1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አማራ ክልል በ1ዓመት ከ1 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተዋል

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2 2016

በአማራ ክልል የወባ በሽታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን የጤና ባለሞያዎች እና ነዋሪዎች አመልክተዋል ። ባለፈው አንድ ዓመት ከ1 ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ሲጠቁ፤ ከነኚህ ውስጥ 26ቱ ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል ።

https://p.dw.com/p/4i43P
Malaria Mosquito
ምስል James Gathany/AP/picture alliance

አማራ ክልል እስካሁን 26 ሰዎች በወባ መሞታቸው ተገልጧል

በአማራ ክልል የወባ በሽታ ከጊዜ ወደጊዜ እየተስፋፋ መምጣቱን የጤና ባለሞያዎች እና ነዋሪዎች አመልክተዋል ። ባለፈው አንድ ዓመት ከ1 ሚሊዮን 400 ሺህ በላይ ሰዎች በወባ ሲጠቁ፤ ከነኚህ ውስጥ 26ቱ ሕይወታቸው ማለፉን የጤና ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። ለበሽታው ስርጭት በክልሉ ያለው የፀጥታ ችግርና የግብዓት አቅርቦት እጥረት መሆኑ ተመልክቷል

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ሰሞኑን ከሌሎች አጋር አካላት ጋር ባዘጋጀው የውይይት መድረክ ላይ እንደተገለፀው በአማራ ክልል የወባ ስርጭት በከፋ ሁኔታ እየተስፋፋ ነው፡፡

በምዕራብ ጎንደር ዞን የቋራ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎች ክትትልና ቁጥጥር ባለሞያ አቶ ቀጠለ ፋሲል በወረዳው የወባ በሽታ ካለፈው ዓመት በእጥፍ ጨምሯል ብለዋል፡፡

«...በወረዳችን በተለይ ባለፉት ሶስት ዓመታት ካሉት የኢንቨስትመንት መደራሻዎችና በአካባቢው ካለው ፀበል ጋር ተያይዞ ሰፊ የወባ ስርጭት አለ፣ ከዚህ አንፃር በርካታ ወባ ታካሚዎች ቁትር አለ፣ የወረዳው ዋናው ጤና ችግርም ወባ ነው፣ በየሳምንቱ 800 ተማሚዎች ወደ ጤና ተቋም ይመጣሉ፣ ይህ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር እጥፍ ነው፡፡» ብለዋል ።

ደቡብ ጎንደር እስካለፈው ሳምንት ድረስ የወባ ታማሚዎች ቁጥር ከ100ሺህ በላይ ደርሷል

በደቡብ ጎንደር ዞን የደራ ወረዳ ጤና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊ ሲስተር ሙሉ ያለው በበኩላቸው በሽታው በእጅጉ መስፋፋቱን አስታውሰው፣ እስካለፈው ሳምንት ድረስ የወባ ታማሚዎች ቁጥር ከ100ሺህ በላይ ደርሷል ነው ያሉት ።

«ከባለፈው ዓመት ወባ በእጥፍ ጨምሯል፣ በ2016 ከፍተኛ ፈተኛ ነው የገጠመን፣ ግብዓት ከባሕር ዳር በራሳችን ወጪ በግል መኪና እስከማጓጓዝ ደርሰናል፣ ስርጭቱ አሁንም እየጨመረ ነው፣ እስካለፈው ሳምንት ብቻ 100ሺህ ሰዎች በወረዳው በወባ የተያዙ ናቸው፡፡ ባለፈው ዓመት በወረዳው አንድ ሞት ተመዝግቧል፣ በዚህ ዓመትም አንድ ታማሚ በወባ ሕይወቱ አልፏል ።»

እስካሁን 26 ሰዎች በወባ መሞታቸው ተገልጧል
እስካሁን 26 ሰዎች በወባ መሞታቸው ተገልጧልምስል pzAxe/IMAGO

የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ገስጥ ጥላሁን ወረርሽኙ እየከፋ መምጣቱን ጠቁመው  በክልሉ ከ1 ሚሊዮን 400ሺህ ሰዎች በወባ መያዛቸውን አስረድተዋል ። «በእኛ ክልል እስካሁን ባለው መረጃ ከ1.4 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ ተጠቅተው ምርመራ አግኝተዋል ህክምና አግኝተዋል ። የህ ክስተት እስካሁን ክምናውቀው የወባ ልምድ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው፣ በዚህ ከቀጠለ፣ በሚቀጥሉት ወሳኝ የወባ ወራት እጅግ አስከፊ ሰብአዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል አመላካች ነው ።»

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ባለው የፀጥታ ችግር፣ የአየር ለውጥ ምክንያትና ለወባ በሽታ እየተሰጠ ለው ትኩረት በማነሱ በሽታው መስፋፋቱን አብራርተዋል ።

እስካሁን 26 ሰዎች በወባ መሞታቸው ተገልጧል

የተቋሙ ከፍተኛ የወባ በሽታዎች ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ዳኛው እምሩ ባቀረቡት ጽሑፍ እንደመለከቱት የበሽታው ስርጭት በእጅጉ ተስፋፍቷል፣ እስካሁንም 26 ሰዎች በወባ መሞታቸውን አስረድተዋል ።

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ
የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ በዛብህ ምስል Aleminew Mekonnen/DW

«85 ከመቶ የሚሆነው የአማራ ክልል ህዝብ ለወባ የተጋለጠ ነው፣ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ የወባ ስርጭት እየጨመረ ነው ። በዚህ ዓመት 1 ሚሊዮን 400 ሺህ ሰዎች በወባ ታምመዋል፣ 26 ሰዎችም በበሽታው ታምመው ሕይወታቸው አልፏል ።»

የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ተቋም ምክትል ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ በመድረኩ እንደገለፁት መስሪያ ቤታቸውና ጤና ሚኒስቴር የበሽታውን ስርጪት ለመቀልበስ በትብብር ይሠራሉ ።

«እንደ ኅብረተሰብ ጤና ተቋምና እንደ ጤና ሚኒስቴር ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ነው ። በቅንጅት አብረን እንሠራለን ። አብረን ለመሥራት የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ ነን» ነው ያሉት ።

ከፌደራል ጤና ሚኒሰቴርና ኅብረተሰብ ጤና ተቋም፣ ከክልልና ከዞን እንዲሁም በአማራ ክልል ወባ በስፋት ከተስፋፋባቸው 34 ወረዳዎች የተውጣጡ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች ተሳትፈዋል ።

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ