አልጀሪያ ያልገዛም ባዮች ምድር | አፍሪቃ | DW | 03.06.2019
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አልጀሪያ ያልገዛም ባዮች ምድር

አልጄሪያዎች እንደ ግብፅ ወይም እንደየመን አረቦች፣ ምናልባት እንደ ኢትዮጵያዉያን አፍሪቃዉያን ይሁኑ እንጂ ግብፆች፣ የመኖች ወይም ኢትዮጵያዉያን አይደለም።ለአልጄሪያዎች ጥያቄያቸዉ ተገቢዉን መልስ የሚያገኘዉ ጨቋኙ ሥርዓት ከስሩ ተመንግሎ ሲወድቅ እንጂ «ቁንጮዉ»ን ከላይ ከርክሞ መቆም ከስር ያለዉ ፋፍቶ እንዲጠረቃ እድል መስጠት ነዉ።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 16:31

የአልጄሪያ ሕዝባዊ አብዮት ሒደትና ድል

በዚያ በራቀዉ ዘመን የድንጋይ ቢላ-ጩቤን የመጥረቢያ-ፋስን አጠራረብ ለዓለም ያስተዋወቁ ሥልጡኖች ምድር ነበረች።ሰዉ በስለት መሳሪያዉ እየታገዘ የያኔዎቹን አዉሬዎች አላምዶ ወደ ቤት እንስሳነት ከቀየረባቸዉ ጥቂት አካባቢዎችም አንዷ ናት።አልጄሪያ።ካርቴዢያዎች፣ቲፓሳዎች፣ሲኪክዳዎች፣ ባርበሮች፣ሮሞች፣ዑመያዶች፣ፋጢሚያዎች፣ቱርኮች፣ ፈረንሳዮች ደካሞችን እያስገበሩ ገዝተዉ፣ለጠንካሮች ገብረዉ ተገዝተዉባታል።ወይም ሸሽተዉባታል።በ2011 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ቱኒዚያ ላይ የተቀጣጠለዉ ሕዝባዊ አብዮት ግብፅ፣ሊቢያ፣የመን ሌላም ጋ ሲዛመት ለቅኝ ገዢዎች አልበገር በማለቱ የታወቀዉ አልጄሪያዊ «ናቅ» አድርጎ ያለፈዉ መስሎ ነበር።ዘንድሮ ግን የሰሜን አፍሪቃዊዉ ሕዝብ በራሱ ልዩ ስልት ገዢዎቹን ተራ በተራ እየመነገለ ነዉ።የአልጀሪያ ሕዝባዊ አብዮት ሒደቱና የእስካሁን ዉጤቱ ያፍታ ዝግጅታችን ትኩረት ነዉ።

አልጄሪያዎች ለፖለቲካዊ ነፃነት፣ ለፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ በተከታታይ ያደረጉት ያአደባባይ ሠልፍና ትግል የረጅም ጊዜ ገዢያቸዉን አብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃን ባለፈዉ ሚያዚያ 2 ለዳግም ዘመነ ሥልጣን ከመወዳደርም፣ ከያዙት ስልጣንም አስወገዷል።ቡተፈሊቃ ሥልጣናቸዉን በመልቀቃቸዉ ተቃዉሞ ሰልፈኛዉ መደሰት-መቦረቁ አልቀረም።

ግን አልጄሪያዎች እንደ ግብፅ ወይም እንደየመን አረቦች፣ ምናልባት እንደ ኢትዮጵያዉያን አፍሪቃዉያን ይሁኑ እንጂ ግብፆች፣ የመኖች ወይም ኢትዮጵያዉያን አይደለም።ለአልጄሪያዎች ጥያቄያቸዉ ተገቢዉን መልስ የሚያገኘዉ ጨቋኙ ሥርዓት ከስሩ ተመንግሎ ሲወድቅ እንጂ «ቁንጮዉ»ን ከላይ ከርክሞ መቆም ከስር ያለዉ ፋፍቶ እንዲጠረቃ እድል መስጠት ነዉ።

ወይም ግብፅ እንደሆነዉ ሕዝብ ሕይወት፣ አካል፣ ደም፣ ጊዜ፣ ክብሩን የገበረበትን የሕዝባዊ አብዮት ጅምር ዉጤትን ለጦር ጄኔራሎች ማስረከብ፣ የመን ላይ እንደሆነዉ በጦርነት፣ ኢትዮጵያ እንዳለዉ ግጭት፣ሥጋት አለመተማመን ማስፈን ነዉ።ባይሆን ኖሮ የ20 ዘመን ገዢዉ ስልጣን ከለቀቁ በኋላ በከባዱ የረመዳን ፆም ጭመር

አደባባይን ሙጥኝ የሚልበት «ሐራረ» ተጣቦት ሊሆን አይችልም።ሰልፈኛዉ ቢያንስ የቡተፈሊቃ ሥርዓት ሶስት ዋና ዋና ሹማምንት ይወገደ ባይ ነዉ።የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች 3ቱ «B» ዎች ይሏቸዋል።

                                    

«የአልጄሪያ ተማሪዎች 3 B ዎች ከስልጣን እንዲለቁ መጠይቅን ጨምሮ፣ያነሳነዉ ፖለቲካዊ ጥያቄ መልስ እስኪያገኝ ድረስ ግፊት ማድረጋችንን እንቀጥላለን።ምርጫዉ ለማድረግም ምርጫዉን የሚያስተባብር ብሔራዊ ኮሚቴ እንዲቋቋም እንጠይቃለን።እነዚያ 3B ዎች ግን ለናጄሪያ ዉድቀት ተጠያቂ በመሆናቸዉ ባስቸኳይ ሥልጣን መልቀቅ አለባቸዉ።»

3B ዎች።ቢ-አንድ፣-ቡተፈሊቃ ሥልጣን ከለቀቁ በኋላ ሐገሪቱን በጊዚያዊ ፕሬዝደንትነት የሚመሩት የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ፕሬዝደንት አብዱቃድር ቤንሳላሕ ናቸዉ።ቢ-ሁለት፣ ጠቅላይ ሚንስትር  ኑረዱን ቤዱዊ፣ ቢ-ሶስት፣ የሕገ መንግሥታዊዉ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጣይብ ቤላኢዝ ናቸዉ።ቢ የተባሉት ሁለተኛዉ ወይም የቤተሰብ ስማቸዉ በላቲኑ «B» ስለሚጀምር ነዉ።

በነገራችን ላይ የፕሬዝደንት  አብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃም ሁለተኛም ስም  የሚጀምረዉ ያዉ በ«B» ነዉ።እድሜም፣ጤናም፣ ሃያ ዓመት የተገዛ ህዝባቸዉም የጨከነባቸዉ ቁጥር 1 B ሥልጣን ከለቀቁ ትናት ሁለተኛ ወራቸዉ።

ቡተፈሊቃን የሚተካዉን ፕሬዝደንትን ለማስመረጥ የሐገሪቱ ሕገ-መንግስታዊ ምክር ቤት ለነገ ይዞት የነበረዉን ቀጠሮ ሰርዞታል።ምክር ቤቱ የምርጫዉ ሒደት ለመሰረዙ የሰጠዉ ምክንያት «ሐገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ» ምርጫ ማድረግ አይቻልም የሚል ነዉ።ሕገ-መንስታዊዉ ምክር ቤት አድበስብሶ ይለፈዉ እንጂ የምርጫዉ ጊዜ የተሠረዘዉ ምርጫዉ በገለልተኛ ልዩ ኮሚቴ እንዲደረግ ተቃዉሞ ሰልፈኛዉ በመጠየቁ ነዉ።

ምርጫዉን በበላይነት የሚመራዉ የሕገ-መንስታዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ወይም «B»ቁጥር 3ም ከዚሕ በፊት በገቡት ቃል መሰረት ስልጣን ለቅቀዋል።የምርጫዉ ጊዜ መራዘም ወይም መሠረዝና የBB ቁጥር 3 ስልጣን መልቀቅ፣ ተቃዉሞ ሠልፈኛዉ ከአጠቃላይ ድሉ መጨረሻ ላይ የመድረሱ ምልክት፣ የደስታ ብስራቱ አብነት በሆነ ነበር።ግን አልሆነም።ወይም ብስራቱን መርዶ ሸፈነዉ።እዉቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ዶክተር ከማል ኢዲኒ ፈቂር አረፉ።የ54 ዓመቱ የመብት ተሟጋች በተለይ በርቤር ቋንቋ የሚናገረዉ የሞዛባይት የተሰኘዉ አናሳ ማሕበረሰብ መብት እንዲከበር ለበርካታ ዓመታት ሲታገሉ ነበር።በ2015 ሕዝብን አጋጭተሐል በሚል ወንጀል ሁለት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዉ የተፈቱት በ2017 ነበር።

ጠበቆቻቸዉ

እንደሚሉት ዶክተር ፈቂር ሕዝባዊ  አመፁ ከተጋጋመ በኋላ በቅርቡ «በመንግስት ተቋም ላይ ጥቃት አድርሰኃል በሚል ጥርጣሬ ተይዘዉ በምርመራ ላይ ነበሩ።ከጥቂት ሳምንታት በፊት የረሐብ አድማ መተዉ እንደነበር ጠበቆቻቸዉ አስታዉቀዋል።የታሰሩበት ወሕኒ ቤት የመብት ተሟጋቹን ወደ ሆስፒታል ያዞራቸዉ በጣም ከደከሙ በኋላ ነበር።

የአልጄሪያ የፍትሕ ሚንስቴር የዶክተሩን አሟሟት ለማጣራት ቃል ገብቷል።ቃሉ የሕዝብ ቁጣና ጥርጣሬን ማብረድ ግን አልቻለም።«ከማል ኢዲኒ ፈቂር ከደጎቹ አንዱ ነበር።የአማዚግሕ ጀግኖች መሪ ነዉ።ፈቂር ነበር።ሌላ የለም።»ይላሉ የቀድሞዉ የጦር ኃይሎች ኮሎኔል ሞክራኔ ጉርዶች።የአልጄሪያ የባሕልና የዴሞክራሲ ለዉጥ ጥምረት (RCD በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) የተኘዉ የተቃዋሚ ፓርቲ ተጠሪ ሳዓዳት ፌታ በበኩላቸዉ የዶክተር ፈቂርን ሞት፣ ለነፃነት የተከፈለ መስዋዕትነት ይሉታል።

«እርግጥ ነዉ ዛሬ ዶክተር ከማል ኢዲኒን እንዘክራለን።ምግባራቸዉን እናስታዉሳለን።መስዋዕት ናቸዉ።የነፃነት መስዋዕት።ሰብአዊ መብት ምንም ሳይጓደል እንዲከበር የታገሉ ጀግና ናቸዉ።ይሁንና እሳቸዉንና ምግባራቸዉን መዘከር ብቻዉን በቂ አይደለም።ፍትሕ ገቢር መሆን አለበት።»

ከ1ሺ 2 መቶ ባቂያ ጀምሮ ገሚስ ዓለም የገዙት የቱርክ ሱልጣኖች፣ ከ19ኛዉ መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ ጉልበታቸዉ  እየተዳከመ፣ የአዉሮጶች በተለይም የብሪታንያና የፈረንሳይ ኃይል ባንፃሩ እየፈረጠመ ሲመጣ አልጀሪያም «አሮጌዎቹን» ገዢዎችዋን አሰናብታ «አዳዲሶቹን» መቀበል ግድ ነበረባት።የፈረንሳይ ቅኝ ገዢ ጦር ጉልበቱ የዛለዉን የቱርክን ኃይል አሸንፎ ሰሜን አፍሪቃን በ1830 መቆጣጠሩ ብዙም አልከበደዉም።ፈረንሳዮች ከሐገሬዉ ሕዝብ የገጠማቸዉን ተቃዉሞ በተለይም አሚር አብዱቃድር ኢብን ሙሕዲን የሚመሩትን ኃይል አሸንፎ የዛሬዋን አልጄሪያን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ግን ለዓመታት መዋጋት፣የብዙ ወታደሮቻቸዉን ሕይወት መገበር፣ የዚያኑ ያሕል ብዙ ሕዝብ ፈጅተዉ ለትዉልድ የሚቆይ ቂም በቀል ማትረፍ ግዳቸዉ ነበር።

በ1830 በተጀመረዉ ጦርነት ከ825ሺሕ በላይ አልጄሪያዊ ሲያልቅ፣ ወደ መቶ ሺሕ የሚጠጋ ፈረንሳዊ ሞቷል።ጦርነቱ በ1875

በፈረንሳዮች የበላይነት ቢደመደምም የአልጄሪያ ሕዝብ በየአካባቢዉ የሚያደርገዉ የነፃነት ትግል ግን ተዳፈነ እንጂ አልጠፋም።ከሰባ ዓመታት በላይ ብልጭ ርግም ሲል የቆየዉ የአልጄሪያዎች የነፃነት ትግል በ1954 እንዳዲስ አገርሽቶ በርካታ ሕዝብ ፈጅቷል።

የመጨረሻ-መጨረሻዉ ድል ግን በርግጥ የነፃነት ተፋላሚዎቹ ነበር።የአልጄሪያዉያን።1962 ሰሜን አፍሪቃዊቱ ሰፊ አረባዊት ሐገር ነፃ ወጣች።በ1830ዎቹ እነ አሚር አብዱቃድር ኢብን ሙሕዲን ከነበሩ ከ1954 እስከ ነፃነት በነበረዉ ትግል ደግሞ እነ ሩባሕ ቢታች፣ እነ ሙስጠፋ ቤን ቡሌይድ፣ እነ ዲዶዉቻ ሙራድ ግንባር ቀደሞቹ ናቸዉ።

ለነፃነት በተደረገዉ ዉጊያ በወጣት ታጋይነቻቸዉ ሥም ዝና ያተረፉት አብዱል አዚዝ ቡተፈሊቃና ጓዶቻቸዉ ሥልጣን ከያዙ በኋላ በሕዝባቸዉ ላይ የሚዉሉትን ግፍ ሲታገሉ ከወደቁት ደግሞ ዶክተር ከማል ኢዲኒ ፈቂር በርግጥ አንዱ ናቸዉ።የአልጄሪያ ሶሻሊስት ኃይላት ግንባር (FFS በፈረንሳይኛ ምሕፃሩ) የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አልይ አስከሪ ባለፈዉ ቅዳሜ  እንዳሉት ደግሞ ዶከተር ፈቂር ሐገር ለሐገራቸዉ መስዋዕት የሆኑ ታጋይ ታጋይ ናቸዉ።

«የክብር ሰዉ፣የኃይማኖት ሰዉ፣ ሐገሩን የሚወድ ሰዉ።ሲ ሁሴይኔ አይት አሕመድ እንዳሉት ዛሬ የሐገር ፍቅር አልጄሪያ ዉስጥ ሰርፅዋል።ከማል ኢዲኒ ፈቂር እራሱ እንዳለዉ ደግሞ መስዋዕትነት መክፈል ሐገርን ማፍቀር ነዉ።ሐገርን ማፍቀር ዴሞክራሲ ነዉ።»

የቡተፈሊቃን አገዛዝ በመቃወም ዛሬ አብዛኛ የአልጄሪያ ከተሞችን የሚያጥለቀልቀዉን ሕዝባዊ አመፅ የጀመሩት ግን ዶክተር ፈቂርም፣የተቃዋሚ ፓርቲ መሪዎቹም አይደሉም።ቱኒዚያ ተጀምሮ፣ግብፅ ላይ ተቀልብሶ፣ ሊቢያን፣ሶሪያን የመንን በደም አበላ የሚያጨቀየዉ፣የአረብ ነገስታትን ያርበተበተዉ የአረብ ሕዝባዊ አብዮት ያኔ ገና አልታሰበም ነበር።2008።

ፕሬዝደንት ቡተፈሊቃ ከ1999 ጀምሮ ለአስር ዓመት የያዙትን ስልጣን አልበቃ ሲላቸዉ ከሁለት ዘመነ-ሥልጣን በላይ መግዛት የሚግደዉ የሐገሪቱን ሕገ-መንግስት አስቀየሩ።ሕዳር 2008።ወይዘሮ አሚራ ቦራዊ ሐገ-መንግስቱ እንደ «ልጃገረድ የተደፈረበት» ማለቱን ይመርጣሉ።

በሙያቸዉ የማሕፀንና ፅንስ ሐኪም ናቸዉ።የሁለት ልጆች እናት።የሕገ-መንግስቱን፣በሳቸዉ ቃል፣ መደፈር በመቃወም ጥቂት ባልደሮቦቻቸዉን አስከትለዉ አደባባይ ወጡ።ያየ እንጂ የተከተላቸዉ አልነበረም።ሲትዮዋ ተስፋ አልቆረጡም።ቡተፈሊቃ በ2014 ለአራተኛ ዘመነ-ስልጣን ሲፎካከሩ ከ2008ቱ ትንሽ በርከት ያሉ ተከታዮቻቸዉን ይዘዉ ባደባባይ ሰልፍ ተቃወሙ።ከጥቂቶች በስተቀር ዓላማቸዉን በግልፅ የደገፉ አልነበሩም።

የካቲት 22 2019 ጥቂቶቹ እነ አሚራ እልፍ ሆኑ።የአልጀርስ አደባባይን አጥለቀለቁት።ቡተፈሊቃ «ለአምስተኛ ጊዜ ተመረጡ ቢባል ኖሮ» አሉ አሚራ ባለፈዉ ወር ፣ ከልጄሪያ ለመሰደድ ወስኜ ነበር።» የአደባባይ ሰልፉ ዛሬም ቀጥሏል።«አዲሲቱ አልጄሪያ እስክትመሠረት አይቋረጥም» ይላሉ አሚራ።

በተከታታይ የተደረገዉ ህዝባዊ ተቃዉሞ አሚራ እንደተመኙት ወይም ሕዝቡ እንደሚጠይቀዉ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣የፍትሕ ልዕልና እና ከሙስና የፀዳ ሥርዓት እስኪመሰርት ጊዜ መዉሰዱ አያጠራጥርም። ሕዝባዊ

ተቃዉሞዉ ሌሎች ሐገራት እንዳታየዉ የከፋ ደም መፋሳስ ሳይስከተል  ከደረሰበት ደረጃ ለመድረሱ ግን ከአደባባይ ሰልፈኛዉ ጥንቃቄ እኩል፣ የሚወገዙት ባለስልጣናት ትዕግስት፣ በተለይም የፀጥታ አስከባሪ አዛዦቹ ብልሐት የሚደነቅ ነዉ።

ከሁሉም በላይ የቡተፈሊቃ ታማኝ የሚባሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹምና ምክትል መከላከያ ሚንስትር ጄኔራል አሕመድ ጋይድ ሳላሕ፣ ጄኔራል አል ሲሲን፣ወይም ጄኔራል ቡርሐንን ከመሆን ይልቅ የቀድሞ አለቃቸዉ የህዝቡን ጥያቄ አክብረዉ ስልጣን እንዲለቁ በማድረጋቸዉ ብዙዎች ያደንቁ፤ ያወድሱ፤ያመሰግኗቸዋልም።የፖለቲካ ተንታኝ መሐመድ ሲፋዊ ግን ከብዙዎቹ አይስማሙም።

«ጄኔራሉ፣ ቡተፈሊቃ ስልጣን እንዲለቁ ያደረጉት፣ የቡተፈሊቃ ሥርዓት እንዲቀጥል ስለፈለጉ ነዉ»

የሰባ ዘጠኝ አመቱ ጄኔራል ግን የጠርጣሪዎችን ምክንያት በተደጋጋሚ ዉድቅ ነዉ ያደረጉት።በቀደምም ደገሙት።«ሐገራችንን ከማገልገል በስተቀር የተለየ የፖለቲካ ጉጉት እንደሌለን መላዉ ዓለም ማወቅ አለበት።እደግመዋለሁ።የምንፈልገዉ ሐገራችንን ማገልገል ነዉ።ዓላማችን በሕገ-መንግሥቱ መርሕና ራዕንይ መሠረት  ሐገርን ማገልገል ነዉ።»

ሽማግሌዉ ጄኔራል እስካሁን ቃላቸዉን አላጠፉም።የአልጄሪያ ሕዝባዊ አብዮትም ከዚሕ ቀደም ከቱኒዚያ እስከ ኢትዮጵያ ከታዩት በተሻለ ሥልት፣ ባነስተኛ መስዋዕትነት ግን ቀስበቀስ ከወደ መጨረሻዉ መጀመሪያ የደርሰ መስሏል።

ነጋሽ መሐመድ 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

 

 

Audios and videos on the topic