አልጀሪያ እና መፃዒው ምክር ቤታዊ ምርጫ | አፍሪቃ | DW | 15.04.2017
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages
ማስታወቂያ

አፍሪቃ

አልጀሪያ እና መፃዒው ምክር ቤታዊ ምርጫ

 በአልጀሪያ ከሶስት ሳምንታት በኋላ እጎአ የፊታችን ግንቦት አራት እና አምስት የሚደረገው ምክር ቤታዊ ምርጫ ዘመቻ በዚህ ሳምንት ተጠናቀቀ። በብሔራዊው ምክር ቤት ላሉት 462 መንበሮች 12,000 እጩዎች በተፎካካሪነት ይወዳደራሉ። የምርጫው ፉክክር ቀልብ የሚስብ ሊሆን እንደሚችል ቢገመትም፣ እስካሁን ያን ያህል የሕዝቡን ትኩረት አላገኘም።

አውዲዮውን ያዳምጡ። 08:18

አልጀሪያ

ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምክር ቤታዊ ምርጫ ላይ እንደሚታወሰው፣ የመምረጥ መብት ካለው ሕዝብ መካከል ከግማሽ ያነሰ ነበር የወጣው። በዘንድሮው ድምፅን የሚሰጠውም ከዚያን ጊዜው ያነሰ እንደሚሆን ነው ለውዝግቦች መፍትሔ ሀሳብ የሚያቀርበው ዓለም አቀፍ ድርጅት፣ «ክራይስስ ግሩፕ» ባልደረባ ኢሳንድር አርማኒ የገመቱት።
« ለአመዛኙ የአልጀሪያ ሕዝብ ይህ ምክር ቤታዊ ምርጫ አንድም ትርጉም የለውም። የሀገሪቱ ምክር ቤት በፕሬዚደንት ቡቴፍሊካ የስልጣን ዓመታት ምን ያህል ፖለቲካዊ ስልጣኑን እያጣ መምጣቱ በጣም የሚያስገርም ነው። ምክር ቤቱ ጥምረት የፈጠሩት ሁለቱ ገዢ ፓርቲዎች፣ ማለትም፣ ብሔራዊ ነፃነት ግንባር እና ብሔራዊ ዴሞክራቲክ ራሊ ፓርቲዎች በምክር ቤቱ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አሳርፈዋል። ሁለቱ ፓርቲዎች ለደጋፊዎቻቸው ገንዘብ ያከፋፍላሉ፣ የሚጠበቅባቸውን ፖለቲካዊ ተግባርም አያከናውኑም። ያም ቢሆን ግን ትንንሾቹ ፓርቲዎች ተፅዕኗቸው እጅግ ንዑስ በመሆኑ ለትልቆቹ ፓርቲዎች ላይ አንዳችም ስጋት አልደቀኑም። »

በቀድሞዋ ቅኝ ገዢ ፈረንሳይ አንፃር በተካሄደው ትግል ዋነና ተዋናይ የሆኑት የአልጀሪያ ፕሬዚደንት አብደልአዚዝ ቡቴፍሊካ የርዕሰ ብሔርነቱን ስልጣን ከያዙ በቅርቡ 20 ዓመት ይሆናቸዋል።  
ብሔራዊ የነፃነት ግንባር ፓርቲያቸው ፣«ኤፍ ኤል ኤን» እና ተጣማሪው «ኤር ኤን ዲ» ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ  ራሊ፣ በምክር ቤቱ ውስጥ አብላጫውን ድምፅ ይዘዋል። በአልጀሪያ መንግሥት እና በአንፃሩ በተንቀሳቀሱ ፅንፈኛ ሙስሊሞች መካካል የተካሄደው እና 150,000 ሰው የሞተበት የርስ በርስ ጦርነት በጎርጎሪዮሳዊው 1990ዎቹ ዓመታት ካበቃ ወዲህ ቡቴፍሊካ የሚመሩት የመንግሥት በአልጀሪያ እውን ለሆነው የመረጋጋት ሁኔታ አስተማማኝ ጠባቂ ሆኖ ታይቶ ነበር። አሁን ግን የራሱን ጥቅም የሚያስጠብቅ የግለሰቦች ስብስብ ብቻ መሆኑ ነው የሚነገረው። የፓርቲዎች ፣ የጦር ኃይሉ፣ የስለላ ድርጅቶች እና ቅርበት ያላቸው ባለተቋማት የተጠቃለሉበት ይኸው የስልጣን መረብ በሙስና የተዘፈቀ በመሆኑ ለሀገሪቱ ዜጎች አንዳችም ደንታ እንደሌለው በዩኒቨርሲቲ የፋርማሲ ትምህርት በመከታተል ላይ የሚገኘው ተማሪ አኒስ ሳይዱን ይተቻል።

« የሚገቡትን ቃል ተግባራዊ በማያደርጉበት አሰራር በጣም ተሰላችተናል። ባለስልጣናት በሀገሪቱ የሚታየውን እንቅስቃሴ ለማስቆም ሲሉ በሚጠቀሙበት ስልት መሰላቸት ይታያል። ስለዚህ መንግሥት ቃሉን እንደሚጠብቅ ዋስትና እንዲሰጠን እንፈልጋለን፣ ምክንያቱም በጎርጎሪዮሳውያኑ በ2011 ዓመተ ምህረትም ቅር አሰኝተውናል። »  

 
በዐረባውያቱ ሀገራት የሕዝብ ዓመፅ ተጠናክሮ በተካሄደበት በ 2011 ዓም አልጀሪያም ውስጥ የስራ ማቆም አድማዎች፣ በተለይም፣ በወጣቱ ትውልድ መደዳ በታየው ግዙፉ ስራ አጥነት አንፃር ተቃውሞዎች መካሄዳቸው አይዘነጋም። በነዳጅ ዘይት እና በጋዝ የተፈጥሮ ሀብት የታደለችው የአልጀሪያ ኤኮኖሚያዊ ሁኔታ በዚያን ጊዜ፣ እንደሚታወቀው፣ ጥሩ ስለነበረ የሀገሪቱ መንግሥት ለዜጎቹ የሚሰጠውን የማህበራዊ ኑሮ አገልግሎት በማሻሻል እና ድጎማ በመስጠት ሀገሪቱን አረጋግተዋል። ይሁን እንጂ፣ በአሁኑ ጊዜ በአልጀሪያ ሁኔታዎች ተቀያይረው መንግሥት የገንዘብ እጥረት ገጥሞታል። የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚደንት ሀፌስ ጋኔም እንደሚሉት፣ ሀገሪቱ ከተፈጥሮ ሀብቷ የሚፈለገውን ጥቅም በማግኘት ላይ አይደለችም፣ ይህም አሳሳቢ ችግር ላይ ጥሏታል።

«  አልጀሪያ የኤኮኖሚ ዘርፏን ለማሳደግ እየተከተለችው ያለውን ዘዴ  መቀየር አለባት። ሌላ ብዙ አማራጭ ያለን አይመስለኝም። የነዳጅ ዘይቱን እና ጋዝን በንግድ ወደ ውጭ በመላኩ አሰራር ብቻ ልንቀጥል አንችልም። አልጀሪያ በንግድ ወደ ውጭ የምትልካቸውን ምርቶችዋን ማስፋት ይኖርባታል። ይህ እንደ አማራጭ የቀረበ ሀሳብ አይደለም፣ በኔ አስተያየት ለሀገሪቱ አስፈላጊ ዘዴ ነው።»      

የነዳጅ ዘይት እና የጋዝ ዋጋ በዓለም ገበያ ከወደቀ ወዲህ በአልጀሪያ መንግሥት ካዝና ውስጥ ለድጎማ የሚሆን ገንዘብ የለም። በዚህ ፈንታ መንግሥት ጭራሹን ተጨማሪ እሴት ታክስን  በሁለት ከመቶ ከፍ አድርጓል።  አትክልት፣ ፍርራፍሬ፣ አሳ፣ ትምባሆ እና ነዳጅ-ቤንዚን ዋጋ የናረ ሲሆን፣ በዚሁ የመንግሥት ውሳኔ አብዝቶ የተጎዳው ለዕለታዊ ኅልውናው በመታገል ላይ የሚገኘው ድሀው ዜጋ ነው።

የዋጋ ግሽበቱ ከፍ ብሏል። ሙስና ተስፋፍቷል።  ጎርጎሪዮሳዊው 2017 ዓም ከገባ ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በአልጀሪያ በተዳጋጋሚ ተቃውሞዎች የተካሄዱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደም አፋሳሽ እንደነበሩ የመገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።  

ዓለም አቀፉ የመብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል በ2016 ባወጣው ዘገባ መሰረት፣  በሀገሪቱ የዘፈቀደ እስራት፣ የፖሊስ የኃይል ርምጃ እና ሳንሱር ተስፋፍቷል። የሀገሪቱ ፀጥታ ኃይላት በተቃዋሚዎች አንፃር የሚወስዱት ጠንካራ ርምጃ መቆም እንዳለበት ነው አኒስ የመሳሰሉ ወጣቶች የሚናገሩት።
« የአልጀሪያ መንግሥት ባለስልጣናት ይኸውም ወጣቱ ወደ ዓመፅ እያመራ መሆኑን ሊረዱት የሚገባ   ይመስለኛል። ባለስልጣናቱ ለይስሙላ ብቻ በተግባር ሊተረጉሙት የማይችሉትን  ቃል መግባት ማቆም አለባቸው። ለወጣቱ በተጨባጭ የሚታይ ነገር ማቅረብ ይኖርባቸዋል። ወጣቱ ስር ሰደድ መፍትሔዎች እንዲገኙ ይፈልጋል። ወጣቱ በወቅቱ የሚታየውን ቀውስ በማስወገድ ተጨባጭ ተሀድሶ ማስገኘት የሚያስችሉ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይገባል ባይ ነው። »
ይሁን እንጂ፣ ይህ የሚሳካ አይመስልም።  የፖለቲካ ታዛቢዎች እንደሚሉት፣ መንግሥት ሁኔታዎችን ካላሻሻለ፣ በሀገሩ ብሩህ የወደፊት እድል እንደሌለው የሚሰማው የአልጀሪያ ወጣት  ትውልድ ወደ አውሮጳ የመሰደድ ወይም ፅንፈኛው እስላማዊ መንግሥት እጅ ውስጥ የመውደቅ አሳሳቢ ስጋት ተደቅኖበታል። 

አርያም ተክሌ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

Audios and videos on the topic