ኖቤል የሠላም ሽልማትና ሊዩ | ዓለም | DW | 08.10.2010
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ዓለም

ኖቤል የሠላም ሽልማትና ሊዩ

የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የ2010ሩ የሥላም ኖቤል ሽልማት ለመሠረታዊ ሠብአዊ መብት መከበር ለረጅም ጊዜ ላደረጉት ሠላማዊ ትግል ለ ሊዩ ሺኦቦ እንዲሰጥ ወስኗል

default

ሊዩ ሺኦቦ

08 10 10

የዘንድሮዉ የሠላም ኖቤል ሽልማት በእስር ላይ ለሚገኙት ለቻይናዊዉ የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብት ተሟጓች ለ ሊዩ ሺአቦ ተሠጠ።የሐምሳ አራት አመቱ ጎልማሳ ፥ የቀድሞዉ የዩኒቨርስቲ የፅነ-ሥሁፍ መምሕር የቻይና ኮሚንስታዊ ሥርዓት እንዲለወጥ በመጠየቃቸዉ ተወንጀለዉ አሥራ-አንድ አመት እስራት ተበይኖባቸዋል።የኖርዌዉ ሸላሚ ድርጅት ዛሬ እንዳስታወቀዉ ሊዩ የተሸለሙት ለመሠረታዊዉ የሰዉ ልጆች መብት መከበር ለረጅም ጊዜ ላደረጉት ሠላማዊ ትግል ነዉ።ቻይና የሊዩን መሸለም ተቃዉማዋለች።ሌሎች ግን ደግፈዉታል።ነጋሽ መሐመድ ዝር ዝር ዘገባ አለዉ።

በ1996 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሮሳዉያኑ አቆጣጠር ነዉ) በሠርጋቸዉ ማግሥት «ዳግም ትምሕርት በጉልበት አገልግሎት» በሚለዉ የቻይና ኮሚንስታዊ መርሕ መሠረት ለሰወስት አመት ተጋዙ።ያኔ አርባ አንድ አመታቸዉ ነበር።ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መታሠር-መፈታት እንግዳቸዉ አልነበረም።ባለፈዉ አመት ታሕሳስ አስራ-አንድ አመት እስራት ሲበየንባቸዉ ግን በደጋፊዎቻቸዉ በኩል ባሰራጩት መግለጫ «ምግባሬ ፍትሐዊ ነዉ ብዬ አምናለሁ።ቻይናም አንድ ቀን ነፃና ዲሞክራሲያዊት ሐገር ትሆናለች።» አሉ

ከሁለቱ እምነቶቻቸዉ የሁለተኛዉ-ቻይና የነፃነትና የዲሞክራሲ ሐገር የምትሆንበት ቀን ምናልባት በእሳቸዉ እድሜ አይታይ ይሆናል።ምግባሬ ፍትሐዊ ነዉ-ያሉት የመጀመሪያዉ እምነታቸዉ ትክክለኛነት ግን በወገን ደጋፊዎቻቸዉ ከመመስከር አልፎ-በአለም አቀፉ ታላቅ ሽልማት ሸላሚ ኮሚቴም ተረጋገጠ።የኮሚቴዉ ሊቀመንበር ቶርብዮርን ያግላንድ-ዛሬ።

«የኖርዌዉ የኖቤል ኮሚቴ የ2010ሩ የሥላም ኖቤል ሽልማት ለመሠረታዊ ሠብአዊ መብት መከበር ለረጅም ጊዜ ላደረጉት ሠላማዊ ትግል ለ ሊዩ ሺኦቦ እንዲሰጥ ወስኗል።»

ሊዩ በቤጂግ የኖርማል ዩኒቨርስቲ የሥነ-ፅሁፍ መምሕር ነበሩ።በ1989 የቻይናን ኮሚንስታዊ ሥርዓት በመቃወም ታይናሚን-ቤጂንግ አደባባይ ተሠልፈዉ የነበሩ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን በመደገፋቸዉ ሁለት አመት ታሠሩ። ከሚሠሩበት ዩኒቨርቲ ተባረሩም።

ከእስር ከተለቀቁ በሕዋላም ለሰብአዊ መብት መከበር የሚያደርጉትን ትግል አጠናክረዉ ቀጠሉ እንጂ አላቋረጡም።በ2001 የቻይና መንግሥት ፋሉን-ጎንብ በተባለዉ የሐማይኖት ሐራጥቃ ተከታዮች ላይ የወሰደዉን እርምጃ በመቃወማቸዉ «ፋሉን-ጎንግ የመጨቆኑ ዋጋ (መዘዝ)» በሚል ርዕሥ ያሳተሙት መጣጥፍ በተለይ በምዕራቡ አለም ከፍተኛ ድጋፍና አቅድናቆት አስገኝቶላቸዋል።

ሊዩ ቻይና የሁለት ሺሕ ስምንቱን የአለም ኦሎምፒክ ለማስተናገድ ስትመረጥ ኮሚንስታዊ መሪዎቿ አጋጣሚዉን የሰብአዊ መብት ለማክበር እንዲጠቀሙበት የዉጪዎቹም ግፊት እንዲያደርጉባቸዉ ጠይቀዉ ነበር።የሰማቸዉ የለም።ባመቱ «ቻርተር 08 ለዲሞክራሲያዊ ለዉጥ» ያሉትን ፅሑፍ ለማሳተም ሲዘጋጁ ታሰሩ።

በታሰሩ ባመቱ አስራ-አንድ አመት ተፈረደባቸዉ።አምና ታሕሳስ።በተፈረደባቸዉ ባመቱ ዘንድሮ ተሸለሙ።የቻይና መንግሥት ክፉኛ ተናደደ።የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስቴር ዛሬዉኑ ባወጣዉ መግለጫዉ የሊዩ መሸለም የቻይናንና የኖርዌን ግንኙነት ይጎዳዋል።የሠላም ሽልማቱን ክብርም ይቃረናል።ሌሎች ብዙ መንግሥታት ግን የሊዩን መሸለም ደግፍዉታል።የጀርመን መንግሥት ቃል አቀባይ ሽቴፈን ሲበርት ደግሞ ሊዩን «ደፋር» ብለዋለቸዋል።
ድምፅ
«የፌደራላዊ መንግሥት የተሰማዉን ደስታ ለቻይናዊዉ ተሸላሚ ይገልጣል።በሐገራቸዉ ዲሞክራሲና ሰብአዊ መብት እንዲሰፍን በፅናት የታገሉና ትግሉንያ ያገዙ፥ የዚያኑ ያክል ትግሉ የረጅም ጊዜ የሚፈጅ ሒደት እንደሆነ፥ ከሁሉም በላይ የረጅም ጊዜዉ ትግል ከአፅና ግጭት ነፃ መሆን እንደሚገባዉ የሚያዉቁና በተደጋጋሚ የተናገሩ ደፋር ሰዉ ናቸዉ።---»

ለዘንድሮዉ የሰላም ኖቤል ሽልማት ከታጩት የቀድሞዉ የጀርመን መራሔ መንግሥት ሔልሙት ኩል አንዱ ነበሩ።የአፍቃኒስታንዋ የሴቶች መብት ተሟጋች ሲማ ሳማራና ሩሲያዊቷ የመብት ተሟጋች ስቬትላና ጋኑሽኪና በግንባር ቀደምትነት ተወዳድረዉ ነበር።ሊዩ አሸነፉ።

ነጋሽ መሐመድ

አርያም ተክሌ


Audios and videos on the topic