ኖርዌይ የሽብር ሰለቦችዋን አሰበች | አውሮጳ/ጀርመን | DW | 24.07.2011
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

አውሮጳ/ጀርመን

ኖርዌይ የሽብር ሰለቦችዋን አሰበች

ከትናንት በስትያ ኖርዌይ ዉስጥ በደረሰ ሁለት ጥቃት ለጠፋ ወደ መቶ ለሚጠጋ ህይወት አገሪቱ ዜጎችዋን በመንፈሳዊ የሃዘን ስነ-ስርአት አሰበች።

default

በኦስሎ ከተማ በሚገኝ ኦስሎ ዶም በተሰኝዉ ካቴድራል በተደረገዉ የሃዘን ስነ-ስርአት ላይ ከጥቃቱ የተረፉ ግለሰቦች፣ በጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ቤተሰቦች፣ የንጉሳዉያን ቤተሰቦች እንዲሁንም የአገሪቷ ጠቅላይ ሚኒስትር የንስ ስቶልትንበርግ እና መላ የአገሪቱ ባለስልጣናት ተገኝተዋል። በኦስሎ በመንግሥቱ መቀመጫ ቀበሌ በመኪና ዉስጥ ቦንብ በመጥመድ ሰባት ሰዎችን የገደለዉ እና በርካታ ህንጻዎችን ከጥቅም ዉጭ ያደረገዉ የሰላሳ ሁለት አመቱ የኖርዌይ ተወላጅ ቦንቡን ለመስራት ስድስት ቶን ማዳበርያ መግዛቱን ፖሊስ አረጋግጦአል። ዋና ከተማይቱ ኦስሎ አጠገብ በኡቶያ ደሴት በሚገኘው በመንግሥቱ ሶሻል ዴሞክራቶቲክ ፓርቲ የወጣቶች ካምፕ ዉስጥ ቢያንስ 85 ወጣቶችን የገደለዉም ከመንግስት በፈቃድ በወሰደዉ አዉቶማቲክ ጠመንጃ መሆኑ ተመልክቶአል። በዚህ በደረሰዉ ጥቃት ሌላ ሁለተኛ ወንጀለኛ መኖር አለመኖሩን ግን ፖሊስ አሁንም በማጣራት ላይ መሆኑን ሲያስታዉቅ የ 32 አመቱ ኖርዊጅያዊ አንድረስ ቤሄሪንግ ብራይቪክ የገዛ አገሩን ልጆች በግፍ መጨፍጨፉን «አሰቃቂ ግን በጣም አስፈላጊ» ሲል መጀመርያ በሰጥዉ ቃል መግለጹን ፖሊስ ይፋ አድርጎአል። ባለፈዉ አርብ ከቀትር በኋላ ኖርዌይ ዉስጥ ደርሶ በነበረው ድርብ ጥቃት የሞቱት ሰዎች ቁጥር በአሁኑ ሰአት ወደ 93 ከፍ ብሎአል።

Doppelanschlag Norwegen - Anders Behring Breivik

የ 32 አመቱ የኖርዌይ ተወላጅ አንድረስ ቤሄሪንግ ብራይቪክ

ሌላ አምስት ወጣቶች ግን እስካሁን እንዳልተገኙ እየተነገረ ነዉ። የኖርዌይ ልዩ ኮማንዶ ባለፈው አርብ ምሽት ወጣቶቹ የእረፍት ግዜያቸዉን ወደ ሚያሳልፉበት ደሴት በመዝለቅ የተኩስ ኡሩምታውን የከፈተውን የ 32 ዓመት ኖርዊጅያዊ ለመያዝ ከግማሽ ሰዓት በላይ እንደፈጀበት ለማወቅ ተችሏል። ተያይዞ እንደተጠቀሰው ወንጀለኛዉ በኢንተርኔት አማካይነት ያሰራጨው አንድ ሽህ አምስት መቶ ገጽ ያህል ያለዉ መልዕክት የቀኝ አክራሪነትና የእሥላም ጥላቻ ዝንባሌን የሚያረጋግጥ መሆኑ ተመልኮአል። በዚህም ወንጀለኛዉ ግድያዉን ለረጅም ግዜ ሲያቅድ መቆየቱ ታዉቆአል። ጠቅላይ ሚኒስትር የንስ ስቶልተንበርግ የደረሰዉ ጥቃት ብሄራዊ አደጋ እና በአገሪቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ የከፋው ነው ማለታቸዉ አይዘነጋም። ዓለምአቀፉ ሕብረተሰብም በበኩሉ በጥቃቱ ያደረበትን ድንጋጤና ቁጣ በመግለጽ ላይ ነዉ። ዋሺንግተን፣ ሞስኮ፣ ለንደንና እሥራኤል ለሕዝቡ የተሰማቸውን ሃዘን በመግለጽ ለመርዳት ዝግጁ መሆናቸውን ሲያስታውቁ ጀርመንም በዚህ በከባድ ሰዓት ከኖርዌይ ጎን እንደምትቆም ቻንስለር አንጌላ ሜርክል አስረድተዋል።


አዜብ ታደሰ

መስፍን መኮንን

ተዛማጅ ዘገባዎች