አመፅና ብቀላ በእስራኤል | ዓለም | DW | 04.07.2014
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

ዓለም

አመፅና ብቀላ በእስራኤል

የእስራኤል ፖሊስ ኢየሩሳሉም ዉስጥ ከፍልስጤም የተቃዉሞ ሰልፈኞች ጋ መጋጨቱ ተሰማ። ፍልስጤማዉያኑ በፅንፈኛ እስራኤላዉያን ሳይገደል እንዳልቀረ በሚገመተዉ ፍልስጤማዊ ታዳጊ ወጣት ቀብር የተሰባሰቡ እንደሆኑ አሶሲየትድ ፕረስ ከስፍራዉ ዘግቧል።

የፍልስጤም ሚሊሺያዎች ስድስት የሚሆኑ ሮኬቶችና ሞርታር ወደእስራኤል ቢተኩሱም ከእስራኤል ወገን ምላሽ አለመሰጠቱንም ዘገባዉ አመልክቷል። ሆኖም ቀኝ ዘመም እስራኤላዉያን ፍልስጤም ይዞታ ዉስጥ ተገድለዉ የተገኙትን ሶስት ወጣቶች ደም መበቀል አለብን የሚል ቅስቀሳቸዉን አጠናክረዋል። የእስራኤል የጦር ኃይል ወደጋዛ አካባቢ ተጨማሪ ወታደሮችን ከማሰማራቱ ቀደም ብሎ የአየር ጥቃት ሰንዝሯል። በአካባቢዉ የተባባሰዉን የአመፅ እንቅስቃሴ እስራኤላዉያን አይሁዶች ሁሉ እንደማይደግፉት የሚገልፁ ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች ተካሂደዋል።

እስራኤል ፍልስጤም ግዛት ዉስጥ ተገድለዉ የተገኙት ሶስት ወጣቶችን ደም የመበቀል ስሜት ተባብሷል። ለዚህም ቀኝ ዘመም እስራኤላዉያን የበቀል ርምጃ እንዲወሰድ በቁጣ እየቀሰቀሱ ነዉ። ብቀላዉ መፈጸም እንዳለበት የጠየቀ አንድ የፌስ ቡክ ገፅ በአጭር ጊዜ 37 ሺህ ደጋፊዎችን አግኝቷል። በገፁ ላይም «አረቦችን መጥላት ዘረኝነት አይደለም» የሚሉ አስተያየቶች ሰፍረዋል። የሰዎችን የቁጣ ስሜት ለማጋልም ከፖሊስ የተገኘዉ ከታገቱት አንዱ ጊላድ ሻር ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ በተንቀሳቃሽ ስልክ ያስተላለፈዉ መልዕክት ከኢንተርኔት ይደመጣል። የገዳዮቹ የደስታ ድምጽም እንዲሁ። ሶስቱ የሃይማኖት ተማሪ ወጣቶች አስከሬን ከተገኘ በኋላ ነዉ ዛሬ ስርዓተ ቀብሩ የተፈፀመዉ ፍልስጤማዊ ታዳጊ ወጣት የተገደለዉ። የልጁ ገዳዮች ፅንፈኛ እስራኤላዉያን ሊሆኑ እንደሚችሉ ነዉ የተገመተዉ። ምስራቅ ኢየሩሳሌም ዉስጥ በቡድን የተሰባሰቡ ፍልስጤማዉያን በእስራኤል ፖሊሶች ላይ ድንጋይ እና ጓዳ ሰራሽ ተቀጣጣይ ፈንጂዎችን ወርዉረዋል። ተሽከርካሪዎች ተቃጥለዋል።

ደቡብ እስራኤል ዉስጥም ከጋዛ ሮኬቶች ተወንጭፈዋል። የእስራኤል አየር ኃይልም በጋዛ መንደሮች የተመረጡ ኢላማዎችን ቀደም ብለዉ ደብድበዋል። ተጨማሪ ወታደሮቿንም እስራኤል ወደአካባቢዉ አንቀሳቅሳለች። ዓለም ዓቀፉ ኅብረተሰብ በመካከለኛዉ ምሥራቅ በተባባሰዉ የአመፅ እንቅስቃሴ ምክንያት መደናገጡን እስራኤል ዉስጥ የሚገኘዉ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት «የሴቶች የሰላም ማኅበር» አባል ማያን ዳክ ይገልጻሉ። እሳቸዉ እንደሚሉት በአካባቢዉ አመፁ የጀመረዉ ዛሬ ነዉ ብሎ የሚያስብ ካለ ተሳስቷል፤

«የዛሬ ሶስት ሳምንት ነዉ የጀመረዉ ብለን እንደየዋህ ማሰብ የለብንም። ከሺ ዓመታት በፊት የጀመረና አሁንም በየቀኑ የቀጠለ መነዉ። በተለይ ደግሞ ሁኔታዎች ሲባባሱ፣ ህዝቡ እንደመሪ የሚያያቸዉ ወይም ፖለቲከኞች ኃይላቸዉን ለመጠቀም ሲሞክሩ አመፁን ለማባባስ በህዝቡ ዉስጥ ያላቸዉን ስፍራ ይጠቀሙበታል።»

አያይዘዉ እንደገለፁትም አንዳዶች አመፁ እንዲባባስ ባይፈልጉም ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ወገኖች በተቃራኒዉ ግጭት መቆራቆሱ እንዲበርድ አይፈልጉም። ለዚህ ማሳያ እንዲሆናቸዉም ትናንት ቴልአቪቭ፣፣ ኢየሬሳሌም፣ ሃይፋና ቤርሼባ፣ ይህ አመፅ እኛን አይወክም በሚል ሰላማዊ ሰልፍ መካሄዱንም አመልክተዋል። አኗኗራችን ይህን አይፈቅድም ያሉት አይሁድ እስራኤላዉያን በሰልፉ ላይ ዘረኝነትን እንደሚቃወሙ ነዉ የገለፁት። እንዲህ ባለዉ ብቀላም እንደማያምኑም አመልክተዋል። ማያን ዳክ አንድ ቀንም በአካባቢዉ የማያባራዉ ደም መፋሰስ መፍትሄ ይኖረዋል የሚል ተስፋ አላቸዉ።

«አንድ ቀን መፍትሄዉ የተለየ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ። ዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ እና በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ፣ በምሥራቅ ኢየሩሳሌም፣ እንዲሁም በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማዉያን የተለየ ድምፅ እና አመለካከት ያላቸዉ ቦታዎችን በኃይል መያዝን እንዲሁም አመፅና ጭቆናን የሚቃወሙ አይሁዳዉያን እስራኤል ዉስጥ እንዳሉ ማወቃቸዉ በጣም አስፈላጊ ጉዳይ ነዉ።»

ከተገደሉት ሶስት እስራኤላዉያን ወጣቶች የአንደኛዉ እናት ብቀላዉን አጥብቀዉ ይቃወማሉ። ማያን ዳክ አባል የሆኑበት የሴቶች ለሰላም ማኅበርም ላለፉት 14 ዓመታት የእስራኤልን በዮርዳኖስ ወንዝ ምዕራባዊ ዳርጃ የሚካሄደዉን የኃይል ሰፈራ ሲቃወም ቆይቷል። እንደእሳቸዉ እምነትም ደቡባዊ እስራኤል የሚኖሩ አይሁዳዉያን በየዕለቱ በሚሰነዘረዉ ጥቃትና ስጋት ዋጋ እየከፈሉ ናቸዉ። በዚህ ምክንያትም መደበኛ ኑሮ እንደሌላዉ ወገን ለመኖር የታደሉ አይደሉም። እሳቸዉና ሌሎች የሰላም አቀንቃኞች ብቀላና ዘረኝነትን አጥብቀዉ ይቃወማሉ። ይህንንም አደባባይ ወጥተዉ እያሳዩ ነዉ።

ዑልሪክ ሽላይሸር/ ሸዋዬ ለገሠ

ተክሌ የኋላ

Audios and videos on the topic