ንፁህ ዉሃ ለሁሉም | ጤና እና አካባቢ | DW | 20.03.2012
  1. Inhalt
  2. Navigation
  3. Weitere Inhalte
  4. Metanavigation
  5. Suche
  6. Choose from 30 Languages

ጤና እና አካባቢ

ንፁህ ዉሃ ለሁሉም

ከአዉሮጳዉያኑ 1997ዓ,ም ወዲህ በየሶስት ዓመቱ የዓለም የዉሃ መድረክ ጉባኤ ይካሄዳል። ዘንድሮም በስድስተኛዉ ጉባኤ ከአንድ መቶ ሰማንያ በላይ ሐገሮች ተሳትፈዋል። በመድረኩ ስምንት መቶ ተናጋሪዎች የቀረቡ ሲሆን የፈጠራ ሥራዎችም ታይተዋል።

ባለፈዉ ሳምንት ሰኞ ዕለት ተጀምሮ ቅዳሜ የተጠናቀቀዉ ይህ ጉባኤ ዉሃን በሚመለከት ዓለም የተጋረጠበትን ተግዳሮት በመዳሰስ በፖለቲካዉ አጀንዳ ከፍተኛ ስፍራ እንዲሰጠዉ ነዉ ያሳሰበዉ። ሳምንታዊዉ ጤናና አካባቢ መሰናዶ የዛሬዉ ትኩረቱ አድርጎታል።

ፈረንሳይ ማርሴል ዉስጥ ካለፈዉ መጋቢት ሶስት እስከ ስምንት 2004ዓ,ም የተካሄደዉ ስድስተኛዉ የዓለም የዉሃ መድረክ ከፖለቲካዉ፤ ከኤኮኖሚዉ፤ እንዲሁም ከሲቪል ተቋማት 20,000 ተሳታፊዎችን ያስተናገደ ነበር። የዓለም የዉሃ ቀን የፊታችን ሐሙስ ከመታሰቡ ጋ የተገጣጠመዉ ይህ ጉባኤ ከሶስት መቶ በላይ በሆኑት መድረኮችና የክብ ጠረጴዛ ዉይይቶቹ፤ የዓለማችንን የዉሃ ችግር ነቅሶ በማዉጣት ሲነጋገር ሰንብቷል። ችግሮችን ከመንቀስ በተጨማሪ፤ የተሻለ የተባሉ ልምዶችን በመጋራት አንድ ሳምንት በሰነበተዉ ጉባኤ የሞቀ ክርክር ያስነሳዉ የግል የዉሃ አቅርቦት ተግባር ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ጉዳይ ነዉ። ከጉባኤዉ በተጓዳኝም ዘጠና ዉሃ ላይ የሚሰሩ ኩባንያዎች የየራሳቸዉን ፈጠራ ያሳዩበት አዉደርዕይ አቅርበዋል። በዚህም በገጠር መንደሮች ዉሃን የማዉጣት፤ ብክነትን የመቀነስ፤ እንዲሁም እንዴት ዉሃን እና የንፅህና መጠበቂያ ስልቶችን ለሁሉም እንዴት ማዳረስ ይቻላል ለሚለዉ የመፍትሄ አማራጮችን ሁሉም በየስልታቸዉ ለማሳየት ሞክረዋል።

Wasser Trinkwasser Wasserhahn läuft

የግል ኩባንያዎች የዉሃ አቅርቦት አገልግሎት ዉስጥ እጃቸዉን መክተታቸዉን የሚቃወሙ ወገኖች በበኩላቸዉ ከየሐገራቱ ተሞክሮ በመነሳት ችግሮችን ለማሳየት ጥረዋል። የፊሊፒንስ የዉሃ መብት ተሟጋች ማሪያ ቴሬሳ N ላዉሮን በሐገራቸዉ ያለዉን ለጉባኤዉ አጋርተዋል፤

«በአሁኑ ጊዜ ፊሊፒንስ ደቡብ እስያ ዉስጥ ከፍተኛዉ የዉሃ መጠን አለ። ከ1997ዓ,ም ከ450 እስከ 800 በመቶ የሚደርስ የዋጋ ጭማሪ ዉሃ ላይ ታይቷል። በዚያ ላይ የዉሃዉ ጥራት እጅግ ተበላሽቷል። ታዉቃላችሁ አብዛኛዎቹ የሐገራችን ዜጎች ለዉሃ ወለድ በሽታ የተጋለጡ ናቸዉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት በእነዚህ የግል ተቋራጮች ምክንያት የዉሃ አገልግሎቱ ቁጥጥር ባለመካሄዱ ወደስድስት መቶ የሚጠጉ ሰዎች ከእኛዉ ዉሃ ኢኮሎ በተሰኘዉ ተህዋሲ ተጎድተዉ ህይወታቸዉን አጥተዋል።»

በተቃራኒዉ በግል የዉሃ አቅርቦት አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎችን ተግባር ከሁሉም አኳያ የሚወቀስ እንዳልሆነ የግል የዉሃ አቅርቦት ኩባንያዎችን ማኅበር አባል ከሆነዉ አኳፌድ ጌራርድ ፓየን ይህን ይላሉ፤

Kind mit Wasser in Afrika Flash-Galerie

«እኔ እስከማዉቀዉ ድረስ ማኒላ ዉስጥ የዉሃ አገልግሎት በሁለት የግል ኩባንያዎች አማካኝነት ትርጉም ያለዉ መሻሻል አሳይቷል። በፊት ዉሃ ያልነበራቸዉ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዉሃ ማግኘት ችለዋል። በግሌ የእኔ ኩባንያ አንድ ጎስቋላ መንደር ዉስጥ ያዘጋጀዉን አዲስ የዉሃ አገልግሎት ምረቃ አስታዉሳለሁ። ህዝቡ ሲደሰትና በፈገግታ ተሞልቶ ተመልክቻለሁ። እየተሰቃዩ ሳይሆን አዲስ ህይወትን እያገኙ ነዉ።»

በምድራችን የሚታየዉን የንፁህ ዉሃ አቅርቦት ችግር ለማስወገድ በተመድ ሥር አንድ ለዉሃ ልማት የሚዉል የገንዘብ አሰባሳቢና አቅራቢ ተቋም እንዲመሠረት የዓለም ዓቀፍ የዉሃ መድረክ ፕሬዝደንት ቤኔዲቶ ብራጋ ያቀረቡት ሃሳብ ግን ተቃዉሞ አላጣዉም። ፈረንሳይ ዉስጥ በምህፃሩ አታክ የተሰኘዉ የፀረ አፅናፋዊ የዓለም ትስስር ድርጅት ተጠሪና የዓለም የማኅበራዊ መድረክ የቦርድ አባል ጉስታቭ መሲያ እንዲህ ያለዉ ተቋም ችግሩን ይብስ ያወሳስብ እንደሆነ እንጂ አይፈታዉም ነዉ የሚሉት፤

«ዓለም ዓቀፍ የዉሃ ፋይናንስ ለየሐገራቱ የሚሰጠዉን ዉሳኔ የማሳለፍ ኃይል ከተሰጠዉ ይሄ መፍትሄ ነዉ ሊባል አይችልም። በተቃራኒዉ ያለዉን የአሰራር ችግር ይበልጥ ያወሳስበዉ ይሆናል።»

እሳቸዉ ያነሱትን ስጋት በተግባር ካዩት የአሠራር ሁኔታ ጋ በማገናዘብ ተቃዉሞዉን ያጠነከሩት ሴፌጅ አፍሪቃ የተሰኘዉ ኩባንያ የቀድሞዉ ኃላፊ ዣክ ካምቦን፤ በዓለማችን ትላልቅ ለተባሉ ፕሮጀክቶች ገንዘብ የሚያበድረዉ የዓለም ባንክ፤ የፕሮጀክቶቹ ዉሳኔና አሠራር በሐገር ዉስጥ ክትትል ሊከናወን ሲገባ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ጣልቃ መግባታቸዉ ሂደቱን ሲያጓትት መታየቱን ጠቁመዋል። ንፁህ ዉሃ ለሁሉም ይዳረስ የሚል መፈክር አንግበዉ በየመድረኩ የሚሟገቱት ወገኖች ማርሴል ላይም አልቦዘኑም። የዉሃን ዋጋ የሚያንረዉ ለእርሻና ሌሎች አገልግሎቶች የሚዉለዉ መጠን መጨመር እንደሆነ በማሳየትም ዋጋዉ እንዲመዘን ጠይቀዋል። ከተሟጋቾቹ አንዱ፤

Wasserknappheit in China

«ዉሃዉ ለእርሻ ተግባር ጥቅም ላይ እየዋለ ነዉ፤ በተለይም ከፍተኛ ለሆኑት የእርሻ ልማት፤ ዉሃዉ ለኢንዱስትሪም እንዲሁ ይዉላል፤ ይህ ግን በየቤቱ ጥቅም ላይ ከሚዉለዉ ጋ አንድ ሊሆን አይችልም።»

ይህን ያነሳዉ አታክ እና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የኢንዱስትሪዉ ዘርፍ ሊከፍል የሚገባዉ የዉሃ ዋጋ ከፍ ሊልና ከቤት ዉስጥ አገልግሎት ሊበልጥ ይገባል የሚል ጥያቄ ሰንዝረዋል። ስለ ዉሃ ዋጋ መነጋገር የሚቻለዉ ቅድሚያ የዉሃ አቅርቦቱ ሲስተካከል ነዉ የሚሉ ወገኖች በበኩላቸዉ አንድ ሰዉ በቀን የሚጠቀምበት 15 ሊትር ዉሃ በነፃ ሊያገኝ ይገባል ባይ ናቸዉ። ሃሳቡ ባይከፋም በተመድ የዉሃ መብት ደንብ ላይ ሰፍሮ ተግባራዊ የመሆኑ ነገር ግን ያጠራጥራል የሚሉትም በርክተዋል። የመንግስታቱ ድርጅት የዉሃ መብት ልዩ ራፖርተር ካትሪነ አልቡከርክ ግን የህጉ እዉቅና ማግኘት ለዉይይት መቅረብ አይኖርበትም ይልቁንስ ለተግባራዊነቱ እንታገል ሲሉ ተሰብሳቢዎቹን ተማፅነዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ሂሩት መለሰ

Audios and videos on the topic