አልቃይዳ የምዕራቡ ዓለም ስጋት | ዓለም | DW | 12.08.2013
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

አልቃይዳ የምዕራቡ ዓለም ስጋት

አሁን ሶስተኛው ትውልድ ላይ መድረሱ እየተነገረ ነው፤ አልቃይዳ። የመጀመሪያው ትውልድ በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከመስከረሙ የ2001 ዓም ጥቃት በፊት የነበረውን እንቅስቃሴ ይጠቀልላል። ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ የአልቃይዳው ዋና ሰው ቢን ላደን እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ የነበሩትን ሁነቶች ያካትታልል። ሶስተኛው ትውልድ የቢን ላደን መገደልና የአረብ

ሃገራትንቅናቄን ተከትሎ የመጣ ነው ይላሉ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች። የሰሞኑንም የአሜሪካና ሸሪኮቿ በአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ሊደርስብን ይችላል ስጋት ከሶስተኛው ትውልድ የአልቃይዳ እንቅስቃሴ ጋር ያዛምዱታል። የሶስተኛውን ትውልድ የአልቃይዳ እንቅስቃሴና የምዕራቡ ዓለም ስጋት የማኅደረ ዜና ማጠንጠኛችን ነው።

ዩ ኤስ አሜሪካ ከእስልምና አክራሪ አሸባሪዎች ጥቃት ሊቃጣብኝ ይችላል ስትል የሽብር ጥቃት የአደጋ ጊዜ ማስጠንቀቂያ ካወጀች አንድ ሣምንት ተቆጥሯል። የአደጋ ማስጠንቀቂያው ገና ለቀጣዮቹ ሶስት ሣምንታትም እንደሚዘልቅ ተጠቁሞዋል። በማስጠንቀቂያውም ምክንያት በወቅቱ ዩናይትድ ስቴትስ እስራኤል ውስጥ የሚገኘውን ጨምሮ ቢያንስ በ25 የእስልምና እምነት ተከታይ ሃገራት ውስጥ የሚገኙ ኤምባሲዎቿን ለመዝጋትም ተገዳ ነበር። የአልቃይዳ የሽብር ጥቃት ዛቻን ተከትሎ የበርካታ ኤምባሲዎችን መዘጋት በማስመልከት የአሜሪካው ማዕከላዊ የስለላ ተቋም CIA የቀድሞ አባልና የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ብሩስ ሪደል እንዲህ ይላሉ፥

«ይህ የሽብር ጥቃት የአደጋ ማስጠንቀቂያ ከዓስርት ዓመት በፊት ከታዩትም በላይ ጠንከር ያለው ነው። አሜሪካንን ጨምሮ አውሮጳውያን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ኤምባሲዎቻቸውንና የቆንስላ ጽ/ቤታቸውን እንዲዘጉ ያስገደደ ዛቻ ሲሆን፤ የአደጋ ማስጠንቀቂያው ነሐሴ ወርን በሙሉ የሚዘልቅ ነው። ይህ የሚያመለክተው የተደቀነው አደጋ የምር እና እጅግ በጣም በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይ እንደሆነ ነው።»

በየመን የብሪታንያ ኤምባሲ ጥበቃ

በየመን የብሪታንያ ኤምባሲ ጥበቃየአሜሪካ ዋነኛ ሸሪክ መንግሥታት የሆኑት ብሪያታንያ፣ ፈረንሳይ እና ጀርመንም የአሜሪካንን ፈለግ በመከተል በተለይ የመን የሚገኘው ኤምባሲያቸውን በመዝጋት ዲፕሎማቶቻቸውን ከሀገሪቱ እስከማስወጣት ደርሰው ነበር። ያንን ተከትሎም ባሳለፍነው አርብ ብቻ የዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በእዛው የመን ውስጥ ባደረጉት ድብደባ ቢያንስ 12 የአልቃይዳ አባላት መገደላቸው ተዘግቧል።


ምዕራባውያን ሃገራትን እንዲያ ስጋት ውስጥ ጥሎ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ብሎም ወደ ድርጊት እንዲሸጋገሩ ያስገደዳቸው በአልቃይዳ የሽብር ጥቃት አውታር ውስጥ ዋነኛ የሚባሉ ሁለት ሰዎች የተለዋወጡት መልዕክት እንደሆነ ተጠቅሷል። የአልቃይዳ የአረብ ባሕረሰላጤ አካባቢ መሪ ናስር ኧል ውሐዪሺ ከሌላኛው የአልቃይዳ መሪ ግብፃዊው አይማን ኧል ዛዋሂሪ ጋር ያደረገው የመልዕክት ግንኙነት በአሜሪካ የደኅንነት አባላት መጠለፍ የስጋቱ ማስጠንቀቂያ ደወል እንዲያስተጋባ ሰበብ ሆኗል ተብሏል። የዩኤስ አሜሪካ ኤታማዦር ሹም ማርቲን ዴምፕሴይ ABC News ለተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ አደጋው ለአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም በሆኑ ነገሮች ላይ ያነጣጠረ ነው ብለዋል።

የአልቃይዳ የአረብ ባሕረሰላጤ አካባቢ መሪ ናስር ኧል ውሐዪሺ

የአልቃይዳ የአረብ ባሕረሰላጤ አካባቢ መሪ ናስር ኧል ውሐዪሺ«የተደቀነው አደጋ ከወደ አልቃይዳ በኩል ነው። አዎ፤ ከአልቃይዳ አንዱ ክፍል የመነጨ ነው። ዓላማውም ግልፅ ነው፤ የአሜሪካን ብቻ ሳይሆን የምዕራቡ ዓለም የሆነውን ነገር ማጥቃት ነው። በደንብ ግልፅ የሆነ ነገር ስለሆነ በቀላሉ የምንመለከተው ነገር አይደለም። መቼም እናንተም እንድናደረግ የምትጠብቁት ይህንኑ ነው። አዎን፤ ቀላል የማይባል አደጋ ተደቅኗል፤ እናም እኛ ለእዛ ምላሽ እየሰጠን ነው።»


አሜሪካን በእርግጥም የዛሬ አስራ ሁለት ዓመታት ግድም በገዛ ምድሯ ላይ በአሸባሪዎች ከደረሰባት ጥቃትና ዕልቂት አንፃር በአልቃይዳ መሪዎች መካከል የሚደረግን የመረጃ ግንኙነት በቀላሉ ልታልፈው ትችላለች ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው። የዛሬ አስራ ሁለት ዓመታት ግድም ልክ መስከረም አንድ ቀን አሸባሪዎች አስገድደው ከጠለፉዋቸው አውሮፕላኖች መካከል ሁለቱን በቀጥታ ከኒውዮርክ መንታ የንግድ ሕንፃዎች ጋር በማላተም እጅግ አሰቃቂ የሽብር ጥቃት መፈፀማቸው ይታወሳል። በወቅቱ የመንገደኞች አውሮፕላኖችን በጠለፉ 19 የአልቃይዳ አባላት በተፈፀሙት የተቀነባበሩ የሽብር ጥቃቶች እስከ ስር መሰረቱ ከተደረመሰው ሕንፃ ፍርስራሽ ስር ከ3000 በላይ ንፁኃን ሰዎች ለዘለዓለሙ ተቀብረው ቀርተዋል። እንደ ብሩስ ሪደል ያሉ ተንታኞች የሰሞኑን የሽብር ጥቃት የማስጠንቀቂያ ደወል የአልቃይዳ ሶስተኛው ትውልድ ሲሉ ይጠሩታል።

nበአሸባሪዎች የተመቱት የኒውዮርክ መንታ ሕንፃዎች

በአሸባሪዎች የተመቱት የኒውዮርክ መንታ ሕንፃዎች«አሁን አሁን የምንመለከተው የአልቃይዳ ሶስተኛው ትውልድ ብዬ የምጠራውን ነው። የመጀመሪያው ትውልድ ከመስከረሙ ከ911 የሽብር ጥቃት በፊት የነበረው ነው። ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ ከአሜሪካው የመስከረም የሽብር ጥቃት አንስቶ የአልቃይዳው መሪ ኦሳማ ቢን ላደን እስከተገደለበት ጊዜ ድረስ የነበረውን ነው። ሶስተኛው ትውልድ ደግሞ የቢን ላድን ሞት እና የአረብ ሃገራት ንቅናቄ በጣምራ ያስከተሉት ውጤት ነው። የአረብ ሃገራት ንቅናቄ በአብዛኛው የአረቡ ሃገራት ከማግሬብ አንስቶ እስከ ማሊ፣ ከሲናይ እስከ ሶሪያ ብሎም በየመንና ኢራቅ ትርምስን አስከትሏል። እናም አሁን ምናልባትም ያለንበት 2013 ዓም የአልቃይዳ ህዋስና ከአልቃይዳ ጋር ንክኪነት ያላቸው ቡድናት በአረቡ ሃገራት ከእዚህ በፊት ከነበረው በተለይ የተስፋፉበት ነው ለማለት ይቻላል።»

ኦሳማ ቢን ላደን ከመገደሉ በፊት የነበረበት ቅፅር በአቦታባድ ፓኪስታን

ኦሳማ ቢን ላደን ከመገደሉ በፊት የነበረበት ቅፅር በአቦታባድ ፓኪስታን

ከኦሳማ ቢን ላደን መገደል ወዲህ ከዋናው የአልቃይዳ ሕዋስ ባሻገር በይፋ በአልቃይዳ ስር ሆነው ግን በተናጠል የሚንቀሳቀሱ ቡድናት እዚህም እዚያም በየቦታው አቆጥቁጠዋል። እንዲህ አይነት ቡድናት በዋናነት በኢራቅ፣ በሰሜን አፍሪቃ እና በአረብ ባሕረ ሠላጤው አካባቢ ይንቀሳቀሳሉ። በእርግጥ ከአልቃይዳ ጋር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ነው ባይባልም በሶማሊያ ራሱን ከአልቃይዳ ስር እንደሚገኝ አድርጎ የሚጠቅሰው የሶማሌው ኧል ሸባብ የተሰኘው ታጣቂ ቡድንም ይገኛል።


አልቃይዳ ከተሰኘው አሸባሪ ቡድን ጋር ጠንካራ ትስስር ያላቸው ቡድናት በተለይ በአልጀሪያ፣ በማሊ እና በሊቢያ ይገኛሉ። በቅርቡ እንኳን ኢራቅ፣ ፓኪስታን እና ሊቢያ ውስጥ አሸባሪዎችና ፅንፈኞች በምዕራባውያን ላይ ጥቃት ከማድረሳቸውም ባሻገር የተለያዩ እስር ቤቶችን ሰብረው አባላቶቻቸውን ለማስለቀቅ ችለዋል። ይህ ድርጊት በእርግጥም ኢንተርፖልን ጨምሩ የምዕራቡ ዓለም የደኅንነት ተቋማት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ አስገድዷቸዋል። የአሜሪካው የስለላ ተቋም CIA የቀድሞ አባልና በቦስተን ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ፕሮፌሰር ጆሴፍ ቪፐል አሸባሪዎቹ እስረኞችን ለማስለቀቅ መቻላቸው የሚያሳየው ነገር አለ ይላሉ።

የተቃጠለ የዩኤስ ቆንስላ ጽ/ቤት በሊቢያ ቤንጋዚ

የተቃጠለ የዩኤስ ቆንስላ ጽ/ቤት በሊቢያ ቤንጋዚ«እስረኞችን ለማስለቀቅ መቻላቸው በእራሱ ሁለት ነገሮችን ያሳያል። በመጀመሪያ አቅሙ አላቸው ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ በእነዚህ የተለያዩ መንግሥታት ውስጥ አንዳንድ ለፅንፈኝነት ፍላጎቱና አዝማማያ ያለቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው። እናም ምናልባት እነዚህ ሰዎች እስረኞቹ ማምለጥ እንዲችሉ ሳያመቻቹ አልቀሩም። ሆኖም የአሁኑ የአደጋ ማስጠንቀቂያ በቀጥታ እስረኞቹን ከእስር ቤት ከማስለቀቁ ጋር የተያያዘ አይመስለኝም።»


ኢራቅ ውስጥም ቢሆን የአልቃይዳ አባላት ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ ነው፤ እዚያ ወደ 1000 የሚጠጉ የአልቃይዳ አባላት እንደሚገኙ ይገመታል። በሶሪያም እንዲሁ ከፕሬዚዳንት ባሽር ኧል አሳድ መንግስት ጋር በተናጠል ፍልሚያ ከገጠሙት ቡድናት መካከል «ጃባት ኧል ኑስራ ግንባር» የተሰኘ ቡድን ይገኛል። ይህ ቡድን ራሱን ጂሀዲስት ብሎ የሚጠራ ሲሆን ወደፊት በሶሪያ አነስተኛ የአሚር ግዛት ማቋቋምን እንደግቡ አድርጎ ነው የሚንቀሳቀሰው። ቡድኑ ወደፊት እስራኤልን ማጥቃት ዓላማው እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲገልፅ ይደመጣል። በእርግጥ እስካሁን ይህ ቡድን በተቀረው ዓለም ላይ የሽብር ጥቃት ሲያካሂድ አልተሰማም። ለወደፊት ግን የሚታወቅ ነገር የለም። የአልቃይዳ ቅርንጭፍ በኢራንም ከተዘረጋ የቅርብ ጊዜ መባሉ እያከተመ ነው።


ኢድዋርድ ስኖውደን የቀድሞ የአሜሪካ ሰላይ

ኢድዋርድ ስኖውደን የቀድሞ የአሜሪካ ሰላይ

የሰሞኑ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ከወደ አሜሪካ የተሰማውም ይህ የአልቃይዳ ሶስተኛው ትውልድ የተሰኘው ቡድን በምዕራባውያን ተቋማት ላይ ዳግም ብርቱ የሽብር ጥቃት ሊያደርስ ነው በሚል ነበር። የሆኖ ሆኖ ግን አንዳንድ ተንታኞች ይህ የአሜሪካ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ ደወል የተሰማው የኦባማ አስተዳደር ከስለላ ጋር በተያያዘ በቅርቡ የተነሳበትን ተቃውሞ ለማዘናግያ በሚል ነው ሲሉ ይደመጣል። የአሜሪካን መንግሥት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የግለሰቦችና የመንግስታት መረጃዎችን በምስጢር አከማችቷል በሚል የሲ አይ ኤ ሰላይ የነበረው አሜሪካዊው ኤድ ዋርድ ስኖውደን በቅርቡ ጉዳዩን ለዓለም ይፋ ካደረገ በኋላ የኦባማ አስተዳደር ከተለያዩ የዓለማችን ክፍላት ከፍተኛ ጫና ደርሶበት እንደነበር ይታወሳል።


በእዚህም አለ በእዚያ በዓለማችን በአሁኑ ወቅት ራሳቸውን የአልቃይዳ አባላት ብለው የሚጠሩ ከ 10,000 በላይ ሰዎች እንደሚገኙ ይገመታል። የአልቃይዳ ካድሬ ሆነው የሚያገለግሉት ደግሞ በቁጥር 5000 ገደማ ይጠጋሉ ይባላል። ከእዚያ ባሻገር ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ የአልቃይዳ ደጋፊዎችና የዕርዳታ ቡድኖችም በተለያየ የዓለም ክፍል እንደሚገኙ ይነገራል።

ማንተጋፍቶት ስለሺሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic