፲፩ኛው የኡንታድ ጉባኤ በሳዎ ፓውሎ | ኤኮኖሚ | DW | 14.06.2004
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ኤኮኖሚ

፲፩ኛው የኡንታድ ጉባኤ በሳዎ ፓውሎ

ትናንት በሳዎ ፓውሎ/ብራዚል ሲዘጋጅ ከቆየ በኋላ ዛሬ እዚያው በይፋ ለስድስት ቀናት የተከፈተው የተባ መ የንግድና የልማት ጉባኤ(ኡንክታድ) ፲፩ኛ መድረክ ከ፩፻፺፪ ሀገሮች የተውጣጡ ከፍተኛ የንግድ ልኡካንን አሰባስቧል። አስተናጋጅ ብራዚል በንግድ ድርድር ረገድ በሐብታሙ ሰሜናዊ ዓለም አንፃር ሚዛን ይሆን ዘንድ፣ አንድ ደንዳና ደቡብ-ደቡብ ጥምረት ለመፍጠር እንደሚቻል ተሥፋ ታደርጋለች። በየአራት ዓመታት የሚከፈተው ጉባኤ በሚደረጁትና በደረጁት ሀገራት መ

�ከል ተመዛዛኝ የንግድ ግንኙነት የሚኖርበትን መንገድ ነው የሚከታተለው

የተባ መ ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ጭምር የሚሳተፉበትና እስከ ዓርብ የሚዘልቀው
ይኸው ፲፩ኛው የኡንክታድ ጉባኤ ብሔራዊ የልማት ስልቶች ከዓለም ኤኮኖሚ ሂደት ጋር የሚጣጣሙበትን መንገድ ነው የሚሻው። የዓለም ንግድ ድርጅት በካንኩን/ሜክሲኮ ያካሄደው ጉባኤ ከከሸፈ ከዘጠኝ ወራት በኋላ መሆኑ ነው አሁን የኡንክታድ መድረክ የተከፈተው።

ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ፩፻፴፪ የሚደረጁ ሀገሮችን ለሚያስተባብረው ለቡድን ፸፯ ባሰሙት ንግግር፣ በዓለምአቀፉ የንግድ ግንኙነት ረገድ ግዙፍ የሚዛን ዝንፈት መኖሩን አስገንዝበዋል። ኣናን ኡንክታድ እና ቡድን-፸፯ የተመሠረቱበትን ፵ኛ ዓውዳመት በማመላከት ያከሉት ማስገንዘቢያ፥ ከ፵ ዓመታት በፊት በዓለም ውስጥ ከነበረው የሚዛን ዝንፈት ይልቅ የዛሬው በጉልህ የባሰነው ይላል። ሆኖም፣ እርሳቸው እንደሚሉት፣ በድሃና በሐብታም መካከል ጎልቶ የነበረው እርስበርስ መወቃቀስና መካሰስ ላለፈው ዘመን ተትቶ፣ አሁን የጋራው መንገድ የሚፈለግበት ትብብር ነው መጠናከር ያለበት፣ ሁለቱም ወገኖች--ሐብታምና ድሃ--የኃላፊነትን ስሜት እያጎለመሱ፣ መግባባትን ለማጠናከር እንዲጥሩ አስፈላጊ ነው። የኡንክታድ ዋናፀሐፊ ሩቤንስ ሪኩፔሮ ያለፈውን ዘመን ሁኔታ መለስ ብለው በመመልከት እንደሚሉት፣ በብዙ የሚደረጁ ሀገሮች ውስጥ ሲንፀባረቅ የነበረው የገበያው ጽንሰሐሳብ ምኑን ያህል እንዳልሠመረ ተሞክሮ አሳይቷል።

የአውሮጳው ኅብረት የንግድ ተጠሪ ፓስካል ላሚ ደግሞ፣ ንግድ ነፃ የሚሆንበትን ስምምነት የሚመለከተው ቀጣዩ የድርድር ዙር ከመሰናክል እንዲድን መላው የዓለም ንግድ አባል-ሀገሮች በዚሁ አግጣጫ የበለጠ ጥረት እንዲያደርጉ ጥሪያቸውን አጉልተዋል። ወደ ፫ ዓመታት ከሚጠጋ ጊዜ በፊት በዶሃ/ቃታር የተጀመረው የዓለም ንግድ ድርድር ዙር ይነቃቃ ዘንድ፣ አሁን በተለይም ከዩኤስ-አሜሪካ፣ ከአውስትራሊያና ከካናዳ ነው አስፈላጊው ርምጃ እንደሚንቀሳቀስ ፓስካል ላሚ የሚጠብቁት። እንግዲህ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የስምምነቱ ጥረት ካልሠመረ፣ ድርድሩ ለምሳሌ በመፀው በሚካሄደው በአሜሪካው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ምክንያት ለረዥም ጊዜ ተሰናክሎ የሚቆይ ሊሆን ይችላል--በፓስካል ላሚ አስተያየት።

የተባ መ የንግድና የልማት ጉባኤ(ኡንክታድ) በእንዱስትረኞቹ ሀገራትና በሚደረጁት ሀገሮች መካከል የንግዱ ልውውጥ እንዲቃና ለማድረግ ነው የሚጥረው። ግን ጠቅላላው የጉምሩክና የንግድ ስምምነት/ጋት እና በዚህም ቦታ የተተካው የዓለም ንግድ ድርጅት ከተመሠረተ ወዲህ የዚያው የተባ መ ጉባኤ ትርጓሜ እየተቀነሰ ነው የተገኘው። የመጨረሻው የኡንክታድ መድረክ ከአራት ዓመታት በፊት በባንኮክ ነበር የተካሄደው።

-ያሁኑን ጉባኤ የምታስተናግደው ብራዚል የሚደረጁትን ሀገሮች በማስተባበር፣ በእነርሱው መካከል ብቻ አንድ የንግድ ውይይት እንዲፈጠርና ይህም ከዓለም ንግድ ድርጅት ድርድሮች ጎን እንዲካሄድ ለማድረግ ነው የምትሻው። በዚሁ የንግድ ድርድር ረገድ ብራዚል የምታደርገው ጥረት፥ እጅግ ጠንካራ ሆነው ከሚታዩት የሚደረጁ ሀገሮች መካከል የ፳ዎቹን ቡድን ለመመሥረት አስችሏታል። የዚሁ ቡድን-፳ አባላት አርጀንቲና፣ ብራዚል፣ ቦሊቪያ፣ ቺሌ፣ ቻይና፣ ኩባ፣ ግብጽ፣ ሕንድ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ሜክሲኮ፣ ናይጀሪያ፣ ፓኪስታን፣ፓራጓይ፣ ፊሊፒን፣ ደቡብ አፍሪቃ፣ ታንዛኒያ፣ ታይላንድ፣ ቬኔዙኤላ እና ዚምባብዌ ናቸው። የደቡባውያን ስብስብ የሚሰኘው ቡድን-፳ የዓለም ንግድ ድርጅት ድርድር በሚካሄድበት ጊዜ በሐብታሞቹ ወይም በሰሜናውያኑ መንግሥታት ላይ ግፊት በማበርከት፣ እነዚያው መንግሥታት ለግብርና ዘርፋቸው የሚሰጡትን የፊናንስ ድጎማ እንዲሰርዙት ወይም እንዲያሳንሱት የማድረግ ዓላማ ነው ያለው።