አልበሽርና የእስራት ትዕዛዙ | አፍሪቃ | DW | 17.07.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አፍሪቃ

አልበሽርና የእስራት ትዕዛዙ

ናይጀሪያ የሱዳኑን ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽርን ለዓለም ዓቀፉ የጦር ወንጀል ተመልካች ፍርድ ቤት ይዛ ባለመስጠቷ እየተወቀሰች ነዉ። ፕሬዝደንት አልበሽር በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያ ናይጀሪያ ላይ በተካሄደዉ የአፍሪቃ ኅብረት የHIV/AIDS ጉባኤ ላይ መገኘታቸዉን የአገሪቱ የመብት ተሟጋቾች ተቃዉመዋል።

የሱዳን መሪ ፕሬዝደንት ኦማር አል በሺር ከአገራቸዉ በወጡ ቁጥር በተገኙበት ይታሠሩ የሚለዉን የዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት የእስር ማዘዣ ሲከተላቸዉ ዓመታት ተቆጥረዋል። እስካሁን ግን አሳልፎ የሰጣቸዉ አገር የለም። በያዝነዉ ሳምንት መጀመሪያም ናይጀሪያ ዉስጥ በአፍሪቃ ኅብረት የHIV/AIDS ጉባኤ ላይ በመገኘታቸዉ አል-በሺርን ናይጀሪያ ለICC እንድትሰጥ ተጠይቋል። ፕሬዝደንት አል-በሺር ግን አሁንም ዞር ብሎ ያያቸዉ ሳይኖር ሰኞ ዕለት ማምሻዉን ወደአገራቸዉ መመለሳቸዉን አቡጃ የሚገኘዉ የሱዳን ኤምባሲ ቃል አቀባይ ገልጸዋል። የኤምባሲዉ ቃል አቀባይ አልበሽር ተጣድፈዉ የተመለሱትም ሌላ አስቸኳይ ሥራ ስላላቸዉ እንጅ ለእስር ሰግተዉ እንዳልሆነም አመልክተዋል። የናይጀሪያ ጋዜጦች እንደዘገቡት ግን አልበሽር በጉባኤዉ ላይ የሚያቀርቡት ዘገባ እንደነበር ግን እንዳላደረጉት ጠቅሰዉ፤ ይህም የሚጠየቁበት ከፍተኛ የወንጀል ጉዳይ እየተጠቀሰ ነገሮች እንዳልተፈጸሙ አድርጎ አደባብሶ የሚታለፍበት ጊዜ ማክተሙን ያሳያል ብለዋል።

  የናይጀሪያ የዓለም ዓቀፍ የጦር ወንጀል ፍርድ ቤት ጥምረት NCICC የመብት ተሟጋቾች የናይጀሪያ መንግስት ICC በዘር ማጥፋትና በጦር ወንጀል ክስ የመሠረተባቸዉን አልበሽርን አማሠሩን በመቃወምም ለአገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ አቅርበዋል። ወደሌሎችም የአፍሪቃ አገሮች ሲጓዙ ተመሳሳይ ሁኔታ መፈጠሩን በመጠቆም ከNCICC ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸዉ የሕግ ባለሙያ ቺኖ ኦቢያጉ፤ መንግስትን መክሰሱ ለዉጥ ያመጣ ይሆን ለሚለዉ እንዲህ ይላሉ፤ 

«በርካታ የአፍሪቃ ሃገሮችን አይደለም የጎበኙት እሳቸዉ የጎበኟቸዉ የICC ፈራሚዎች አይደሉም፤ አብዛኞቹ የአፍሪቃ ሃገሮች የዚህን ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ ስምምነት አለመፈረማቸዉ ግልጽ ነዉ። የፈረሙት 34 ቢሆኑ ነዉ። ፈራሚ ሆነዉ እሳቸዉ የሄዱባቸዉ ሃገሮች ደግሞ የዲፕሎማሲ መዘዝ ተከትሏቸዋል። እናም ናይጀሪያን መጎብኘታቸዉ የጆናታን አስተዳደር የዲፕሎማሲ ስህተት ይመስለኛል።»

አቡጃ የሚገኘዉ ዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲ ባወጣዉ መግለጫ ናይጀሪያ በወንጀል የሚፈለጉት መሪ በማስተናገዷ ማዘኑን ገልጿል። እራስዋ ዩናይትድ ስቴትስ ግን የICC አባልነትን አልተቀበለችም። የቀድሞ የናይጀሪያ ቅኝ ብሪታኒያም እንዲሁ በድርጊቱ ቅር መሰኘቷን አሳዉቃለች።   

የናይጀሪያ መንግስት ቃል አቀባይ ሩበን አባቲ በበኩላቸዉ አልበሽር የመጡት በአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤ ለመሳተፍ እንጂ በናይጀሪያ መንግስት ግብዣ እንዳልሆነ ነዉ የገለጹት። ናይጀሪያ በጉባኤዉ ላይ እንዲሳተፉ የፈቀደችዉም ከአፍሪቃ ኅብረት በተሰጣት ትዕዛዝ መሠረት መሆኑም አመልክተዋል። አባቲ ኅብረቱ አፍሪቃዉያን ላይ ብቻ ያተኩራል ሲል ከወቀሰዉ ICC ጋ 53ቱም አባላቱ እንዳይተባበሩም አስቀድሞ ማስጠንቀቁን ጨምረዉ ጠቅሰዋል። ዘገባዎች እንደሚሉት አንድ ቀን ብቻ ከወሰደዉ የአፍሪቃ ኅብረት የHIV/AIDS ጉባኤ ተሳታፊዎች መካከልም የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ብቻ ናቸዉ እስከማክሰኞ አቢጃን የቆዩት፤ አልበሽርን ጨምሮ ሌሎቹ በዕለቱ ወደየአገራቸዉ ተመልሰዋል። ICCም ቢሆን የናይጀሪያ መንግስት የሱዳኑን ፕሬዝደንት እንዲያስር የጠየቀዉ ዘግይቶ ነዉ። የፍርድ ቤቱ  ምስረታ ስምምነት ፈራሚ የሆነችዉ ናይጀሪያ ባለመተባበሯም ለተመድ የጸጥታዉ ምክር ቤት ጉዳዩን እንደሚያቀርብ ICC ዝቷል። ICC በጎርጎሪዮሳዊዉ 2009 እና 2010 ነዉ አልበሽር በተገኙበት እንዲታሰሩ ትዕዛዝ ያስተላለፈዉ። እስካሁን ግን ይህን ተግባራዊ ያደረገ የስምምነቱ ፈራሚ አገር የለም። ማላዊ ብቻ ናት የአፍሪቃ ኅብረት ጉባኤን የማስተናገድ ተራ ደርሷት በነበረበት ወቅት በሽር ከመጡ ለICC ተላልፈዉ ይሰጣሉ ስትል በይፋ ያሳወቀችዉ። በዚህ ምክንያትም በወቅቱ ጉባኤዉ አዲስ አበባ ላይ ሊካሄድ ግድ ሆኗል። ዑጋንዳና ደቡብ አፍሪቃም እንዲሁ አልበሽርን ለማስተናገድ ፈቃደኞች አልሆኑም።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

Audios and videos on the topic