አማራጭ የኃይል ምንጭ፤ መንግሥትና ተቋማት | ሳይንስ እና ኅብረተሰብ | DW | 11.05.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ሳይንስ እና ኅብረተሰብ

አማራጭ የኃይል ምንጭ፤ መንግሥትና ተቋማት

በኃይለኛ የባህር ወለል ነውጥና የውቅያኖስ ማዕበል ሳቢያ፤ ጃፓን ውስጥ በአቶም ኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ አደጋ ከደረሰ ወዲህ፤ ሰዎች የገነቡትና የሚገነቡት ማንኛውም አውታር ከተፈጥሮ አደጋ ሊጠበቅ እንደማይችል ፤

default

ከታዳሽ የኃይል ምንጮች መካከል አንዱ ነፋስ ነው።

ለዓለም ኅብረተሰብ ይበልጥ ግልጽ ሳይሆንለት እንዳልቀረ ይታሰባል። ጉዳዩ ካሳሳበቸውና ለአማራጭ የኅይል ምንጭ ዐቢይ ግምት ከሰጡት በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት አገሮች መካከል አንዷ ጀርመን ናት።

የጀርመን መንግሥት በአማራጭ የኃይል ምንጭ ላይ ላቅ ያለ ትኩረት ለማድረግ የተነሣሣውም በህዝብና በተቃውሞ ፓርቲዎችም ትግል ጭምር ነው። በኃይል ምንጭና በመሳሰለው ያተኮሩ ጠበብትና ሳይንቲስቶችም የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከታቸው አልቀረም። የፌደራሉ መንግሥት ፤ በፉኩሺማ ፣ ጃፓን የአቶም ጣቢያ አደጋ ከደረሰ በኋላ ወዲያው ያቋቋመው 17 ጠበብት የሚገኙበት የሥነ-ምግባር ኮሚሽን የተሰኘው አማካሪ ቡድን፤ የሚመራው በቀድሞው የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳይ ሚንስትር (CDU)ና የጀርመን ተመራማሪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት ማትያስ ክላይነር ሲሆን፤ ከኤኮኖሚ ፣ ሳይንስና ቤተ- ክርስቲያን የተወከሉም ይገኙበታል።

የጀርመን የምርምር ማኅበር ፕሬዚዳንት ማትያስ ክልይነር---

«እኔ በበኩሌ፣ እዚህ ላይ፣ በጥብቅ ማሳሰብ የምፈልገው ፣ ለጀርመን ኤኮኖሚ ፣ በዛ ያለ የንግድ ዘርፍ መኖሩን ነው። ለአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን፤ ለውጭም ፣ ማለት ለውጭ ገበያ ምርትን ማቅረብ የሚቻልበት ሁኔታም አለ።»

የሥነ-ምግባሩ ኮሚሽን መሪ የቀድሞው የተፈጥሮ ጥበቃ ጉዳይ ሚንስትር ክላውስ ቶዖፈር በበኩላቸው እንዲህ ነበረ ያሉት---

«የአየር ንብረትን እጅግ በሚጎዳ ላይ አላተኩርም። ለማኅበራዊ ኑሮ ጎጂ የሆነን ፣ሊደፋፈር የማይገባውን ፣ ዜጎችንም ብዙ ወጪ የሚያስወጣ፣ እንዲሁም በኤኮኖሚ ረገድ፣ የሥራ ቦታ የሚያሳጣውን አልደግፈውም።»

የተጠቀሰው አማካሪ ቡድን፤ እስከ ግንቦት 22 ቀን 2003 ዓ ም፣ የመጨረሻውን የጥናት ዘገባውን ለመንግሥት ያቀርባል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የአቶም ኃይል ማመንጫ ደኅንነት ኮሚሽን በበኩሉ፣ የ 17 ቱን የጀርመን የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች የቴክኒክ ይዞታ ለመመርመር ዘገባውን በተጨማሪ ማየት የሚፈልግ መሆኑ ተመልክቷል። የመንግሥት አማካሪው ኮሚሽን፤ ከአቶም ኃይል ምንጭ መገላገል የሚቻልበት ዘመን ዘገየ ቢባል እ ጎ አ፣ ከ 2021 ዓ ም በፊት መሆን ይኖርበታል ሲል በረቂቅ ውሳኔ ላይ መጥቀሱ፣ ለፀጥታ ጉዳይ ኮሚሽኑ አስገራሚ ሆኖ ታይቷል።

ግራም ነፈሰ ቀኝ ፤ የጀርመን የህዝብ እንደራሴዎች ም/ቤት(ቡንደስታኽ) እና የፌደራል ክፍላተ ሀገር አስተዳዳሪዎች ም/ቤት፤ ሁለቱም ም/ቤቶች፤ እስከ ሐምሌ 1 ቀን 2003 ዓ ም ፤ በጀርመን ሀገር በአቶም ኃይል ምንጭ መጠቀም የሚቻልበትን የጊዜ ገደብ ይደነግጋሉ ተብሎ ነው የሚጠበቀው።

መራኂተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል፣ Die Zeit(ጊዜ) ለተሰኘው ሳምንታዊ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፣ አገሪቱ በታቻለ ፍጥነት ከአቶም ኃይል ምንጭ በአጭር ጊዜ ውስጥ መላቀቋ ካልቀረ፤ በምትኩ፤ በጋዝ የሚሠሩ የኃይል ምንጭ አውታሮች መትከል ይኖርብናል ነው ያሉት። ጋዝ ፤ በተዘጉ የድንጋይ ከሰል ጣቢያዎች ምትክ ወዲያው ተተክሎ አገልግሎት መስጠት የሚችል፤ ወደ ከባቢ አየር የሚለቀው የተቃጠለ አየር(CO2) መጠንም እጅግ አነስተኛ ነው ሲሉም መራኂተ-መንግሥቷ ተናግረዋል።

በጀርመን ሀገር ከታወቁት የምርምር ተቋማት መካከል፣ እ ጎ አ በ 1949 ዓ ም የተቋቋመው Fraunhofer-Gesellschaft የፍራውን ሆፈር ማኅበር የተሰኘው የሳይንስ ምርምር ድርጅት፤ ጀርመን እ ጎ አ እስከ 2050 ዓ ም፤ ሙሉ- በሙሉ ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ መዛወር ትችላለች ሲል በጥናት የተደገፈ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫውን ትናንት ፤ ሙዑንሸን(ሙዩኒክ) ላይ የሰጡት፤ የተቋሙ ፕሬዚዳንት Hans- Jörg Bullinger ናቸው። እንደ ቡሊንገር አስተያየት፤ በሰሜን ባህር ፤ ከጠረፍ ወደ ባህር ገባ ብሎ በብዛት በሚተከሉ የብረት ምሰሶዎችና ግዙፍ ፉሪቶች አማካኝነት ከነፋስ የኤልክትሪክ ኃይል በሰፊው ማመንጨት ይቻላል።

ተቋማቸው፤ በተጠናከረ መልኩ፣ በታዳሽ የኅይል ምንጮች ላይ እንደሚያተኩር፤ የፀሐይ ኃይልን የአጠቃቀም ሥነ ቴክኒክ እንደሚያጎለብት፣ በቤት ሥራ ረገድም የቤት ክፍሎች ግድግዳዎች ሙቀት የሚሰጡበትንም ሆነ ሙቀት የማያባክኑበትን ቴክኒክም እንደሚያተኩርበት አያይዘው ነው የገለጡት። በአውሮፓ ፤ እ ጎ አ እስከ 2020 ዓ ም ድረስ፤ በታዳሽ የኃይል ምንጭ አውታሮች ዙሪያ ብቻ ለ 400,000 ሰዎች አዲስ የሥራ ቦታ ማስገኘት እንደሚቻል፣ ጠበብት ግምት አላቸው። ወደ አዲስ የኃይል ምንጭ ለመዛወር እስከ 2015 በያመቱ 20 ቢሊዮን ዩውሮ ወጪ መጠየቁ የማይቀር ነው።

ይህ የሚቻል ነገር ያሉት የፍራውንሆፈር ተቋም ፕሬዚዳንት ቡሊንገር፤ በተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል መጠንና የቤት ማሞቂያ ወጪን በሥነ-ቴክኒክ በማሻሻል ፣ በአጠቃላይ 730 ቢልዮን ዩውሮ መቆጠብ እንደሚቻል ገልጸዋል። በሚመጡት ዓመታት፣ አንድ በተቋሙ ትኩረት የሚደረግበት ጉዳይ፤ በከተሞች የኤልክትሪክ ኃይል መጠንን መቀነስ ይሆናል። ይህን ደግሞ በ Lithium ባትሪ በመጠቀም ተገልጋዮች፤ ወደፊት የራሳቸውን የኤሌክትሪክ ኃይል በቤት ውስጥ መሙላት ይችላሉ ሲሉም ሐንስ- ዮዖርግ ቡቲንገር ፤ የፍራውንሆፈር የምርምር ተቋም ፕሬዚዳንት አስረድተዋል።

ከትናንት በስቲያ የዓለም የአየር ንብረት ጉዳይ ም/ቤት፣እ ጎ አ እስከ 2050 ድረስ፣ በዓለም ዙሪያ፣ የፖለቲካና ኤኮኖሚ ድግፍ እስከተደረገለት ድረስ፤ ታዳሹ የኃይል ምንጭ 77 ከመቶ አገልግሎት መስጠት ይቻላል።

ዋና ጽ/ቤቱ በደቡብ ጀርመን ፣በሙዑንሸን የሚገኘው ፍራውንሆፈር ተቋም፣ በጀርመን በአጠቃላይ 60 ቅርንጫፍ የምርምር ጣቢያዎች አሉት። አምና፣ እ ጎ አ በ 2010 ዓ ም፤ ለምርምር 1,66 ቢሊዮን ዩውሮ የመደበ ሲሆን፤ ከሃቻምናው ጋር ሲነጻጸር የ 2% ጭማሪ ተደርጎበታል። በጀርመን አጠቃላዩ የፍራውንሆፈር ተቋማት ሠራተኞቹ ብዛት 18 ሺ ገደማ ነው።

(ድምፅ)-------

በዓለም ዙሪያ አስተማማኝ አለመሆኑ የተረጋገጠለት የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታር ወደፊት በሌላ ጠንቀኛ ባልሆነ ታዳሽ የኃይል ምንጭ እንዲተካ በጥሞና መምከርና እርምጃም በመውሰድ ላይ ያለችው ጀርመን የተቃጠለ አየርን መጠን ለመቀነስም ትኩረት በመስጠት ወደፊት በቤንዚንና ናፍጣ ሳይሆን በኤሌክትሪክና በሃድሮጂን ጋዝ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎችን ገና በሰፊው ገበያ ላይ ባይውሉም፣ ጥቂቶቹን ማቅረቧ አልቀረም። ይህን እርምጃ ከወሰዱት የአገሪቱ ታዋቂ የአውቶሞቢል ኢንዱስትሪዎች መካከል አንዱ፣ በአሽቱትጋርት የሚገኘው ዳይምለር ቤንዝ ነው። Merecedes B-Class F-Cell የተሰኙ 3 በሃይድሮጂን ጋዝ የሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ለናሙና ይታዩ ዘንድ፣ ከክፍለ-ዓለም ፣ ክፍለ-ዓለም 30,000 ኪሎሜትር ተጉዘው እንዲመለሱ ተሠማርተዋል። ይህ ፕሮጀክት ሥራ ላይ የዋለው፣ እ ጎ አ ጥር 30 ቀን 2011 ዓ ም፤ በዓለም ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አውቶሞቢል በጀርመን ሀገር የተሠራበት 125ኛ ዓመት በታሰበ ማግሥት ነው። በዓለም ዙሪያ እስካሁን የሃይድሮጂን ጋዝ ማደያ ጣቢያዎች 200 ብቻ ናቸው። «ኤፍ ሴል» አውቶሞቢል፤ የኤሌክትሪክ ሞተር 65 ኪሎዋት ጉልበት ያለው ነው። ፍጥነቱ፤ በ 14 ሴኮንድ ውስጥ ከ 0-100 ኪሎሜትር ይደርሳል። ከፍተኛ ፍጥነቱ፤ በሰዓት ከ 140 ኪሎሜትር እንዳይበልጥ ተደርጎ ነው የተሠራው። እስካሁን ፤ ለሙከራ፣ 60 «ሜርሰደስ ቤንዝ አፍ ሴል» ተሽከርካሪዎች በአውሮፓ ፤ ዩናይትድ እስቴትስና ጃፓን ነው የተሠማሩት።

የአቶም ኃይል ማመንጫ አውታሮች፣ በታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚተኩበት እርምጃ በዓለም አቀፍ ስምምነት የተቀናጀ እርምጃ ካልተወሰደ፣ ፋይዳ አይኖረውም። የአየር ንብረትን የማይበክሉ ተሽከርካሪዎች ሥምሪትም እንዲሁ!

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ