሲሆን፤ መቃው አጠገብ የተሰቀለው ደወል እያቃጨለ ነው። ኮኮ የተሰኘችው የሶስት ዓመቷ ድንክዬ ውሻ እኛን ስታይ ጭራዋን እያወዛወዘች ተጠጋችን። «አትናካም ሰው ትወዳለች» አሉን ባለቤቷ ግሌን ክላይን። ጡረተኛው የቀድሞ የፖሊስ ባልደረባ ግሌን ስላለፉት አስር ዓመታት ለመናገር ዝግጁ ናቸው። ባለቤታቸው ካሮል ግን ከጋዜጠኞች ጋር ማውራቱን አይፈቅዱም።

«ምክንያቱ» አሉ ግሌን «ምክንያቱ ያኔ የዛሬ አስር ዓመት ግድም ባለቤቴ ኩላሊቷን ለስራ ባልደረባዬ መለገሷ ነው። ያኔም የዜና አውታሮች ባጠቃላይ ሊጠይቋት መጥተው ነበር። እሷ ግን ልገሳውን ያደረግኩት ለዕይታ ብዬ አይደለም ብላ ለአንዳቸውም መግለጫ ከመስጠት ተቆጠበች። በተለይ ባልደረባዬ የተጎዳው በአሸባሪዎች ጥቃት በተደረመሱት የኒውዮርክ መንታ የንግድ ማዕከላት ፍርስራሽ ውስጥ ሲሰራ ነበር። ከዚያን ግዜ አንስቶ ስለዛ ከማንም ጋር አታወራም» አሉና ለአፍታ በሀሳብ ጭልጥ አሉ። እንደ ባልደረባቸው ሁሉ ግሌን በተደረመሱት ህንፃዎች ውስጥ የመጨረሻዎቹ ፍርስራሾች እስኪወገዱ ድረስ በማፅዳት ተግባር ለዘጠኝ ወራት አገልግለዋል።

«ያኔ ይመስለኛል የጨጓራና የአንጀት ችግር የጀመረኝ። የጨጓራው በሽታ ጠንቶብኝ ነበር። አሁንም ድረስ አልተፈወስኩም። «የምትሰሩበት ንፁህና ለመተንፈስ አስቸጋሪ ያልሆነ ቦታ ነው» ተብለን የነበረ ቢሆንም፤ ያ ግን ፈፅሞ ከእውነት የራቀ ነበር። እዚያ ጋር መንግስታችን ዋሽቶናል። የአክሲዮን ሽያጭ ገበያው እንዲነቃቃና ኒውዮርክ ዳግም ነፍስ ዘርቶባት እንድታንሰራራ ለማድረግ ይቻለው ዘንድ ዋሽቶናል»

በፍርስራሾቹ ውስጥ ለ800 ሠዓታት አለያም ከዚያ በላይ በማፅዳቱ ተግባር ተሰማርተው ነበር። የዛሬ አስር ዓመት ግድም አሜሪካ ውስጥ በተፈፀመው የመስከረም አስራ አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃት ወቅት የጋዝ ጭንብል አጥልቀው በፍርስራሾቹ ውስጥ በትጋት አገልግለዋል። ኋላ ላይ ግን የመተንፈሻ አካላቸው ችግር ይገጥመዋል። የጭንብሉ ማጣሪያ ከፍርስራሾቹ ውስጥ የሚቦነውን የላመ አቧራ ማጣራት የሚችል አልነበረም። እናም ግሌን ይታመማሉ። በርግጥ ግሌን የመስከርም አስራ አንዱ የአሸባሪዎች ጥቃት በተፈፀመበት ዕለት እረፍት ላይ ነበሩ። ሆኖም ጥቃቱን እንደሰሙ ወዲያውኑ በእርዳታ ተግባሩ ለመሰማራት አመለከቱ።

«ሬዲዮ እያዳመጥኩ ነበር። አስታውሳለሁ፤ አንድ የፖሊስ ባልደረባ በሬዲዮ ውስጥ «ከህንፃው አካባቢ ባስቸኳይ ገሸሽ በሉ፣ ሰዎች ከፎቅ ላይ እየተወረወሩ ነው» እያለ ሲጮህ ትዝ ይለኛል። «አቤት አምላኬ፥ ምን እየተከናወነ ነው? ምን አይነት መዓት እየወረደ ነው?» እያልኩ በውስጤ ማሰላሰሌን አስታውሳለሁ»

ግሌን ወደ ንግድ ማዕከሉ መንታ ህንፃዎች ሲደርሱ አንደኛው ህንፃ ገና አልተደረመሰም ነበር። ዶግ አመድ ሆኖ ያገኙት ሌላኛው ህንፃ ግን 14 የስራ ባልደረቦቻቸውን ቀብሮ ነው የጠበቃቸው። ሁሉም ጤነኞች እና ለእርዳታ ብቁ የነበሩ፣ በልዩ ሁኔታ የሰለጠኑ ሰራተኞቸ ነበሩ። የህንፃው ፍርስራሽ ተጭኗቸው በጣር ላይ ይገኙ የነበሩ ሰላማዊ ዜጎችን ለማዳን ነበር ጥድፊያቸው። እንደማይሆን ሆነና ግን ፍርስራሹ እነሱንም ለዘለዓለሙ ቀበራቸው። ይህ ሰቀቀን ከግሌን አዕምሮ በቀላሉ የሚወጣ አይነት አይደለም። ከሃያ ዓመታት የፖሊስነት አገልግሎት በኋላ ጡረታ የወጡት ግሌን ከትውስታ ማኅደራቸው አልወገድ ያለውን የአዕምሮ ጭንቀት ለመቀነስ የተለያዩ ሐኪሞች ጋር ተመላልሰዋል።

በእርግጥ አሁን በተወሰነ መልኩ ሻል ቢላቸውም የሽብር ጥቃቱ ክስተት በውስጣቸው የፈጠረው ተፅዕኖ ወደ ጭንቀትና ድብርት ተቀይሮ ይመላለስባቸዋል። በነፍስ አድንና በሌሎች የዕርዳታ ተግባራት ተሰማርተው ከነበሩ ግለሰቦች መካከል የብዙዎቹ መታመምና በሞት መለየት ደግሞ የበለጠ ያስጨንቃቸዋል።

«ማብቂያ የለሽ ነው። እና እንዳልኩት፤ ኒውዮርክ ላይ ከደረሰው የሽብርተኞች ጥቃት በኋላ ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች እንደሞቱ እናውቃለን። እኛን ለማገዝ ከመላ ሐገሪቱ ከመጡት ፖሊሶችና የእሳት አደጋ መከላከያ ባልደረቦች መካከል በሽተኛ ሆነው የቀሩ ምናልባትም ህመማቸው ከሽብር ጥቃቱ ጋር የተያያዘ መሆኑን ሳይረዱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት በመቶዎች ይቆጠራሉ። ከነዚህ ሰዎች ጋር በፌዴራልም ሆነ በዓለም-አቀፍ ደረጃ የተቀናጀ ግንኙነት ስለሌለን እርግጡን ለመናገር ይከብዳል»

ግሌን በመስከረም 11ዱ የተከሰተውን የአሸባሪዎች ጥቃት መርሳት የማይቻል ነው ይላሉ። ደሴት ወስጥ ተደብቆ ቴሌቪዥን አለመመልከት፣ ጋዜጣ አለማንበብ፥ ከማንም ጋር አለማውራት ይቻል ይሆናል፤ የመስከረም አስራ አንዱን ጥቃት መርሳት ግን ፈፅሞ የማይቻል ነው ሲሉ ትዝታው ምን ያህል አስከፊ እንደነበር ከገፅታቸው ላይ በቀላሉ ማንበብ ይቻላል። ከዚህ ሁሉ ጭንቀት ጀርባ ግን መልካም ዜና አልታጣም። በባለቤታቸው የኩላሊት ልገሳ ዛሬም ድረስ ህይወቱን ማቆየት የቻለው ባልደረባቸው ጤንነቱ እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ነው።

ክሪስቲና ቤርግማን

ማንተጋፍቶት ስለሺ